Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸው እንዲከበር ፍርድ...

በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የደኅንነት ሠራተኞች ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸው እንዲከበር ፍርድ ቤት አሳሰበ

ቀን:

ፌዴራል ፖሊስ ለእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መጥሪያ እንዲያደርስ ትዕዛዝ ተሰጠ

በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሽ የደኅንነት ሠራተኞች የእምነት ክህደት ቃል ሰጡ

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ላለፉት ሰባት ወራት በምርመራ ላይ የቆዩትና ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የተካተቱና የደኅንነት ሠራተኞች የነበሩ 22 ተከሳሾች (በእስር ላይ የሚገኙ) ጥፋተኛ መሆናቸው በፍርድ ቤት እስከሚረጋገጥ ድረስ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ንፁህ ሆነው የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት ፍርድ ቤት አሳሰበ፡፡

- Advertisement -

ማሳሰቢያውን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. የተከፈተውን ክስ ለሦስት ቀናት ማለትም እስከ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በንባብ ያሰማውን በ96 ገጽ የተዘጋጁትን 46 ክሶች በንባብ አሰምቶ እንዳጠናቀቀ፣ ከተከሳሾች በቀረበ አቤቱታ ምክንያት ነው፡፡

ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ እነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ተብለው በእስር ላይ እያሉ፣ በቤተሰቦቻቸውና በልጆቻቸው ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው ብለዋል፡፡ ይኼም የሆነው እነሱ ተጠርጥረው በእስር ላይ ባሉበት ሁኔታ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በማስረጃ ተጣርቶ ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸው ሳይረጋገጥ፣ በእነሱ ደመወዝ የሚተዳደሩ ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸው እንዳይከፈላቸው (ደመወዝ በውክልና እንዳይወስዱ) መከልከላቸውን ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን አቤቱታ ካዳመጠ በኋላ እንደገለጸው፣ ተከሳሾቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ እንደ ማንኛውም ሰው ንፁህ ሆነው የመገመት መብት አላቸው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊት በእነሱም ላይ ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ሊደርስ እንደማይገባም አስታውቋል፡፡

ተከሳሾቹ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቤቱታም በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በመንገር፣ የቀረበባቸው ክስ ግልጽ መሆን አለመሆኑን ጠይቋቸዋል፡፡ ተከሳሾቹም ክሱ ግልጽ እንደሆነ ከገለጹ በኋላ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ውስጥ 17 ሲዲዎች  እንዳሉ መግለጹን ፍርድ ቤቱ አስታውሶ፣ ለምን ከእሱ ጋር አያይዞ እንዳላቀረበ ጠይቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ ሲዲዎቹ በችሎት የሚታዩ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ እንደሚያቀርብ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም በመቀጠል፣ ‹‹በየትኛው ሕግ ነው የሲዲ ማስረጃ እናንተ ዘንድ የሚቀመጠው?›› በማለት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ስለምስክሮች ደኅንነት ጥበቃ ስለሚደነግግ የ29 ምስክሮችን ስም ዝርዝር አለማያያዝ የሕግ መሠረት እንዳለው በመጠቆም፣ ሲዲዎቹን ግን ለሁሉም ተከሳሾች እንዲደርሱዋቸው እንዲያደርግ ትዕዛዝ በመስጠት ‹‹ሬጂስትራር አይቀበለንም›› የሚለውን የዓቃቤ ሕግ ምላሽ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ማቅረብ አለማቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ከመጠየቁ በፊት፣ በራሳቸው ጠበቃ ማቆም መቻል አለመቻላቸውን ጠይቋቸው፣ ከአራት ተከሳሾች በስተቀር ሁሉም በራሳቸው ጠበቃ ማቆም እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጥያቄ ያቀረቡት አራት ተከሳሾች ምንም ዓይነት ሀብትም ሆነ መተዳደሪያ ንብረት እንደሌላቸው በቃለ መሃላ ከማረጋገጣቸው በፊት፣ አቶ ዮሴፍ ኪሮስና አቶ ክፍላይ መሀሪ የተባሉ ጠበቆች ለሌሎች ተከሳሾች የቆሙ ቢሆኑም፣ እስከ መጨረሻው እንደሚቆሙላቸው ለፍርድ ቤቱ አሳውቀው ሐዲቱ ቀጥሏል፡፡ ጠበቆች በዓመት 50 ሰዓታት ነፃ አገልግሎት የመስጠት ሕጋዊ ግዴታ እንዳለባቸው ፍርድ ቤቱ አስታውሶ፣ የእነዚህ ጠበቆች አገልግሎትም በዚያ እንዲያዝላቸው ትዕዛዝ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቀጠልም በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንዳላቸውና እንደሌላቸው ሲጠይቃቸው፣ ከአንድ ተከሳሽ በስተቀር ሁሉም ተከሳሾች ‹‹የክስ መቃወሚያ የለንም›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ሰይፈ በላይ የተባሉ ተጠርጣሪ ግን የክስ መቃወሚያ እንዳላቸውና በዕለቱ በችሎት ካልተገኙት ጠበቃቸው ጋር ተነጋግረው እንደሚያቀርቡ አሳውቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ከአቶ ሰይፈ በስተቀር ሌሎቹ የእምነት ክህደት ቃላቸቸውን እንዲሰጡ ሲጠይቃቸው የተወሰኑ ተከሳሾች፣ ‹‹ክሱ የፈጠራ ነው፣ ድርሰት ነው፣ በመሆኑም ድርጊቱን አልፈጸምንም፣ ጥፋተኛም አይደለንም፤› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በመሀል አስቁሞ፣ ‹‹ችሎቱ ነፃና ገለልተኛ ነው፡፡ ለሁላችሁም ለግራ (ተከሳሾች) ለቀኝ (ዓቃቤ ሕግ) እና ለሁሉም ተከሳሽ የሚሰጠው ዳኝነት እኩል ነው፡፡ የማንንም ጣልቃ ገብነት አናስተናግድም፡፡ የተመሠረተውን ክስ በሚቀርበው ማስረጃና ምስክር በሕግ አግባብ መርምረን ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘን ጥፋተኛ እንላለን፡፡ ነፃ የሆነውንም ነፃ እንላለን፡፡ ከዚህ ውጪ አላስፈላጊ ንግግርና መልስ መስጠት እንደ ዳኛም ሆነ እንደ ችሎት ምንም የምናደርገው ነገር የለም፤›› በማለት ተከሳሾቹ በክሱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ክርክራቸውን በነፃነት እንዲቀጥሉ አሳስቦ፣ የእምነት ክህደት ቃል አሰጣጥ ቀጥሏል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች በተመሳሳይ ሁኔታ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምንም፣ ጥፋተኛም አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡ ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ፣ ጠበቆቻቸው ከመብት ጥያቄ ጋር የተያያዘ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

የደንበኞቻቸውን የዋስትና መብት በሚመለከት ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዋስትና መርህ ነው፡፡ የሚከለከለውም በልዩ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ይኼም ቢሆን መተርጎም ያለበት ለተከሳሹ በሚያግዝና በጠባቡ መሆን እንዳለበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበትም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በሁኔታ ዋስትና ሲያስከለክል የሚችል ነገር እንደሌለ፣ በሕግም ሊያስከለክላቸው የሚችል ነገር እንዳልቀረበባቸውና እንደሌለ፣ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881 እንደማያስከለክሏቸው ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የጠቀሳቸው ተደራራቢ የሕግ ድንጋጌዎችም ግልጽነት እንደሚጎድላቸው፣ ሁለት የሕግ ድንጋጌዎች ‹‹እና›› በሚል ቃል አያይዞ ማቅረብ አሻሚ  ስለሚሆን አንዱ መመረጥ እንዳለበትም አክለዋል፡፡ የቀረበባቸው ክስም የክስ አቀራረብ መርህን የተከተለ እንዳልሆነ፣ ሁለት ሁለት ክሶችን በአንድ ተከሳሽ ላይ በማቅረብ ተከሳሹን የዋስትና መብት ለማስነፈግ ታስቦ የቀረበ ክስ እንጂ፣ የክስ አቀራረብ መርህን የተከተለ አለመሆኑን በመደጋገም ተቃውመዋል፡፡

ክሱ ከባድ የሙስና ወንጀል መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ቢገልጽም፣ ሙስና ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ፍርድ ቤቱ በሒደት መርምሮ የሚደርስበት ይሆናል ያሉት ጠበቆቹ፣ ክሱ ሆን ተብሎ ዋስትናን ለማስከልክል ታስቦ የተመሠረተ እንጂ ትክክለኛ ክስ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ሙስና የተባለው ከአሥር ዓመታት በላይ ስለሚያስቀጣ ዋስትና ለማስከልከል እንጂ፣ ምንም የሙስና ድርጊት በክሱ ውስጥ አለመጠቆሙን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የክሱን ይዘት በደንብ ሊመረምረው ይገባል ብለዋል፡፡

ዋስትና ለማስከልከል ተገቢ ያልሆነ ሕግ መጥቀስ ተገቢ እንዳልሆነ፣ ዓቃቤ ሕግ ዓላማ ይዞ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብት ሊያስነፍግ እንደማይችልም አክለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተከሳሾች ጠበቆች ባቀረቡት የመብት ጥያቄና የክስ መቃወሚያ ላይ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብት መሆኑን በማረጋገጥ ምላሽ የሰጠው ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው፣ ዋስትና መብት የመሆኑን ያህል በሁኔታዎችም ሊገደብ ይችላል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለተከሳሾች ዋስትና መፈቀድ የለበትም የሚለው በሕግ አግባብ እንደሆነ፣ የተጠቀሱት ሕጎች ከአሥር ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል የወንጀል ድርጊት ከመሆናቸውም በላይ፣ ወንጀሎች ተደምረው የሚያስቀምጡት ከአሥር ዓመታት በላይ መሆኑን ከተረጋገጠ ዋስትና በሕግ መከልከሉን አብራርቷል፡፡

የተከሳሾች ጠበቆች ያቀረቧቸው መቃወሚያዎች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 ድንጋጌ መሠረት የሚቀርቡ ቢሆኑም፣ የክስ መቃወሚያ እንደሌላቸው በመግለጻቸው ብይን የተሰጠበትና የታለፈ መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የዋስትና ጥያቄ በክሱ ላይ የተጠቀሱና በሕግ ድንጋጌ የተከለከሉ በመሆናቸው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾች ከነበሩበት ቦታና ከነበራቸው ሥልጣን አንፃር በዋስ ቢወጡ መረጃ ሊደብቁ፣ ምስክር ሊያባብሉና ሊያስፈራሩ ስለሚችሉ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 (ሀ፣ ለ እና ሐ) ድንጋጌ መሠረት የዋስትናው ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግ በድጋሚ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112 ድንጋጌ መሠረት የክስ መቃወሚያ ባልቀረበበትና ፍርድ ቤቱም ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ ባልሰጠበት ሁኔታ፣ ዋስትና እንዲፈቀድ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130 ድንጋጌ መሠረት መቃወሚያ የሚቀርብበት እንጂ ዝም ተብሎ ‹‹ሙስና አይደለም›› ተብሎ መቃወሚያ የሚቀርብበት አለመሆኑንም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾች በዋስ ቢወጡ ያላቸውን ሥልጣን ተጠቅመው ማስረጃ ሊያጠፉ፣ ምስክሮች ሊያባብሉና ሊያስፈራሩ ይችላሉ በሚል ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው መቃወሚያ ላይ ጠበቆች ምላሽ እንዲሰጡ ፈቅዶላቸዋል፡፡ ጠበቆቹ እንደገለጹት፣ ደንበኞቻቸው የተያዙት በሥራ ላይ እንዳሉ ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ ተብለው ነው፡፡ ስብሰባ በተባሉበት ቦታ ሲደርሱ ያጠፉት ነገር ሳይነገራቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተናገሩት ቃል ታልፎ ወደ እስር ቤት መወርወራቸውን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥልጣናቸው መወሰዱን፣ ኃይልም፣ ሥልጣንም እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ተከሳሾቹ ምስክሮቹ እነማን እንደሆኑ እንደማያውቋቸው፣ ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ለሁለት ወራት በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክሮች ቃላቸውን የሰጡት በመጋረጃ ተደብቀውና ሌላ ክፍል ውስጥ ሆነው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ስማቸውም የሚጠራው በኮድ (ሚስጥር) እንደነበርም አክለዋል፡፡

ምስክሮቹን የሚያውቋቸው ‹‹ፈጣሪና ዓቃቤ ሕግ ብቻ ናቸው ያሉት ጠበቆቹ፣ በዋስ ወጥተው በመንገድ ላይ ቢያገኟቸው እንኳን ሊያውቋቸው የሚችሉበት ምንም ዓይነት ሁኔታ ስለማይኖር፣ ዓቃቤ ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 ጠቅሶ ዋስትና እንዲከለከሉ ያቀረበው መቃወሚያ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ቢሆን እንኳን ዓቃቤ ሕግ ዝም ብሎ ለማለት ያህል ካልሆነ በስተቀር፣ አንዳንዶቹ ምስክሮች በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው የተናገሩ መሆናቸውን ጠቁመው ምንም የሚያስፈራቸው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

ተከሳሾቹ ብዙ በደል የደረሰባቸው መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ለሁለት ወራት የተሰጠው የምስክርነት ቃል ተገልብጦ እስከሚያልቅ ለሁለት ወራት ያለ ምንም ሕጋዊ ምክንያት ታስረው መቆየታቸውንም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡  

ተከሳሾቹ ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ መቆየታቸውን ማለትም ሦስት ወራት በፖሊስ ምርመራ፣ ሁለት ወራት በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ምስክሮች ሲሰሙና ሁለት ወራት ያለ ምንም ምክንያት ታስረው በመቆየታቸው፣ አካላቸውን ነፃ ለማውጣት የፍትሐ ብሔር አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአቤቱታው ላይ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ትዕዛዝ ሊሰጥ ቀጥሯቸው እያለ ዓቃቤ ሕግ ተሯሩጦ በተመሳሳይ ቀን ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ክስ መመሥረቱን ጠቁመው፣ የፍትሐ ብሔሩን ጉዳይ የመረመረው ችሎት በሦስት ቀናት ውስጥ መፍትሔ ካልተሰጠ ከእስር ሊፈታቸው እንደሚችል ትዕዛዝ መስጠቱን መስማታቸውንም በችሎት ተናግረዋል፡፡

ጠበቆች አቤቱታቸውን እንደ ጨረሱ ዓቃቤ ሕግ በአንዳንድ አቤቱታዎች ላይ ምላሽ ለመስጠት ጠይቆ፣ ስለክሱ አቀራረብ ለማስረዳት ሲሞክር ፍርድ ቤቱ አስቁሞታል፡፡ ‹‹ይኼ ችሎት ነው፡፡ የሚመራው በሕግና ሕግ ብቻ ነው፡፡ ይኼ ሽምግልና አይደለም፡፡ ክሱ ተጠንቶም ይቅረብ ወይም አካልን ነፃ ለማውጣት የቀረበውን አቤቱታ ለማክሸፍ ክስ ሆኖ ቀርቧል፤›› በማለት የዓቃቤ ሕግ ድጋሚ የማስረዳት ጥያቄን ውድቅ አድርጎታል፡፡ በመቀጠልም ተከሳሾች ድርጊቱን አለመፈጸማቸውንና ጥፋተኛ አለመሆናቸውን በመግለጻቸው ዓቃቤ ሕግ የሚያመለክተው ካለው ተጠይቆ፣ የቀረበባቸውን ክስ ክደው የተከራከሩ ስለሆነ፣ እንደ ክሱ የሚያስረዱለትን ምስክሮች አቅርቦ ለማሰማት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ዓቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡

ክርክሩ በመጠናቅ ላይ እያለ አንድ ተከሳሽ ሁሉንም ተከሳሾች በመወከል እየደረሰባቸው ስላለው አስተዳደራዊ በደል እንዲያስረዱ ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ተከሳሹ እንዳብራሩት፣ ከተያዙ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ስድስተኛ ወራቸውን ጨርሰው ሰባተኛ ወራቸው ገብቷል፡፡ አያያዛቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ የተጠርጣሪዎችን አያያዝ በሚመለከት የተናገሩትን መርህ የጣሰ ነው፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስብሰባ ተብለው መያዛቸውንና የተጠረጠሩበት ወንጀል የሌለ መሆኑን ጠቁመው፣ አንዳንዶቹ በስድስት ወራት ውስጥ መርማሪ ፊት የቀረቡት አንድ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አካልን ነፃ ለማውጣት ያቀረቡት አቤቱታ ለማደናቀፍ የተመሠረተ ክስ መሆኑን ጠቁመው አሳዛኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አገራቸውን ሲያገለግሉና ከብዙ አደጋና ችግር ሲታደጉ ቆይተው መጨረሻቸው እስር መሆኑ አሳዛኝ እንደሆነ ጠቁመው፣ ከፍተኛ የአገር ክህደት የፈጸሙና አገሪቱን በፈንጂና በተለያየ ነገሮች ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች አሁን ሹመት ተሰጥቷቸው እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰዎቹ መሾማቸውና ለአገር መሥራታቸውን ባይቃወሙም፣ እነሱም ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ባላቸው ዕውቀት ሲያገለግሉ ከመኖራቸው ውጪ ምንም ያጠፉት ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡ ከተያዙ ጀምሮ ደመወዛቸው በመቋረጡ ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸው ገልጸው፣ ‹‹እኛስ እሺ ልጆቻችን ምን አደረጉ? ከዚህ በላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ?›› በማለትም ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹እናንተ ንፁህ ናችሁ ብለን ነው የምንገምተው፡፡ በማስረጃ ነፃ ወይም ጥፋተኛ እስከምትባሉ በዚህ ደረጃ አስቡት፤›› በማለት የጥቅማ ጥቅምና የቤተሰብን ጉዳይ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በመንገር ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ ጌታቸው አሰፋን፣ አቶ አጽበሃ ግደይን፣ አቶ አሰፋ በላይንና አቶ ሻሸይ ልዑልን የፌዴራል ፖሊስ በመጥሪያ እንዲያቀርብ፣ እንዲሁም ዓቃቤ ሕግና ተከሳሾች ባደረጉት ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ክሱን እንደሚቃወሙ የገለጹት አቶ ሰይፈ በላይም የክስ መቃወሚያቸውን በዕለቱ እንዲያቀርቡ፣ ወይም ሐሳባቸውን ቀይረው የማይቃወሙ ከሆነ የእምነት ቃላቸውን ለመቀበል በተመሳሳይ ቀን ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...