Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 26 የደኅንነት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ክስ ተመሠረተባቸው

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 26 የደኅንነት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ 26 የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማክሰኞ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ 10፡00 ሰዓት አካባቢ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበባቸው ክሶች 46 ሲሆኑ፣ በሌሉበት ክስ በተመሠረተባቸው አቶ ጌታቸው ላይ ሁለት ክሶችን በብቸኝነት አቅርቦባቸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአቶ ጌታቸው ላይ ያቀረበው የመጀመርያ ክስ እንደሚያብራራው፣ አቶ ጌታቸው ከ1994 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ በቀድሞ የደኅንነት፣ ኢሚግሬሽንና ስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ ነበር፡፡ ዳይሬክተሩ በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን ወደ ጎን በመተው በሰዎች መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ከሕግ ውጪ ሰውን የመያዝ፣ አስሮ የመመርመርና እስር ቤቶችን የማዘጋጀት ሥልጣን ሳይኖራቸው፣ ሰዎችን በኃይልና በማስገደድ እንዲያዙ እንዲታሰሩ፣ መረጃ እንዲሰጡና ወኪል በመሆን መረጃ እንዲያቀርብሏቸው ያደርጉ እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡ ይኼንንም የሚያደርጉት በሥራቸው በሚመሯቸው የተቋሙ ሠራተኞች አማካይነት ታስረው እየተመረመሩ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት በተቋሙ ውስጥ በማዘጋጀት፣ በበላይነት ይመሩ እንደነበር አክሏል፡፡ የሚታሰሩ ሰዎች የሚቆዩባቸው ድብቅ እስር ቤቶች በጦር ኃይሎች አካባቢ፣ በጉለሌ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ምናዬ ሕንፃ አካባቢ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቄራ ቡልጋሪያ ማዞሪያና ቄራ መስጊድ አካባቢ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ካርል አደባባይ አካባቢ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጦር ኃይሎች አካባቢና በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ድልድይ አካባቢ ከመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶች በመውሰድ በድብቅ እንዲዘጋጁ አደርገው እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ለሚታሰሩ ሰዎች ሕክምና የሚሰጥ፣ ምግብ የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸትና እስር ቤቶቹን የሚያስተዳደር ሰው መድበውም እንደነበር ጠቁሟል፡፡

በአገሪቱ በሚገኙ ከተሞች በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በነቀምቴ፣ በጅማ፣ በሻሸመኔ፣ በቢሾፍቱና በሐዋሳ ከተሞች ሰዎች እየተያዙ ይታሰሩ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ በክሱ አክሏል፡፡

አቶ ጌታቸው በወቅቱ በአሸባሪነት ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ኦነግ፣ አርበኞች ግንቦት ሰባትና ከሃይማኖት አክራሪነት ጋር በተያያዘና በኢኮኖሚ ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው ክትትል የሚረግባቸው ሰዎች እንዲያዙ፣ በኃይል ታፍነው እንዲታሰሩ፣ የሚታሰሩበትን ቦታ እንዳያውቁ ዓይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን ከላይ ወደ ተጠቀሱት ሥውር እስር ቤቶች፣ በማዕከላዊና በማረሚያ ቤት በመገኘት ታሳሪዎቹን በተለያየ መንገድ በማሰቃየት ምርመራ መረጃ እንዲቀበሉ ለበታች ሠራተኞች መመርያ ይሰጡ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በተለያዩ ድብቅ እስር ቤቶች በማሰቃየት የተመረመሩትን አብዛኞቹን ወደ ማዕከላዊ በመውሰድና ቀሪዎቹን ከታሰሩበት ቦታ በማውጣት፣ ዓይናቸውን በጨርቅ በመሸፈን ከታሰሩበት ቦታ አርቆ በመውሰድና መንገድ ላይም እንዲጣሉ ያደርጉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ በርካታ ሰዎችም እስከ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ጉዳት እንደ ደረሰባቸውም አክሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር በ2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲዮም በሚያደርገው ጨዋታ ላይ ቦምብ ለማፈንዳት አስበዋል በማለት፣ በርካታ ሰዎች ተይዘው ወደ ማዕከላዊ ተወስደው ምርመራ መደረጉን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አቶ ጌታቸው ምርመራው በደንብ አልተከናወነም በማለት ማጣራት ሲደረግባቸው ከነበሩት መካከል ሼክ ኡስማን መሐመድ፣ መሐመድ ኢብራሂም፣ መሐመድ ሲዶ፣ መሐመድ ዓሊና ሌላ ያልታወቀ ግለሰብ ከታሰሩበት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲወጡና ቄራ መስጊድ ጀርባ በሚገኘው ድብቅ እስር ቤት ተወስደው እንዲታሰሩ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጿል፡፡ ምርመራው ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ደኅንነቶች በጥብቅ በድጋሚ እንዲደረግ አቶ ተስፋዬ ገብረ ፃዲቅ የተባሉት ተከሳሽ ለአቶ ያሬድ ዘሪሁን (የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩ)፣ አቶ ያሬድ ደግሞ ለአቶ ጌታቸው በማቅረብና በመገምገም ተጨማሪ የምርመራ አቅጣጫ በመስጠት ምርመራውን ለረዥም ጊዜ በማድረግ ሲያሰቃዩ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

በዚህም ምርመራ መሐመድ ኢብራሂም የተባለው ተመርማሪ ለረዥም ጊዜ ቆሞ ድብደባና ምርመራ ሲካሄድበት ተዝለፍልፎ በመውደቅ ሕይወቱ ማለፉን ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ አቶ ጌታቸው በተበዳዮቹ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸምባቸው በማድረጋቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆናቸውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገልላቸው ከባድ የወንጀል ክስ እንዳቀረበባቸው ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ይኼንንም ወንጀል የፈጸሙት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)፣ 407 (1ለ እና ሐ) እና 407 (3) ድንጋጌንና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ለ እና ሐ) እና 9(3) የተደነገገውን ተላልፈው መሆኑን ጠቁሟል፡፡

አቶ ያሬድ ዘሪሁንና አቶ መአሾ ኪዳኔ የተባሉ ሦስተኛና አራተኛ ተከሳሾችም፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ) እና 407 (1) (ለ እና ሐ) እና 407 (2) ድንጋጌን በመተላለፍ ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዘርዝሮ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ተከሳሾች ከአቶ ጌታቸው ጋር በመሆን ከላይ እንደተገለጸው በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ደረሰውን ድብደባና ሕገወጥ ምርመራ እንደዲረግ ትዕዛዝ በመስጠትና በመሳተፍ፣ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በስፋት ዘርዝሯል፡፡

አቶ ያሬድና አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወር ገንዘብ የመያዝም ሆነ በተቋሙ እንዲወረስ የማድረግ ሥልጣን ሳይኖራቸው፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም በሕግ አግባብ ከተቀመጠው ውጪ በመጠቀም ዜጎች በኃይልና በግዳጅ ተይዘው መረጃ እንዲሰጡ ያደርጉ እንደበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ወኪል በመሆንም ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ ገንዘብ እንዲልኩ በማድረግና በመቀበል ለግል ጥቅማቸው ያውሉ እንደነበርም አክሏል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. በአሸባሪነት ከተፈረጀው ኦነግ ጋር ግንኙነት አላችሁ በማለት የተለያዩ ግለሰቦችን በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረዋል በማለት በኃይል አስገድደው አፍነው በመያዝ፣ በሕገወጥ መንገድ ባዘጋጁት እስር ቤት ውስጥ በድብቅ ለረዥም ጊዜ አስሮ በማቆየት አስገድደው በመመርመርና የተጠርጣሪዎቹ ወኪል በመሆን መረጃ እንዲያቀብሏቸውና ከአገር ውጭ ከሚገኙ የኦነግ አመራሮችና አባላት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ በአገር ውስጥ ባሉ የኦነግ አባላት የተለያዩ የትግል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ያሉ በማስመሰል የተለያዩ ድርጊቶች በቪዲዮ እንዲቀረፁ ያደርጉ እንደነበር ክሱ ጠቁማል፡፡

ድርጊቱ እውነት እንዲመስል ከኦነግ ጋር የተገናኙ ጽሑፎች በራሪ ወረቀቶች፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩና አምቦ ከተሞች በመስቀልና በመለጠፍ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በመሥሪያ ቤቶችና በሌሎች ቦታዎችም በመስቀልና በመለጠፍ ቪዲዮ አንስተው፣ በውጭ ለሚገኙ የኦነግ አመራሮችና አባላት በመላክ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በሕገወጥ ሐዋላ ወደ አገር ውስጥ እንዲላክ በማድረግ፣ አቶ ተስፋዬ ለተቋሙ ሠራተኞች ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት በአጠቃላይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ መቀበላቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች በየደረጃው ከበላይ ኃላፊዎች በመቀበል፣ አግባብ ያልሆነ ድርጊት በመፈጸም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆንና ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በችሎት የተገኙትን የሁለተኛ፣ የሦስተኛ፣ የአራተኛና አምስተኛ ተከሳሾች ክስ አንብቦ ቀሪውን በንባብ ለማሰማት ለረቡዕ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌሉት ተከሳሾ ላይ (አቶ ጌታቸውን ጨምሮ አራት ናቸው) የዓቃቤ ሕግን ምላሽ ሰምቶ ብይን ለመስጠት በአዳር ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...