Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰበር ችሎት ዳኞችን ተሳድበዋል የተባሉ ባለሀብት ችሎት በመድፈር ወንጀል ከእነ ቤተሰቦቻቸው ታሰሩ

የሰበር ችሎት ዳኞችን ተሳድበዋል የተባሉ ባለሀብት ችሎት በመድፈር ወንጀል ከእነ ቤተሰቦቻቸው ታሰሩ

ቀን:

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የተጠየቁ የሰበር ችሎት ዳኛ ፈቃደኛ አልሆኑም

 

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ ፍርድ በሰበር ሰሚ ችሎት በመፅደቁ የተበሳጩ ባለሀብት፣ የችሎቱን ክብር በማሳጣትና የዳኞችን ሞራል በሚነካ ሁኔታ ተሳድበዋል ተብለው ችሎት በመድፈር ወንጀል ሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ተይዘው ከእነ ቤተሰቦቻቸው ታሰሩ፡፡

- Advertisement -

 

ባለሀብቱ የሕክምና ባለሙያ፣ የመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች አስመጪ ድርጅት ባለቤት ናቸው የተባሉት ዶ/ር በዕውቀቱ ታደሰ ናቸው፡፡ እሳቸው ዳኞችን በመሳደብና የችሎቱን ክብር በመንካት ላይ እያሉ የእሳቸውን ድርጊት በመደገፍ ያልተገባ ሁኔታ አሳይተዋል ተብለው አብረው በቁጥጥር ሥር ውለው በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ እንዲታሰሩ የተደረጉት ደግሞ መሠረት (የአባታቸው ስም ያልተገለጸ)፣ ጥሩወርቅ በረድድ፣ ቴዎድሮስ በረደድ፣ አገሬ በረደድና እና መንግሥቴ የሚባሉ ግለሰቦች መሆኑንም ሪፖርተር ለማጣራት ችሏል፡፡

ዶ/ር በዕውቀቱን ለእስር ያበቃቸው ጉዳይ የተጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት መሆኑንና ከፋብሪካ ሽያጭ ጋር የተያያዘ እንደሆነ፣ ሪፖርተር ካገኘው መረጃ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) የሚገኘውን ንብረትነቱ የአቶ ጌታቸው እሸቱ የሆነ ‹‹ጌትሸት የዲተርጀንትና ሳሙና ፋብሪካ››፣ ዶ/ር በዕውቀቱ ከስድስት ዓመታት በፊት መግዛታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዶ/ር በዕውቀቱ ፋብሪካውን ከገዙ በኋላ ለሻጭ የተወሰነ ገንዘብ ይከፍሉና ሻጭ ያለባቸውን የባንክ ዕዳ ሰባት ሚሊዮን ብር ሊከፍሉ ይስማማሉ፡፡ የሽያጩ ስምምነት ከተደረገ በኋላ አቶ ጌታቸውና ዶ/ር በዕውቀቱ ያልተስማሙበት ምክንያት በመፈጠሩ፣ አቶ ጌታቸው የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐ ብሔር ክስ መመሥረታቸው ታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካከራከረ በኋላ ዶ/ር በዕውቀቱ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ትዕዛዝ በመስጠት የሽያጭ ውሉን ያፀድቃል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ፍርድ ቅር የተሰኙት ዶ/ር በዕውቀቱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ይላሉ፡፡ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በመመርመር ላይ እያለ የፋብሪካው ሻጭ አቶ ጌታቸው ዶ/ር በዕውቀቱ አጠቃለው እንደገዙ የሚናገሩት ፋብሪካ ሁለት ካርታ ያለው መሆኑን በመግለጽ፣ የሸጡት በፋብሪካው ስም በተሠራው የይዞታ ማረጋገጫ ላይ ያለውን እንጂ በስማቸው የተሠራውን 13,015 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ አለመሆኑን በማስታወቅ ሌላ ክስ ማቅረባቸውንም የሪፖርተር መረጃ ያረጋግጣል፡፡

ሁለቱም ወገኖች ያቀረቡትን የክስ አቤቱታና የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ የመረመረው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ ሁለቱንም መዝገቦች በማጣመር ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በሰጠውም ፍርድ የፋብሪካውን ሽያጭ አፅድቆ፣ በአቶ ጌታቸው ስም የተሠራው የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) ላይ ያለውን 3,015 ካሬ ሜትር ቦታ የአቶ ጌታቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዶ/ር በዕውቀቱ 17 ሚሊዮን ብር ለአቶ ጌታቸው እንዲከፍሉም ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔና ትዕዛዝ ያበሳጫቸው ዶ/ር በዕውቀቱ፣ ለሰበር ሰሚ ችሎት መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመግለጽ አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ችሎቱም የሥር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትን ፍርድ ሲመረምር፣ የተሰጠው ፍርድ የሚነቀፍ ሆኖ ስላላገኘው ሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ያፀድቀዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑን ያወቁት ዶ/ር በዕውቀቱ፣ ፍርዱን ያፀደቁትን ዳኞች በመስደብና የችሎቱንም ክብር በመንካት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በመዋል ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል፡፡

ዶ/ር በዕውቀቱና አብረዋቸው የታሰሩት አምስት ግለሰቦች ረቡዕ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. አምስት ዳኞች በሚሰየሙበት ሰበር ሰሚ ችሎት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በችሎት መድፈር ስለመታሰራቸውና ስለሰነዘሩትም ስድብም ሆነ የችሎት ክብር ማሳጣት ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ ከችሎቱ አስቻይ ዳኞች አንዱ የነበሩትን የሰበር ችሎት ዳኛ አቶ ተኽሊት ይመስልን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ‹‹ጉዳዩ ገና በሒደት ላይ ነው፡፡ ደብዳቤ ጽፈውም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ በአምስት ዳኞች ታይቶ የሚወሰን ጉዳይ በመሆኑ ከውሳኔ በኋላ ጠይቁ፤›› በማለት ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ውሳኔ ያረፈበትን መዝገብ እንኳን ለማየት የቀረበላቸውን ጥያቄም ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...