ተገልጋዮች በእጅጉ ከሚማረሩባቸውና ‹‹የመፍትሔ ያለህ›› በማለት ከሚጮሁባቸው ጉዳዮች አንዱ የግል የትምህርት ተቋማት ጉዳይ ነው፡፡ አንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ክፍያ ከጊዜ ወዲህ አልቀመስ ብሏል የሚለው ድምፅ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ የወላጆችን እሮሮ እያባሰው ስለመምጣቱም በግልጽ ይታያል፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ተቋማት ድረስ ባለው አገልግሎታቸው ውስጥ የሚጠየቁት የክፍያ መጠን በየዓመቱ ሳያቋርጥ ሲጨምር መቆየቱ ግራ ያጋባል፡፡
እርግጥ ነው አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ተገቢውን ድጋፍ ከመንግሥት አያገኙም፡፡ በአዲስ አበባ ከ52 በመቶ ያላነሰውን የትምህርት ሽፋን የሚይዙት የግል ተቋማት ናቸው፡፡ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎችማ የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤቶች እንደሌሉና ይህንንም ኃላፊነት የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚወጡት ይታወቃል፡፡ አብዛኞቹ በኪራይ ሕንጻ እንደሚሠሩ እናውቃለን፡፡ ትምህርት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ እንደሚመደብ ቢነገርም፣ መሬትና መሰል አቅርቦቶች ለዘርፉ ባለሀብቶች እንደ ኢንቨስትመንት ማበረታቻ አይቀርብላቸውም፡፡ ግብዓት ሲያስመጡም በውድ ዋጋ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መንግሥት በርካሽ ዋጋ የሚያሳትመውን የመማሪያ መጽሐፍ በብዙ ዕጥፍ ይሸጥላቸዋል፡፡ በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችና ወላጆች የሌላ አገር ዜጎች እስከሚስሉ ድረስ በመንግሥት ቦታ አለማግኘታቸውም እየታየ ነው፡፡ የመንግሥት ሥራ በአብዛኛው በትምህርት መስክ የተሰማራውን ነጋዴና ወላጅን የማጋጨት አካሄድ የሚከተል እስኪመስል ድረስ በሁለቱ መካከል ሰፊ አለመግባባት እንዲሰፍን ምክንያት እየሆነ ነው፡፡
ይህ እንግዲህ ዋናው የችግሩ መነሻ ይሁንና፣ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎታቸው የሚጠየቁት የክፍያ መጠን ግን የተጋነነ ሆኖ ይገኛል፡፡ ለስሙ ወላጆች በወላጅና ተማሪ ኮሚቴ በኩል ስምምነት ያደረጉበት ጭማሪ ብቻ ተፈጻሚ ይደረጋል የሚል አሠራር ቢኖርም፣ ስንቱ ነው ይህንን በትክክል በወላጆች ተሳትፎና ስምምነት ጭማሪውን የሚያጸድቀው ብሎ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቢሆን ኑሮ አብዛኛው ወላጅ በየሚዲያው እሮሮውን ባላሰማ ነበር፡፡ መንግሥት የራሱን የቁጥጥርና የዕገዛ ሥራ ወደ ወላጆች በማንከባበለሉ ተጠያቂነት እንዲላላ ያደረገበት አሠራር እየታየ ነው፡፡
ይህ በመሆኑም ይመስላል፣ ወላጆች በየዓመቱ ተቋማቱ የሚያደርጉባቸውን የዋጋ ጭማሪ መቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ እየተቃረቡ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተቋማቱ ከሚሰጡት አገልግሎት በላይ በየዓመቱ የሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ ላይ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው የሚያሳብቅ ዕርምጃ ከወዲሁ እያየን ነው፡፡ ይኸውም በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወቅት ይጨመራል ያሉትን የዋጋ ተመን ከወዲሁ ወላጆችን እየጠሩ የሚያሳውቁ ትምህርት ቤቶች ተበራክተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የግል የትምርት ቤቶች፣ የዘንድሮ የትምህርት ወቀት ገና ሳይጠናቀቅና ተማሪዎችም ለመጪው ዓመት የሚያበቃቸውን ውጤት ሳያውቁት፣ በይሆናል ብቻ ለመጪው ዓመት የወርኃዊና የተርም ክፍያ ዋጋ ላይ ለመነጋገር በማለት ለወላጆች ጥሪ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ ተቋማቱ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ስለመወሰናቸው በመግለጽ ወላጆችን ጠርተው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ወላጆች ሐሳባቸውን ባለመቀበላቸው ሳቢያ በተፈጠረ አለመግባባት ስብሰባ የተበተነባቸው ትምህርት ቤቶችም አይተናል፡፡
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶችማ ወላጆችና የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ለጠብ እስከመተናነቅ የደረሱበት አጋጣሚ ተከስቷል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ውሳኔያቸው እንደማይቀየርና ወላጆች ምን ማምጣት እንደማይችሉ በመግለጽ ያሳዩት ተገቢነት የጎደለው አድራጎትም ታይቷል፡፡ ይህ የጉዳዩን አሳሳቢነት ፍንትው ያደርገዋል፡፡ ዋጋ በማናር ስም የወጣላቸው የግል የትምህርት ትምህርት ቤቶች ሳይታክቱ በየዓመቱ በጭማሪ መዝለቃቸው እየታየ፣ የኢትዮጵያ የትምህርት ክፍያ ዋጋ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ ከሚከፈለውም በላይ ስንት ልቆ እንደሚገኝ የሚያጣቅሱ መረጃዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ይሁንና ግን የግል ትምህርት ቤቶች ግን እጥፍና ከእጥፍ እያሻቀበ ለሚገኘው ጭማሪያቸው ትክክለኛነት መነሻና መሠረታዊ ምክንያት ማረጋገጫ የሚሰጥ አካል ጠፍቷል፡፡
ተቋማቱ በየዓመቱ ለሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ የሚጠቅሷቸው ምክንያቶች ወላጆችን ባይመለከቱም፣ ምን ተዳኸኝ ያሉ ይመስል የዓመት ሥራቸው አንዱ ዋጋ መጨመር ሆኗል፡፡ ሰሞኑን የዋጋ ጭማሪ ስለማድረጋቸው ካሳወቁ ትምህርት ቤቶች አንዳንዶቹ በአንድ ተርም (በአብዛኛው ሦስት ወራትና ከዚያ በታች) እስከ አንድ ሺሕ ብር ጭማሪ ሲያደርጊጉ፣ መካከለኛ የሚባሉት ትምህርት ቤቶችም በአንድ ተማሪ ከሁለት መቶ ብር በላይ ጭማሪ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ከየትኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ተለይተው እነዚህ ተቋማት ያለማቋረጥ በየዓመቱ ጭማሪ የሚያደርጉበት አካሄድ ማቆሚያና ማባሪያ የሌለው ‹‹ብዝበዛ›› ሊባል በሚባል ደረጃ እንደደረሰ የወላጅን እሮሮ መስማቱ በቂ ነው፡፡
ተቋማቱ የሚያደርጉት ጭማሪ ከወላጆች ገቢ አኳያ ግንዛቤ ውስጥ አያስገቡም፡፡ ‹‹ከቻልክ ክፈል፡፡ ካልቻልክ ወደምትሔድበት ልጅህን ይዘህ ሒድ›› የሚመስል አሠራር ይከተላሉ፡፡ የአገሪቱን ሁኔታም ያላገናዘበ ነው፡፡ ይህም ሆኖ እኮ የሚሰጡት ትምህርትና ጥራቱ ተማሪዎቻችንን ከመሠረቱ ቀይሮና ለውጦ አንቸው በሆነ ባልከፋን ነበር፡፡ ከእጅ አይሻል ዶማ በሆነ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ፣ የግሎቹ በመንግሥት ላይ መንግሥትም በእነሱ ላይ ጣት እየተቀሳሰሩ የጥራት ጉዳይ ጫማ ሥር በዋለበት አገር ውስጥ፣ ዋጋው ሰማይ መንካቱ ምን ዓይነት ሞራል ቢኖር ነው ዋጋው እንዲህ ከአቅም በላይ የናረው፡፡ ደመወዝ ይጨመር የሚለው የአብዛኛው ሠራተኛ ጥያቄ ምላሽ ባላገኘበትና ለትምህርት ድጎማ ባልተሰጠበት አገር ውስጥ መንግሥትም የትምህርት ተቋማቱም የዋጋ ጭማሪ ላይ ዝምታቸው መጽናቱ ‹‹ወላጅ እንደቻለ ይቻለው›› ነው ወይስ ምን ተፈልጎ ነው? እንድንል ያነሳሳናል፡፡
እስከ ሦስት ሺሕ ተማሪዎችን ያጎረ ትምህርት ቤት፣ በየወሩ ከተማሪዎች የሚሰበስበው ክፍያና ሊያወጣ የሚችለው ወጪ ሲሰላ በእርግጥ አሁን ባለው ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስከፍሉት ክፍያ ፈጽሞ ኢኮኖሚያዊ አግባብነት አለው ለማለት ያዳግታል፡፡
በትክክለኛ የኢኮኖሚ ቀመር የተሰላ ዋጋ የላቸውም፡፡ ቢኖራቸው እንኳ የትርፍ ሕዳጋቸው የትዬ ለሌ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህን ጉዳይ መርምሮ የአካሄዱን አደገኝነት ከግምት በማስገባት መንግሥት እንዳልተቆጣጠራቸው ያመላክተናል፡፡
‹‹ክፍያ ከጨመራችሁ ጨምሩ፤ ካልጨመራችሁ ልጆቻችሁን አስወጡ፤›› የሚሉ ደፋር የግል ትምህርት ተቋማት እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ በአግባቡ የሚሠሩትና ኃላፊነት በሚሰማቸው ተቋማት ላይም ጫና በማሳደር ዘርፉን እየበረዙት ነው፡፡
ጉዳዩ በወላጆች ላይ በሚፈጠረው ጫና የሚቆም ሳይሆን፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይም ችግር እንደሚያመጣ መታሰብ አለበት፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑ ታውቆ የትምህርት ተቋማቱ ቀድሞም ሆነ አሁን የሚያስከፍሉት ክፍያ አግባብ መሆን አለመሆኑን በግልጽ እንዲመረመር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ዝም ማለት የለበትም፡፡ አሁን ያለው ጭማሪ ምክንያታዊ መሆን አለመሆኑን መመርመር ብቻ ሳይሆን፣ እንዲህ ያሉ ተቋማት የትርፍ ህዳግ መገደብ ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ተቋማት አጠቃላይ የአገልግሎት ክፍያ ጉዳይ ለብቻው የሚተዳደርበት ሕግ ማውጣትም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ከትምህርት የሚሰበስቡት ገንዘብ በትክክል ለተቋሙ የሚያውሉና ሌሎች ቢዝነሶች ማሯሯጫ ጭምር በመሆኑ አማራጭ እንዲያጣ የተደረገው ወላጅ ላይ ዋጋ መቆለል ልምድ እየሆነ ሄዷልና ጉዳዩ እንዲህ በዋዛ የሚታይ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንዴ ቢታሰብ እኒህ ተቋማት ከመንግሥት በላይ የሚሆኑት እጃቸው ረዥም በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ አገር ለመለወጥ የምናስብ ከሆነ ዜጎች በተመጣጠነ ዋጋ ደረጃቸውን እንዲያስተምሩ፣ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እስከዛሬም መካከለኛ አቅም ያላቸው የሚባሉ ዜጎች ልጆች የዚህን ያህል ዋጋ ከፍለው ማስተማራቸው ለአገርም ጭምር በማሰብ በመሆኑ አሁን ያለውን አካሄድ መስበር ያስፈልጋል፡፡
ትምህርት ደንታ በሌላቸው አካላት መመራት እንደሌለበት ማስገንዘብ ለዚህም የሚሆን ሕግ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ሥር እየሰደደ ቢሆንም ነገሩን መስመር ለማስያዝ መሠራት ያለበት ዘላቂ የሆነ መፍትሔ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሌሎች አማራጮች እንዲቀርቡ ያስፈልጋል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤቶች እያስፋፋ ማድረግ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት የጥራት ደረጃ ከፍ እንዲል ባለማድረግ በእውቀት ሰበብ የሚደረግ አለስፈላጊ ብዝበዛ ሊቆም ይገባል፡፡