Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከመንግሥት ዕውቅና ውጪ መጥተዋል በተባሉ የሳዑዲ ዓረቢያ የሥራ ቅጥር ኤጀንሲ ልዑካን ላይ...

ከመንግሥት ዕውቅና ውጪ መጥተዋል በተባሉ የሳዑዲ ዓረቢያ የሥራ ቅጥር ኤጀንሲ ልዑካን ላይ ተቃውሞ ቀረበ

ቀን:

ኢትዮጵያ የላከችው ዕውቅና ያልተሰጠው ሞዴል የሥራ ውል ተቀባይነት አጣ

ከኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ውጪ ወደ አገር ውስጥ በመግባት በክርስትና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ትኩረት በሚሰጠው በትንሳዔ (ፋሲካ) በዓል ቀን ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የተለያዩ ሕክምና ተቋማትን ጎብኝተዋል የተባሉ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጡ የሥራ ቅጥር ኤጀንሲ ልዑካን ላይ ተቃውሞ ቀረበ፡፡

ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት 12 የጤና ምርመራ የሚሰጡ ተቋማትን አሠራርና በመካከላኛው ምሥራቅ አገሮች የተቀመጠውን መሥፈርት ማሟላት አለማሟላታቸውን በማረጋገጥ የዕውቅና ሰርተፊኬት ሊሰጡ እንደሆነ ቢነገርም፣ ዓላማው ግን ከዚህ የተለየ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

- Advertisement -

ከመንግሥት ዕውቅና ውጪና የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 የጣሰ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሞ ያቀረበው ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ወደ ውጭ አገሮች ለሚሄዱ ዜጎች ምርመራ የሚሰጡ ተቋማት አሠሪዎች ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው የተቃውሞ ደብዳቤ እንዳሳወቀው፣ በኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 አንቀጽ 9(1)፣ የጤና ሚኒስቴር ለሥራ ወደ ውጭ አገሮች ለሚሄዱ ዜጎች የጤና ምርመራ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን የመመልመል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ሚኒስቴሩም የአሠራር ሥርዓቱን በማስቀመጥ፣ ከጤና ተቋማቱ ምልመላ ጋር በተያያዘ በተጨባጭ እየታዩ ያሉትን ችግሮች የሚፈቱበት የአሠራር ሥርዓት የያዘ መመርያ ማውጣቱንም አስታውሷል፡፡ በመመርያው አንቀጽ 18 እንዳብራራው፣ በመመርያው መሠረት ሕጉን (አዋጁን) ለማስፈጸም መሠረት ያደረጋቸውን ሕጎች ለመፈጸም የሚያስችለውን አስተዳደራዊ መዋቅር መፍጠር እንደሚችልም፣ በአዋጅ ቁጥር 377/96 ሥልጣን እንደተሰጠውም የማኅበሩ ሊቀመንበር ዶ/ር ዮሴፍ ደነቀው ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት ማኅበሩ መቋቋሙን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ በአዲስ አበባ 59 የጤና ምርመራ ተቋማትንና ለክልል ከተሞች 12 መመልመሉን አክለዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ያወጣውን መሥፈርት በማሟላትና አስፈላጊው ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ሥራውን ለመጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው እየጠበቁ እያለ፣ ሕግን የተላለፈና ከመንግሥት ዕይታ ውጪ አሠራር ለመፍጠር 12 የጤና ምርመራ ተቋማት (ቀድሞም የተመረጡ ናቸው) ጋር ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ 12 የጤና ተቋማቱ ለመሥራት ተስማምተዋል የተባለው ጋምካ (GAMCA) በሚል ስያሜ ከሚጠራውና ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት ተገምግሞ በተዘጋው ተቋም ሥር፣ ጂሲሲ በተባለ የማይታወቅ ተቋም የተከለለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ባወጣው አዋጅ ቁጥር 923/2008 ድንጋጌ መሠረት ሥልጣን በተሰጠው ጤና ሚኒስቴር የተመለመሉ፣ በአጠቃላይ 71 የምርመራ ተቋማትን ለማግለልና ጥቅምን ጠቅልሎ ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ ድርጊቱ መሥፈርት አሟልተው የተመረጡ የጤና ምርመራ ተቋማትን የመመርመር መብትን የሚጎዳ፣ የነፃ ገበያን ውድድርን የሚያቀጭጭ፣ በዜጎች ላይ ወጪና እንግልትን የሚፈጥር መሆኑን ቀደም ብሎ መረጋገጡን ጠቁመው እንቅስቃሴያቸው እንዲገታ ጠይቀዋል፡፡   

ጋምካን ተክቶ በተቋቋመው ጂሲሲ በኩል 12 የጤና ምርመራ ተቋማት መመረጣቸው ሁለት ጉዳት እንዳለው የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፣ የመጀመርያው ለሥራ የሚሄዱ የቤት ሠራተኛ ዜጎች በፈለጉትና አቅራቢያቸው በሚገኝ የምርመራ ተቋም እንዳይጠቀሙ በማድረግ እንግልትና ወጪን እንደሚያስከትልባቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል ተቋማቱ በመረጧቸው ላኪ ኤጀንሲዎች ብቻ መላኩ ደግሞ፣ ምዝበራና መጨናነቅ በመፍጠር ቀደም ብሎ ይሠራበት የነበረው አሠራር ሊደገም እንደሚችል ሥጋታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የማኅበሩ ሊቀመንበር እንደገለጹት ያለ ምንም መንግሥታዊ ተቋምና መንግሥት ዕውቅና ሉዓላዊት በሆነች አገር ያውም በአገር አቀፍ በዓል የልዑካኑ መምጣት፣ በዲፕሎማሲ ተሽከርካሪ እየተዘዋወሩ የጠሯቸውን የጤና ምርመራ ተቋማት መጎብኘታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ጉብኝታቸውን ሕጋዊ ለማስመሰል በዕለተ ሰንበትና ትንሳዔ በዓል ቀን የሙስሊም የጤና ተቋማትን ከጎበኙ በኋላ፣ በማግሥቱ ሰኞ ሚያዝያ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌሎች የጤና ምርመራ ተቋማትን መጎብኘታቸውንም እንደደረሱበት ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ አሠራሩ ከአገሪቱ ደንብና አጠቃላይ አሠራር ጋር የማይገናኝ፣ መንግሥት የማያውቀው፣ የአገርን ሉዓላዊነት የሚፃረር፣ ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራርን የሚያስፋፋ፣ የነፃ ገበያ ውድድርን መርህ የሚፃረር፣ ዜጎችን ላላስፈላጊ ወጪ የሚዳርግና አገሪቱን ለውጭ ምንዛሪ ኪሳራ የሚዳርግ በመሆኑ፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በአስቸኳይ ከድርጊቱ እንዲታቀቡ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡   

በሌላ በኩል የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጅዳ ውስጥ ባደረጉት የሠራተኞችን ቅጥር የሚመለከት የሁለትዮሽ ስምምነት፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች ስምምነት መሠረት ሁለቱ አገሮች በሚመለከታቸው የአስፈጻሚ ተቋሞቻቸው ተቀባይነት ያለው ሞዴል የሠራተኞች ቅጥር ውል ተስማምተው እንደሚያፀድቁ፣ የሁለቱ አገሮች ኤጀንሲዎች አሠሪና ሠራተኛ ላይ ሕጋዊ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፤›› ይላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት የላከችው የሥራ ሞዴል ከስምምነቱ ውጪ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር አብዱል አዚዝ አህመድ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ ያሳያል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለይ በስምምነቱ መሠረት የሥራ ሞዴሎች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁት አምባሳደሩ፣ በሁለቱ አገሮች በተደረገው የሁለትዮሽ ስምምነትና በአዋጅ ቁጥር 923/2008 አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሠረት፣ ‹‹በአሠሪውና በኤጀንቱ የተፈረመውን የዜጎች የሥራ ውልና ተዛማጅ ሰነዶች ትክክለኛነታቸው ተረጋግጦ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መፅደቅ አለባቸው፤›› የሚለውን ድንጋጌም አስታውሰዋል፡፡ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት ለሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ‹‹ሞዴል የሥራ ውል›› ብሎ በኤምባሲው በኩል ቢልክም፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ግን እስካሁን አስተያየትና ምላሽ አለመስጠቱንም ኤምባሲው የጻፈው ደብዳቤ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱ አገሮች መካከል ዕውቅና ያገኘ ሞዴል የሥራ ውል አለመኖሩን፣ ተዛማጅ ሰነዶች ከስምምነቱ ጋር እንደማይጣጣሙም አክሏል፡፡ በመሆኑም ኤምባሲው ትክክኛነታቸውን በማረጋገጥ ተፈጻሚ እንዲያደርግና ሥራው እንዲጀመር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረባቸው ሞዴል የሥራ ውሎችና ተዛማጅ ሰነዶች ላይ ሕጋዊና አግባብነት ያለው ማብራሪያና መመርያ እንዲሰጠው ኤምባሲው ጠይቋል፡፡

ኤምባሲው ከላይ የተጠቀሰ አሠራር ግልጽ እንዲደረግለትና በስምምነቱ መሠረት እንዲፈጸም ጥረት ቢያደርግም፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኤጀንሲዎች ‹‹ሙሳነድ›› የሚባል የሠራተኞች ማዋዋያ ሰነድ በማዘጋጀት የኦንላይን ውል ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁም ተሰምቷል፡፡ ላኪ ኤጀንሲዎችና ተቀባይ ኤጀንሲዎች ኦንላይን ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፣ የሠራተኞቹ የሥራና የትምህርት ማስረጃ ሰነድ (ሲቪ) ተቀድቶ (ስካን ተደርጎ) በመላክ ቀጣሪዎቹ የሚፈልጉትን ሠራተኛ እንዲመርጡ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡

አሠሪዎች የተስማሙበትን ሠራተኛ ሰነድ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተልኮ ከፀደቀ፣ ቪዛ ለማግኘት ለሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ እንደሚላክም ታውቋል፡፡ ይኼ አሠራር አገሪቱ ከላኪና ከተቀባይ ኤጀንሲ ማግኘት የነበረባትን 20 ዶላር በአንድ ሰው ከማጣቷም በተጨማሪ፣ አሠራሩ አዋጅ ቁጥር 923/2008 የጣሰና ሙሳነድ የተባለው ኦንላይን ሰነድ ቢሰረዝ፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት መለኪያ የሌለው በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራበት ተጠይቋል፡፡

የሚመለከታቸውን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒቴርም ለኤምባሲው ስለሰጠው ምላሽ ለማወቅ ጥረት ቢደረግም የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች ማግኘት አልተቻለም፡፡ ጤና ሚኒስቴርን በሚመለከት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ኃላፊ በሰጡት አስተያየት፣ የልዑካን ቡድኑ መምጣቱንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ለማነጋገር ቢሞክርም አሠራርና አካሄዳቸው ትክክል እንዳልሆነ ተገልጾላቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...