Saturday, May 18, 2024

የሚዲያ ሪፎርም ተስፋና ፈተናዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አገሪቱ አሁን በምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት የተደነገገ ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱን በኢትዮጵያ ለማስፈን ለታለመው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በምሰሶነት ከሚገለጹ ድንጋጌዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ መብት ከተገለጸበት የሕገ መንግሥቱ ገጽ ወርዶ መተግበርና መሬት መያዝ ሳይችል 24 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ ለዜጎች የተፈቀደ ሆኖ ሳለ በተግባር አለመታየቱ ልዩ ያደርገዋል እንጂ፣ በቀደሙት የዘመናዊ ኢትዮጵያ መንግሥታት የአገዛዝ ዘመንም አገሪቱና ሕዝቧ የሰው ልጆች በተፈጥሮ የሚያገኙትን የመናገር ነፃነትና በዚህ ተፈጥሮአዊ መርህ ውስጥ የተወለደውን የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ፍሬ ቀምሰዋል ማለት አይቻልም፡፡

የዚህ ጎደሎ ዕጣቸው ቀዳሚ ምክንያት ደግሞ የመንግሥታት ጣልቃ ገብነትና አፈና፣ እንዲሁም ሙያተኞችን የማሳደድና ወህኒ ቤት የመወርወር ተደጋጋሚ ተግባር ስለመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) እና ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት እንደ ሲፒጄ (CPJ)፣ ሂውማን ራይትስ ዎች (HRW)፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉ ተቋማት ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በየዓመቱ ሲያወጧቸው በነበሩ ሪፖርቶች ለታሪክ ያስቀመጡት ሀቅ ነው፡፡ በእነዚህ ሪፖርቶችም ጋዜጠኞችን በማፈን፣ በማሳደድና በማሰር ኢትዮጵያ በዓለም ከሚታወቁ አገሮች መካከል አንዷ እንደሆነች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ሥልጣን ላይ የሚገኘው የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግሥት፣ በእነዚህ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ደንግጦ ለማስተካከል እስከ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ድረስ ፈቅዶም ሞክሮም አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡

በሕዝባዊ እምቢተኝነትና ለውጥ በናፈቃቸው ተራማጅ የኢሕአዴግ ኃይሎች በራሱ በፓርቲው ውስጥ ባቀጣጠሉት ትግል በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. በድንገት የተወለደው ለውጥ፣ የቀደመውን ታሪክ ለመቀየር ቁርጠኝነቱን በቃልም በተግባርም ከመጀመርያው ዕለት አንስቶ በማሳየት ብሩህ ተስፋን በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ ፈንጥቋል፡፡

የውስጥ ትግሉን አሸንፎ ወደ ሥልጣን የመጣው ተራማጁ የኢሕአዴግ ኃይል በመንግሥትነት በቆየበት ባለፉት 13 ወራት የአንድ ዓመት ውስጥ የጋዜጠኝነት የሙያ ተግባራቸውን በመወጣታቸው ምክንያት ከወንጀል ሕጉ እስከ ፀረ ሽብር ሕጉ ያሉ አንቀጾች ተጠቅሰውባቸው የተወነጀሉና የተፈረደባቸው ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሠሩ በመፍቀድና በማመቻቸት ቃሉንና ተግባሩን ዕውን አድርጓል፡፡ ተዘግተው የነበሩ ከ200 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ድረ ገጾች እንዲከፈቱ፣ በአገር ውስጥ መሥራት ባለመቻላቸው በተሰደዱበት አገር የቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም በሳተላይት አማካይነት ፕሮግራማቸውን ሲያስተላልፉ የነበሩ፣ በወቅቱም በኢትዮጵያ ሕግ እንደ አሸባሪ የተቆጠሩ የመገናኛ ብዙኃን በአዲስ አበባ ቢሯቸውን ከፍተው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል፡፡

በዚህ ብቻም አልበቃም፡፡ አፋኝ የነበረው የሚዲያ ሕግ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን በሥራቸው ምክንያት በአሸባሪነት ለመፈረጅና ለመወንጀል ጥቅም ላይ ሲውል የቆየው የፀረ ሽብር ሕጉና ሎሎች ከዴሞክራሲና ከሕግ የበላይነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሕጎች እንዲሻሻሉ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን በማቋቋም ሕጎቹን የማሻሻል ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በተገለጸው ጊዜ ውስጥም የሲቪክ ማኅበራት ሕጉን ጨምሮ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂንና የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ ሕጎችን በማሻሻል በፓርላማው እንዲፀድቁ አድርጓል፡፡

ይኼንን በአንድ ዓመት ውስጥ የታየውን ለውጥ የተገነዘበው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ተቋም (UNESCO) በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 2 ቀን የሚካሄደውን የዓለም የሚዲያ ነፃነት ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር በመወሰን፣ ከሳምንት በፊት ከበርካታ አገሮች የተወጣጡ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ምሁራን በታደሙበት ተከብሮ አልፏል፡፡

በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት እንዲከበር ሲወተውቱና ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ውጣ ውረድ ሰንደው የያዙት ቀደም ሲል የተገለጹት ዓለም አቀፎቹ ተሟጋች ተቋማት፣ በዚህ ዓመት ሪፖርታቸው ኢትዮጵያ በዓለም የሚዲያ ነፃነት የደረጃ እርከን ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ አርባ ደረጃዎችን ወደፊት በማሻሻል 110ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ባለፉት 12 ወራት የተከናወኑት የለውጥ ተግባራት ማስቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይኼንን የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ቀን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ አገሮች ለመጡ ተሳታፊዎችና የአገር ውስጥ የሚዲያ ባለሙያዎች የእራት ግብዣ ያደረጉት የዚህ ለውጥ ፊት አመራር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የአንድ ዓመት የለውጥ ተግባራትን የተመለከቱና በፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም አሁንም አጠንክረው የያዙትን እምነትና የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን ባደረጉት ንግግር አጠናክረዋል፡፡

በዚህ ንግግራቸውም፣ ‹‹አሁን ኢትዮጵያ በመናገር የሚገኘውን በረከት የምትሻበት እንጂ፣ ለዘመናት እንዳደረገችው ተናጋሪውንም ንግግሩንም ደብዛውን የምታጠፋበት ዘመን ተደምድሞ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል፤›› በማለት፣ በዓለም ጋዜጠኞች ፊት የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን፣ ለኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ ተዋናዮች  ደግሞ ቀድመው የፈነጠቁትን ተስፋ በድጋሚ አድሰዋል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ማለት የጋዜጠኞች ነፃነት ብቻ ማለት እንዳልሆነ በወቅቱ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹ለፕሬስ ነፃነት የምናደርገው ትግል ለጋዜጠኞች መብት ስንል የምናደርገው ሳይሆን ለራሳችን መብት ስንል የምናደርገው ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት የራሳችንም ነፃነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፕሬስ ነፃነት ያላቸውን አቋም በተገለጸው መንገድ ሲያስቀምጡም፣ በውስጣቸው ግን ሥጋት እንዳለ ካደረጉት ንግግር መገንዘብ ይቻላል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ከመደበኛዎቹ ሦስት የመንግሥት መዋቅሮች ውጪ ሆኖ እንደ አራተኛ ገለልተኛ መንግሥት ይቆጠራል፡፡ ይኼንን በንግግራቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹›አራተኛው መንግሥት ቢሆንም ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም መንግሥት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን ያሉበት ምክንያት ሲያብራሩም፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ነው፡ እንደ እሳቸው አባባል በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ አገርንና ማኅበረሰቦቿን ለማገዝና ለማሸጋገር የሚያስችል የሚዲያ ከባቢና በኃላፊነት ሙያውን የሚወጣ የሚዲያ ባለሙያ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

‹‹ከግጭት ቀስቃሽነት፣ ከጠብ አጫሪነት፣ ከአሉታ አነፍናፊነትና ከስሜታዊነት የወጣ ፕሬስ ያስፈልገናል፡፡ ሙያዊ ብቃቱን የጠበቀ፣ የሞራል ልዕልና ያለው፣ የሚሠራው ሥራና የሚያስከትለውን ውጤት ቀድሞ ለመገመት የሚችል ፕሬስ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የሪፎርሙ ሥጋቶች

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ሚዲያ አሲስታንስ (CIMA) የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ዘርፍ አቅም ግንባታ ድርጅት፣ በአዲስ አበባ በተከበረው የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ቀን ከተሳተፉ ስመጥር ተቋማት አንዱ ነው፡፡

ይህ ተቋም የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ክብረ በዓልን የዘከረው፣ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም ለማገዝ በማቀድ ለመጀመርያ ጊዜ ባካሄደው ውይይት ነው፡፡

በዚህ ውይይት ላይ በኢትዮጵያ የሚዲያ ሪፎርም ክንዋኔዎች መካከል መገናኛ ብዙኃንን የተመለከቱ ሕጎችን ለማሻሻል ኃላፊነት የወሰዱ ምሁራን፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተመረጡ አዘጋጆች፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ተቋማት ተወካዮችና እንደ ኢትዮጵያ በፈታኝ የፖለቲካ አፈና ውስጥ አልፈው የሚዲያ ዘርፋቸውን በራሳቸው መንገድ ከገነቡ የአፍሪካ አገሮች የተወከሉ ጋዜጠኞች ተሳታፊ ነበሩ፡፡   

ጋና ያለፈችበትን የሚዲያ ጭቆናና በኋላ የመጣውን የሚዲያ ነፃነት በተመለከተ፣ በጋና የሚዲያ ጭቆና ዘመን 15 ዓመታትን በስደት በማሳለፉ ገፈቱን የቀመሱት ናና ካዋሲ የአገራቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡

በጋና የሚዲያ ሪፎርም እስከመጣበት እ.ኤ.አ. 1992 ድረስ አንድም የግል የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ እንዳልነበር ያስታወሱት የሚዲያ ባለሙያው፣ በወቅቱ የነበረው የአገሪቱ መንግሥት የነበሩትን የመገናኛ ብዙኃን በሙሉ በባለቤትነት ከመያዙም በላይ በእነዚህ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡትን ዜናዎች የመወሰንና ከመንግሥት የፖለቲካ ፍላጎት የሚቃረኑ የሕዝብ ድምፅ ውድቅ ያደርጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይኼንን የተላለፉ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ኃላፊዎች ይታሰሩ እንደነበር፣ እሳቸውን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች ከአገራቸው ተሰደው ለበርካታ ዓመታት መሰቃየታቸውንም ተርከዋል፡፡

ይኼንን ሁኔታ ለመቀየርም ተፅዕኖ ፈጣሪ ጋዜጠኞች ተሰባስበው የሚዲያ ነፃነትንና ዴሞክራሲን በጋና ለመትከል ከሚፈልጉ የፖለቲካ ልሂቃንና የሲቪክ ተቋማት ጋር ጥምረት መፍጠራቸውን፣ በዚህ ጥምረት አማካይነትም በጋና ሊፈጠር የሚገባውን የሚዲያ ነፃነት በተመለከተ በሚያስማሟቸው መሠረታዊ መርሆዎች ላይ አንድነት ፈጥረው እንደተንቀሳቀሱ ይገልጻሉ፡፡

ከእነዚህም መሠረታዊ መርሆዎች መካከል የሚዲያ ነፃነት፣ ለሁሉም እኩል የሆነ መረጃ የማግኘት መብትና የግል ሚዲያ ባለቤትነት እንዲረጋገጥ ስምምነት መደረጉን፣ በዚህ ውስጥ ደግሞ የሚፈለገው ለውጥ ፅኑ እንዲሆን ፕሮፌሽናሊዝም (የሙያ ብቃት) የሚፈለገው ለውጥ አስኳል እንዲሆን መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ይህ የለውጥ እንቅስቃሴ ውጤት አምጥቶ በሥራ ላይ በሚገኘው የጋና ሕገ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1992 ሲደነገግ ከመጡ ለውጦች መካከልም፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ለመመሥረት የሚዲያ ፈቃድ ማውጣት እንዲቀር መደረጉንና ማንኛውም ግለሰብ (አቅሙ ያለው) የንግድ ፈቃድ ብቻ ማውጣት እንደሚጠበቅበት፣ የሚዲያ ተቋሙን የጋና ብሔራዊ የሚዲያ ኮሚሽን ተብሎ በወቅቱ ለተቋቋመውና የሚዲያ ዘርፍ ባለድርሻዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲቆጣጠሩ ላቋቋሙት ኮሚሽን ማስመዝገብ ብቻ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ውስጥ በአባልነት የሚወከሉት 18 አባላት እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል አብላጫውን የሲቪክ ማኅበራትን በመወከል ራስን በራስ የመቆጣጠር ተግባሩ በገለልተኛነት እንዲመራ ተደርጎ መቀረፁን ገልጸዋል፡፡

ይህ በመሆኑም ጋና በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም የአፍሪካ አገር የተሻለ የሚዲያ ነፃነት እንደሰፈነባት ይገልጻሉ፡፡

ኮሚሽኑ በጋና ያሉትን የመገናኛ ብዙኃን ከመቆጣጠርና ከማረም ባለፈ፣ በመንግሥት ይዞታ ሥር ለሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አመራሮች የሚሾሙት በመንግሥት ሳይሆን በኮሚሽኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ በመሆኑም የመንግሥት ነው የምንለው ሚዲያ የለም፤›› ያሉት ባለሙያው፣ ወደዚህ ለውጥ ለመድረስ ካስቻሉት ምክንያቶች መካከል ለውጡ የተመራውም የተጠነሰሰውም በራሳቸው በባለሙያዎቹና በየትኛውም ዴሞክራሲ ውስጥ የሚዲያ ነፃነት ድጋፍ በሆኑት ሲቪክ ማኅበራት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም ሕጎችን በማሻሻል ረገድ የተደረሰበትን ደረጃ የሕግ ማሻሻያ ቡድን አባላት ተወካዮች አብራርተዋል፡፡

በእስካሁኑ ሒደትም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጉ፣ የኮምፒዩተር ወንጀል ሕጉና የብሮድካስት አዋጁ ያስከተሏቸው ችግሮችና ማነቆዎች፣ እንዲሁም ችግሮቹ የሚፈቱበትን መንገድ የዳሰሳ ጥልቅ ጥናት ተካሂዶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዶበት የሕግ ረቂቶቹን ማዘጋጀት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የረቂቆቹን መጠናቀቅ ተከትሎ የባለድርሻ አካላት ውይይት እንደሚካሄድና ግፋ ቢል በ2012 ዓ.ም. መጀመርያ ላይ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተብራርቷል፡፡ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም በከፍተኛ ደረጃ ያግዛሉ ተብለው ከሚጠበቁት ደጋፊ ዘውጎች መካከል፣ አፋኝ የነበረው የሲቪክ ማኅበራት ማቋቋሚያ አዋጅ ተሻሽሎ መፅደቁ በበጎነት ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የሚዲያ ባለሙያዎች በሪፎርሙ ለመሳተፍ የሚያሳዩት የባለቤትነት ስሜት ቀዝቃዛ መሆኑ፣ የሚዲያው ዘርፍ ራሱን በራሱ ለመቆጣጠር በማሰብ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትን ለማቋቋም ጥረት ቢደረግም ተመዝግቦ ሕጋዊ ዕውቅና አለማግኘቱ፣ በሚዲያ ዘርፍ ከፍተኛ የአቅም ውስንነት መኖሩና የዘርፉ ተዋናይ ጋዜጠኞች በአንድነት ተቀራርበውና ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበርና ግዴታቸውንም ለመወጣት ከመሞከር ይልቅ በመገፋፋትና በመጠራጠር ውስጥ መሆናቸው፣ በተለይም በፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው ዙሪያ ተሠልፈው እርስ በርስ የሚጓተቱ መሆናቸው የተጀመረውን የሚዲያ ሪፎርም በሚፈለገው መንገድ እንዳይጓዝ፣ ወይም በመንግሥት የአድራጊ ፈጣሪነት የበላይነት ውስጥ ወድቆ የሚፈለገው ነፃነት እንዳይሟላ ሥጋት መደቀኑን ተወያዮች ተስማምተውበታል፡፡

መቀመጫውን አሜሪካ አድርጎ የተመሠረተው ‹‹መርሳ ሚዲያ ኢንስቲትዩት›› የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርምር ተቋም መሥራችና የቀድሞ የአሜሪካ ድምፅ ባልደረባ የነበረው አቶ ሔኖክ ሰማእግዜር ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‹‹Developing Independent Media Association In Ethiopia›› በሚል ርዕስ ያሳተመው ጥናትም፣ የኢትዮጵያ የሚዲያ ባለሙያዎች ተበታትነውና ተራርቀው እንደሚገኙና በሚያግቧቧቸው መሠረታዊያን ላይ እንኳን ተቀራርበው ለመሥራት የተቸገሩ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡

በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎች ማኅበራት ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ተመሥርተው የነበረ ቢሆንም፣ አንዳቸውም ተልዕኳቸውን ሳይወጡ አንድም በመንግሥት ጫና አንድም በመሥራቾቹና በባለሙያዎቹ መካከል ባለ ጥርጣሬ ተልዕኳቸውን አለመወጣታቸውን በመግለጽ፣ የሚዲያ ሪፎርሙ ሙሉ እንዲሆን ከተፈለገ የነበረውን ልማድ ቀርፎ የሚዲያ ባለሙያዎች ተቀራርበው በመወያየት ጠንካራ ማኅበር ሊመሠርቱ እንደሚገባ በጥናቱ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -