Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበጦር መሣሪያ በታገዘ ዝርፊያ የተጠረጠሩ 1,680 ግለሰቦች በ1,300 መዝገቦች ክስ ተመሠረተባቸው

በጦር መሣሪያ በታገዘ ዝርፊያ የተጠረጠሩ 1,680 ግለሰቦች በ1,300 መዝገቦች ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

ኅብረተሰቡን ሥጋት ላይ የሚጥሉ ከባድና አደገኛ ወንጀሎችን በጦር መሣሪያ በመታገዝ በመፈጸም የተጠረጠሩ 1,680 ግለሰቦች ላይ በ1,300 የክስ መዝገቦች በማደራጀት ክስ እንደተመሠረተባቸው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

 

ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲን በመተካት በቅርቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ ጌቱ አራጋው ሰኞ ግንቦት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በሌብነት፣ በቅሚያና በኪስ ስርቆት በአጠቃላይ 8,354 ወንጀሎች ተመዝግበዋል፡፡

- Advertisement -

 

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል ወንጀሎችን 85 በመቶ ለማጣራት ዕቅድ የተያዘ ቢሆንም፣ ማጣራት የተቻለው ግን 68 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተፈጸሙት ወንጀሎች ውስጥ ቤት በመስበር ስርቆት፣ በመኪና ስርቆትና ሞባይል በመቀማት ውንብድና ላይ ተሰማርተዋል ከተባሉ 1,948 ግለሰቦች መካከል፣ በ1,680 ተጠርጣሪዎች ላይ መረጃና ማስረጃ ማሰባሰብ በመቻሉ በ1,300 የክስ መዝገቦች ክስ እንደተመሠረተ ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡

ፖሊስ በቡድን ተደራጅተው በዘረፋ ላይ የተሰማሩትን ብቻ ሳይሆን የራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ የጫት መቃሚያ ቤቶች፣ የቁማር ቤቶችና ሌሎች ወንጀል መፈጸሚያ ቦታዎችን በጥናት ታግዞ ልዩ ክትትል በማድረግ፣ በድርጊቱ የተሰማሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተካተቱበት የወንጀል ድርጊትና ሕገወጥ ተግባራትን በቁጥጥር ሥር እያዋለና ለሕግ እያቀረበ መሆኑን ኮሚሽነር ጌቱ አስረድተዋል፡፡

ቅዳሜ ግንቦት 3  ቀን 2011 ዓ.ም. በልዩ ክትትል ሲጠኑ በነበሩና ቦሌ አካባቢ በሚገኙ 12 ሺሻ ማጨሻ ቤቶች ላይ በተደረገ ድንገተኛ የዘመቻ ፍተሻ ሺሻ በማጨስ፣ አደንዛዥ ዕፅ በማጨስና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ተግባራትን ሲፈጽሙ የተገኙ የውጭ አገሮች ዜጎችን ጨምሮ ከ600 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በሺሻ ማጨሻ ቤቶች ውስጥ ዘመናዊና እጅግ ውድ የሆኑ የሺሻ ማጨሻ ዕቃዎች፣ ግማሽ ኪሎ ሐሺሽ፣ ሽጉጦችና ሌሎች ሕገወጥ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ ከተያዙት ግለሰቦች ውስጥ በሌላም ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ ስምንት ግሰቦችም በመያዛቸው፣ እነሱ ለተጨማሪ ምርመራ በማስቀረት ሌሎቹን 600 ግለሰቦች በመምከር ከእስር እንዲፈቱ መደረጉንም አቶ ጌቱ ገልጸዋል፡፡

በዘጠኝ ወራት አፈጻጸም 12,326 ከባድ የወንጀል ዓይነቶች መመዝገባቸውንና በየሩብ ዓመቱ ግን በ19 በመቶ መቀነሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በተደረገ ጥረት 10,732 ሽጉጦች፣ አራት መትረየሶች፣ 30 ክላሽኒኮቭ ጠብመንጃዎች፣ 99,785 የሽጉጥ ጥይቶችና 18,974 የክላሽኒኮቭና የመትረየስ ጥይቶች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

ሐሰተኛ የኢትዮጵያ ብር እያተሙ የሚያሠራጩ ሕገወጦች ጭምር መኖራቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ 181,379 ዶላር፣ 12,620 ፓውንድ፣ 9,930 ዩሮ፣ 4,615 ዩዋንና 111,145 የሌሎች አገሮች ገንዘቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም አክለዋል፡፡

ዝርፊያ የሚካሄደው በዋናነት በቪትስና በሞተር ብስክሌቶች መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ የሰሌዳ ቁጥር የሌላቸው ከ15 ሺሕ በላይ ሞተር ብስክሌቶች፣ ሚኒባሶችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

ወንጀል ከሚፈጸምባቸው ተሽከርካሪዎች የተወሰኑት በኪራይ የሚገኙ ቢሆኑም፣ ከስርቆቱ ጀርባ ባለቤቶቹም አሉ ተብሎ ስለሚገመት እነሱም የሕግ ተጠያቂ መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ አዲስ አበባ ከተማን ከወንጀል የፀዳ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በቅርቡ በተደረገ ግምገማ ጥቆማ በተደረገባቸው የፖሊስ አባላት ላይ ዕርምጃ መውሰዱንና ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመው፣ ‹‹ፖሊስ ሲነገረው ችላ ይላል፣ ክትትል አያደርግም፣ ከሌባ ጋር ይተባበራል፣ እንዳላየ ዓይቶ ያልፋል፣ ግዴለሽ ሆኗል. . .›› እና ሌሎችም ጥቆማዎችን እስከ ማዕከል ድረስ ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ ኮሚሽኑም የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወስድም አስታውቀዋል፡፡

ኅብረተሰቡ የተለየ ዘዴ በመጠቀም ዝርፊያ ከሚያካሂዱ ማለትም በንፁኃን ልብስ ላይ ቀለም በመቀባት፣ በመግፋት፣ የሞባይል ስልክን በተከፈተ የተሽከርካሪ መስኮትና በመንገድም ላይም ቀምቶ መሮጥ ስላለ መጠንቀቅ እንዳበትም አሳስበዋል፡፡

ፖሊስ ኑሮውን የተሻለና ከገቢ አንፃር ሕይወቱን የተሟላ በማድረግ ለተሰማራበት ሥራ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ ለማድረግ፣ በ2012 በጀት ዓመት ተጀምረው በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቁ በስድስት ይዞታዎች ላይ ባለ አሥርና 15 ፎቅ ሰባት ሕንፃዎችን በአራት ቢሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ኮሚሽነር ጌቱ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...