Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ትወልደ ኢትዮጵያዊው ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ትወልደ ኢትዮጵያዊው ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ መወሰኑ ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

በሁለቱ አገሮች መካከል ተጠርጣሪን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት የለም

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአሜሪካ ሁለት ሰዎችን በመግደልና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጠርጥሮ፣ በኢትዮጵያ በቁጥጥር ሥር የሚገኘውን በትውልድ ኢትዮጵያዊና በዜግነት አሜሪካዊ የሆነውን ወጣት አሳልፎ ለመስጠት መወሰኑ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ዓቃቤ ሕግ ውሳኔውን ያስተላለፈው በማቋቋሚያ አዋጁ 943 አንቀጽ 6 (12) በተሰጠው ድንጋጌ መሠረት መሆኑን ቢገልጽም፣ አንቀጹ የሚገልጸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር እንደሚያደርግ ከመግለጽ ባለፈ፣ ተጠርጣሪን አሳልፎ ለመስጠት የመወሰን ሥልጣን የሚሰጠው እንዳልሆነ የሕግ ባለሙያዎች እየገለጹ ነው፡፡

- Advertisement -

ተጠርጣሪው ዮሐንስ ነሲቡ የሚባል ወጣት ሲሆን፣ የፌዴራል ፖሊስ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር አውሎ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት አቅርቦታል፡፡ ግለሰቡ በአሜሪካ በሁለት ሰዎች ግድያና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር መጠርጠሩን ገልጾ፣ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጠይቆበት እስከ ሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሲያቀርበው መቆየቱን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ ያሳያል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች የፖሊስን ተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ሲቃወሙ ቆይተዋል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመው በአሜሪካ መሆኑን ፖሊስ ማስረዳቱን ለፍርድ ቤቱ ጠቁመው፣ ምርመራውን ለማድረግ የሚያስችለው የሕግ መሠረት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ተጠርጣሪው በኢትዮጵያ እንዲመረመር ስለመጠየቁ የቀረበ ማስረጃ በሌለበትና በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ተጠርጣሪን አሳልፎ ለመስጠት የተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ፣ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ተገቢ ባለመሆኑ ደንበኛቸው ከእስር እንዲፈታ ወይም ተመጣጣኝ ዋስትና እንዲጠበቅለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ያደረጉትን ክርክር ሲመረምር፣ ፖሊስ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉን አንቀጽ 59 (2) መሠረት አድርጎ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተገቢ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው በአሜሪካ ሁለት ሰዎችን በመግደል ወንጀል መጠርጠሩን ፖሊስ ገልጾ፣ የጠየቀውን 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ በቂ ነው ያለውን መፍቀዱን በትዕዛዙ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሌላው የገለጸው ፖሊስ ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጠርጣሪውን ይዞ ቀርቦ ድርጊቱ የተፈጸመው በአሜሪካ በመሆኑ፣ በአሜሪካ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ ውሳኔ ያስተላለፈበትን ሰነድ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ፖሊስ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 59 (2) ጠቅሶ የጠየቀው ዳኝነት ለምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት እንጂ፣ ተጠርጣሪው ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ የቀረበለት ጥያቄ ባለመኖሩ ፍርድ ቤቱ ባልተጠየቀበት ዳኝነት ውሳኔ መስጠት የማይችል መሆኑን በትዕዛዙ ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃዎች ከአሜሪካ ተጠቃለው እስከሚመጡ በቂ የሆነ ጊዜ ቢሰጠውም፣ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ የሚያስጠረጥር ማስረጃ አቅርቦ ለፍርድ ቤቱ ያላስረዳ መሆኑን ጠቁሞ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ተላልፎ እንዲሰጥ የሰጠውን ውሳኔ መቃወማቸውን ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡ በውሳኔውም ላይ ዕግድ እንዲጣልላቸው ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸውንም አክሏል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው ተላልፎ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤቱ የቀረበለት ጥያቄ እንደሌለ አስታውሶ፣ ፍርድ ቤቱ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ውሳኔ በጊዜያዊነት ሊያግድ የሚችልበት አግባብ እንደሌለ በመግለጽ አቤቱታቸውን እንዳልተቀበለው በትዕዛዙ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ውድቅ በማድረግና የተጠርጣሪው የአካል ደኅንነት መብት መጠበቅ እንዳለበት ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቶታል፡፡

ነገር ግን ተጠርጣሪው በጠበቆቹ በኩል ባቀረበው አቤቱታ እንደገለጸው፣ በዓለም አቀፍ ሕግ ልማድ መሠረት ማንም አገር የራሱን ዜጋ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ተጠርጣሪው ከኢትዮጵያዊ እናትና አባት በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሆኑና በሁለቱ አገሮችም ተጠርጣሪን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባለመኖሩ፣ ተላልፎ ሊሰጥ እንደማይገባም አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜግነት ሲያገኝ ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ያጣል፤›› በማለት ያወጣው የዜግነት አዋጅ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር መሆኑን በማመን በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በራሱ መሪነት እየተሻሻለ መሆኑን አስታውሶ፣ እሱም ኢትዮጵያዊ ዜግነቱን ያለ ፈቃዱ ሊያጣ እንደማይገባ አስረድቷል፡፡

እናት፣ አባቱና ዘመዶቹ ባሉበት በአገሩ ሊዳኝ እንደሚገባም ጠይቋል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 21 (1) ላይ በግልጽ ተደንግጎ እንደሚገኘው አንድ የውጭ አገር ሰው ከኢትዮጵያ ግዛት ውጪ ሆኖ መደበኛው የወንጀል ሕግን በመተላለፍ በፈጸመው ወንጀል የተከሰሰ እንደሆነ፣ በመንግሥታት መካከል በተደረገ ውል ወይም በዓለም አቀፍ ልማድ መሠረት አግባብ የሆነ ጥያቄ ሲቀርብ፣ ለፍርድ ወደሚቀርብበት አገር ተላልፎ እንደሚሰጥ ተጠርጣሪው በጠበቆቹ አማካይነት አስረድቷል፡፡

ነገር ግን በሁለቱ አገሮች መካከል ተጠርጣሪን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በሌለበትና ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊት አገር በግዛቷ ውስጥ በሚገኙ ላይ ሁሉ ሙሉ ሥልጣን እያላት፣ አሳልፋ የምትሰጠው በእንካ ለእንካ መርህ መሠረት በሚደረግ አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ብቻ እንጂ፣ በደፈናው አለመሆኑንም አስረድቷል፡፡

አንድ ተጠርጣሪ ተላልፎ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ተጠርጣሪን በአግባቡ ለመለየት የሚያስችል የጣት አሻራ፣ የወንጀል ድርጊቱን የሚያቋቁሙ የሕግ ክፍሎችና ሊጣል የሚችለውን የቅጣት ዓይነት፣ ወንጀሉን የሚመለከቱ የይርጋ ደንቦች ወይም ቅጣት መፈጸም አለመፈጸሙን የሚያመለክት መግለጫና የመያዣ መየጠቂያ፣ ከጠያቂ አገር መቅረብ የነበረበት ቢሆንም ያ አለመደረጉንም የተጠርጣሪው ጠበቃ አስረድተዋል፡፡

ጥያቄው የቀረበው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ከመሆኑም በተጨማሪ ጥያቄው በቀጥታ የቀረበው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ልማድ መሠረት ሊከተል የሚገባውን የዲፕሎማሲ የፍሰት መስመር እንዳልጠበቀ የሚያሳይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት በአዋጅ ቁጥር 790/2005 ድንጋጌ መሠረት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንጂ በቀጥታ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...