Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበ40/60 ቤቶች ምክንያት የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ የቀረበው አቤቱታ ተቃውሞ ገጠመው

በ40/60 ቤቶች ምክንያት የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ የቀረበው አቤቱታ ተቃውሞ ገጠመው

ቀን:

ይደርሳል የተባለው ጉዳት ተሠልቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ

የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መቶ በመቶ ክፍያ በፈጸሙ 98 ግለሰቦች ተቃውሞ ምክንያት፣ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ ከከሳሾች ተቃውሞ ገጠመው፡፡

ዕጣ የወጣባቸው ከ18,000 በላይ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ለወጣላቸው ግለሰቦች እንዳይተላለፉና ወደፊትም ዕጣ የሚወጣባቸው ካሉ ዕጣው እንዳይወጣ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ቀጥታ ክስ ችሎት ዕግድ እንደተጣለባቸው ይታወሳል፡፡

ዘጠና ስምንት የሆኑ ግለሰቦች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በገቡት ውል መቶ በመቶ ክፍያ ከፈጸሙ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው፣ ወይም ቤቶቹ መቶ በመቶ ከከፈሉት ቤት ፈላጊዎች ቁጥር ካነሱ እነሱን ብቻ በማወዳደር በዕጣ እንደሚሰጥ ተስማምተው ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ግን ውሉ ተጥሶ ከ18,000 በላይ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ሁሉንም የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢዎችን በማወዳደር ዕጣው እንዲወጣ በመደረጉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዷል፡፡

መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ ግለሰቦች ክስ የመሠረቱት፣ ውል ባስገባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የቤቶቹን ፕሮግራም በአዋጅ አፀድቆ ፕሮግራሞቹን በሚያስፈጸመው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ግንባታውን በሚገነባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሦስቱም ተከሳሾች ለቀረበባቸው ክስ ምላሻቸውን ግንቦት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በማቅረብ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ለክርክር እንዲቀርቡ፣ ክርክሩ እስከሚካሄድ ዕጣ የወጣባቸውና ሊወጣባቸው የሚችሉ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕግድ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ ኢንተርፕራይዙ ግን ተቃውሞውን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡

የቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የመጀመርያ አቤቱታ፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 154 ድንጋጌ መሠረት ዕጣ በወጣባቸውም ሆነ በመገንባት ላይ ባሉ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በአቤቱታው እንዳስረዳው የከሳሾች ቁጥር 98 ነው፡፡ ዕጣ የወጣላቸው ደግሞ ከ18,000 በላይ ናቸው፡፡ ዕግዱ በቀጣይ ቤቶችን አስገንብቶ ለዕድለኞች ለማስተላለፍ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግድ ነው፡፡ ይኼ የሚሆነው ደግሞ ከሳሾች መብትና ጥቅም በሌላቸው ጉዳይ ላይ ነው፡፡

ከሳሾች ጥቅም አላቸው ቢባል እንኳን ከ98 ቤቶች በላይ ጥቅምና መብት ሊኖራቸው ስለማይችል፣ ዕጣ የወጣላቸውን ከ18,000 በላይ ዕድለኞች ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያግድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ዕግዱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ቤቶቹ ለዕድለኞቹ ቢተላለፉ ከሳሾች ገንዘባቸው ከወለድ ጋር ታሳቢ ሆኖ በዝግ አካውንት ተቀማጭ ሆኖ በቀጣይም ከሌሎቹ እኩል የዕጣ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁሞ፣ ጉዳት እንደማይደርስባቸውም አክሏል፡፡ ገና ለገና ‹‹ለወደፊት ዕጣ ሊወጣባቸው ይችላል›› በማለት ብቻ በምንም ዓይነት ማስረጃም ሆነ በቃለ መሃላ ሊረጋገጥ በማይችል ግምታዊ አቤቱታ፣ ዕግድ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ተገቢ እንዳልሆነም አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም ዕግድ መስጠቱ አግባብነት ስለሌለው ዕግዱ እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡ በሌላ በኩል ኢንተርፕራይዙ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 200 ድንጋጌ መሠረት፣ ከሳሾች ባሳገዷቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ለሚደርስ ኪሳራ ዋስትና እንዲያሲዙም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ዕጣ የወጣባቸው ቤቶችን በውል ባለማስተላለፉ ኢንተርፕራይዙ በቀን ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ፣ በወር ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም ክርክሩ አንድ ዓመት ቢፈጅ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ሊደርስበት እንደሚችል ገልጿል፡፡

ዕጣ እንዳይወጣባቸው ዕግድ የተጣለባቸውም የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግምቱ ለማይታወቅ ከፍተኛ ለሆነ የባንክ ወለድ ኪሳራ የሚዳረግ መሆኑን ጠቁሞ፣ ክርክሩ እስከሚጠናቀቅ ከሳሾች ለሚደርሰው ኪሳራ መያዣ እንዲያስይዙ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡

የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ላቀረበው አቤቱታ ከሳሾች የመቃወሚያ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከሳሾች ውል ማዋዋል ሒደቱ እንዲታገድ ሳይጠይቁ ዕግድ እንደተሰጣቸው ኢንተርፕራይዙ በአቤቱታው መግለጹን በሚመለከት በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፣ ዕግዱ የተሰጠው ሳይጠይቁ ሳይሆን ዕጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊተላለፉ እንደነበር መረጃ ስላላቸው ነው፡፡

በዚህ መሠረት እንዲታገዱ ጥያቄ በማቅረባቸውና የቤት ባለቤትነትም የሚተላለፈው ውል በሚዋዋሉበት ጊዜ በመሆኑ፣ በጥያቄያቸው መሠረት ፍርድ ቤቱ ዕግድ መጣሉ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ‹‹ውል ማዋዋል ሊከናወን እንደነበረ በቃለ መሃላም ሆነ በሌላ ማስረጃ ባላረጋገጡበት ጉዳይ›› በማለት ያቀረበው መከራከሪያ፣ ከእውነታው ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱ አቤቱታ ጋር እርስ በርሱ እንደሚጋጭ የጠቆሙት ከሳሾቹ በሌላ በኩል ‹‹ከሳሾቹ ባቀረቡት ቃለ መሃላ መሠረት የተሰጠው ዕግድ ይነሳልኝ›› ብሎ አቤቱታ ማቅረቡን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም ከሳሾች አቤቱታቸውን በቃለ መሃላ እንዳላረጋገጡ ገልጾ ኢንተርፕራይዙ ያቀረበባቸው አቤቱታ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቃለ መሃላው በማስረጃ የተረጋገጠ መሆኑንና ከመዝገቡ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከሳሾቹ መብትና ጥቅም እንደሌላቸው ጠቅሶ ኢንተርፕራይዙ ያቀረበውን አቤቱታ በሚመለከት በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ክስ ያቀረቡት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረጉትን ውል መሠረት አድርገው ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ሙሉ ክፍያ የፈጸሙበትንም ደረሰኝ ማያያዛቸውንም ገልጸዋል፡፡ የገለጿቸው ሰነዶች ክስ ባቀረቡባቸው ቤቶች ላይ በቂ መብትና ጥቅም እንዳላቸው የሚያስረዱ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ የኢንተርፕራይዙ አቤቱታ የከሳሾችን ሞራል የሚነካ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡  

ፍትሕ በሰዎች ብዛትና ማነስ የሚወሰን ወይም እንደማይሰጥ መሆኑን የገለጹት ከሳሾች፣ ክስ የመሠረቱት 98 ግለሰቦች ቢሆኑም የዳኝነት መክፈል የቻሉ 110 ግለሰቦችም በክሱ መካተታቸውን አሳውቀዋል፡፡ በአጠቃላይ መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ 21,000 ተመዝጋቢዎች መኖራቸውንና ዕግዱ የተሰጠው በ18,000 ዕጣ በወጣላቸው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከመመርያው ውጪ የተደረጉት ከላይ የተጠቀሱትን ሰዎች መብት ጭምር ለማስከበር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከሳሾች የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጋፋ ክርክር እንዳቀረቡ ኢንተርፕራይዙ መጥቀሱ ተገቢ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡

የከተማ  ነዋሪዎች ንብረት የማፍራትም ሆነ የመኖሪያ ቤት የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚኖራቸው ሕጉ ያስቀመጣቸውን ግዴታዎችና ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው ሲገኙ መሆኑን የጠቆሙት ከሳሾች፣ ሕግና መመርያን በመጣስ የሌሎችን ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ጨፍልቀው መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡ ከሳሾች ባንኩ ያስቀመጠውን ‹‹ቅድሚያ የከፈለ ቅድሚያ ያገኛል›› የሚለውን መመርያና ውል ተማምነው፣ ንብረታቸውን በመሸጥና በከፍተኛ ወለድ በመበደር ከአቅማቸው በላይ ክፍያ መፈጸማቸውንም አክለዋል፡፡ ጥያቄያቸውን ያቀረቡትም ሆነ ሊስተናገዱ የሚገባው በውሉና በመመርያው በተቀመጠው መርህ መሠረት መሆኑንም አክለዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን ያከበረ አሠራር ሲጣስ ፍርድ ቤት ተገቢውን ዕግድ ሰጥቶ ጉዳዩን በመመርመር፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን ጭምር የማስከበር ኃላፊነት ስላለበት፣ እነሱም ያደረጉት ይኼንኑ በመሆኑ ኢንተርፕራይዙ ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከሳሾች ሊተካ የማይችል ጉዳት እንደማይደርስባቸው በመጠቆም የቀረበውን ክርክርም ተቃውመዋል፡፡ የእነሱ ገንዘብ በዝግ አካውንት እንደተቀመጠና በቀጣይ በሚወጣ ዕጣ ላይ እኩል ተሳታፊ እንደሆኑ በመግለጽ፣ ‹‹ሊተካ የማይችል ጉዳት አይደርስባቸውም›› ማለቱ በምን ዓይነት መመዘኛ እንዳየው ባይገባቸውም፣ የመከራከሪያ ሐሳቡ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ገንዘባቸው በዝግ አካውንት ተቀምጧል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቁመው፣ ምክንያታቸው ደግሞ ገንዘባቸው ወጪ ተደርጎ ቤቶቹ የተሠሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዋናነት ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የመብት ጥያቄ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡ መብታቸው ተከብሮ ዕጣ የወጣባቸው ቤቶች በድጋሚ ዕጣ እንዲወጣባቸውና ይኼ ካልተደረገ ቤቶቹ ቢተላለፉ ግልጽ የሆነ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል በማመናቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ከሚገነቡበት ሥፍራ አንፃር ተለያዩ ዋጋ ያላቸው ከመሆኑም በላይ፣ ተፈላጊነታቸውም እንደሚገኙበት ቦታ (Location Value) እንደሚለያዩም የጉዳቱን መጠን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ቤቶቹ ከተላለፉ በኋላ በክርክር ሒደት አሸናፊ ሆነው ለእነሱ ቢወሰን፣ ዕጣ የወጣባቸውን ቤቶች የማግኘት ዕድል ስለማይኖራቸው ይኼም ሊተካ የማይችል ጉዳት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ በሚወጣው ዕጣ ዕድላቸውን እንዲሞክሩ ሳይሆን ‹‹ቅድሚያ የከፈለ ቅድሚያ ይሰጠዋል›› በሚለው ውልና መመርያ መሠረት መብታቸው ተከብሮ፣ ሙሉ ክፍያ ከከፈሉት ጋር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲወዳደሩ እንጂ ዕድላቸውን ለመሞከር እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣይ ዕጣ ከመውጣቱ በፊት የተጀመረው የሕግ ክርክር እልባት ሊሰጠው እንደሚገባም አክለዋል፡፡ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕግድ እንዲጣልባቸው ዳኝነት መጠየቃቸው፣ ‹‹ቅድሚያ የከፈሉ ቅድሚያ ይስተናገዳሉ›› የሚለው ከንግድ ባንክ ጋር የተደረገው ውል (ሕግ) እንዲከበር በመሆኑ፣ ዕግዱ እንዲነሳ መጠየቅ፣ ‹‹ክርክሩ ሳይደረግ ውሳኔ ይሰጠኝ›› ማለትና ‹‹የክሱ ምክንያት ውድቅ ይደረግ›› በመሆኑ፣ ጥያቄው ተገቢ ስላልሆነ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ዋስትናን በሚመለከት ኢንተርፕራይዙ ያቀረበውን አቤቱታም ከሳሾች ተቃውመዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ወለድ የሚከፍለው በቤቶቹ ላይ ዕግድ ስለተጣለበት ሳይሆን፣ ቤቶቹን የገነባው ከባንክ ተበድሮ በመሆኑ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱን ለማሳሳት ካልሆነ በስተቀር ዕግድ ስለተጣለበት ብቻ ወለድ እየከፈለ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ እነሱ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹በክርክር ቢረቱ የሚከፍሉት ዋስትና የላቸውም›› በሚል ያቀረበው መከራከሪያ ውኃ የማያነሳ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀው፣ ‹‹የከሳሾች ገንዘብ በዝግ አካውንት ተቀምጧል›› ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 200 (2) ድንጋጌ መሠረት ዋስትና የሚጠየቀው፣ ከሳሽ በውጭ አገር የሚኖር ሲሆንና አገር ውስጥ ምንም ዓይነት ተንቀሳቃሽ ንብረት የሌለው መሆኑ ሲረጋገጥ መሆኑን የጠቀሱት ከሳሾቹ፣ ከስድስት ግለሰቦች ውጪ ሁሉም ነዋሪነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ኢንተርፕራይዙ ዋስትና ማስያዝ ግድ የሚላቸው ስለመሆኑ በማስረጃ የተደገፈ ምክንያት ባለማቅረቡ፣ ያቀረባቸው ጥያቄዎችና መቃወሚያዎች ውድቅ እንዲደረግላቸው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 92 መሠረት ምላሻቸውን ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይደርሳል የተባለው የጉዳት መጠን ተሠልቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ተከራካሪ ወገኖች ያቀረቡትን ክርክር መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...