Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከንብረት ግዥ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አራት የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች...

ከንብረት ግዥ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አራት የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ታሰሩ

ቀን:

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል 21 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል

የመንግሥት ግዥ መመርያን በመጣስና ግዥዎችን በሕገወጥ መንገድ በመፈጸም በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (የቀድሞ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን) እና የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ግብረ አበሮቻቸው የተባሉ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከፍተኛ ኃላፊዎች የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባና ሁለት ምክትል ዳይሬክተሮች፣ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ፣ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኃይለ ሥላሴ ቢሆን፣ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አታክልት ተካና የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ በድምሩ 59 ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቀዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ በጽሕፈት ቤታቸው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የሙስና ዋና ምንጭ ከሚባሉትና ሆነው ከሚገኙት አንዱና ዋናው በሆነው የግዥ ሒደት ጋር በተያያዘ ምርመራ ተሠርቷል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ያለውን ሕጋዊ ግንኙነት በሚመለከት በተደረገ ምርመራ፣ የተፈጸመውን ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

አገልግሎቱ ከ400 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ማድረሱን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ዓለም አቀፍ የግዥ ጨረታውን በ94 ሚሊዮን ዶላር ያሸነፈው የውጭ ድርጅት እያለ፣ ከእሱ በ19 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለውን ድርጅት በማሳለፍ የተጠቀሰውን ያህል ዶላር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ያላግባብ 19 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈል ከማድረጋቸውም በላይ የማጓጓዙን ሒደት በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት በኩል ማድረግ ሲገባቸው፣ በሌላ በማጓጓዝ አራት ሚሊዮን ዶላር በመክፈል በአጠቃላይ የ23.7 ሚሊዮን ዶላር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ ላይ የዳቦ ዱቄት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲፈጠር ማድረጋቸውንም አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ግብረ አበሮቻቸው ከሌሎች ተቋማት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ከኮምፒዩተር ግዥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የቴክኒክ ግምገማውን ያለፈ ድርጅትን ትተው ያላለፈው እንዲያቀርብ በማድረግ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡

ቀድሞ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ይባል የነበረውና አሁን የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሚባለው ተቋም በቦርድ የሚተዳደር ቢሆንም፣ የተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ አታክልት ተካና ግብረ አበሮቻቸው እርስ በርሳቸው በመመሳጠር የብረት ክምችት እያለ ቦርዱን ሳያስፈቅዱና አስፈላጊም ሳይሆን የ58 ሚሊዮን ብር የግንባታ ብረት ግዥ እንዲፈጸም በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚሁ ተቋም ከፍተኛ ክሊኒክ የማያስፈልጉ መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችን በመግዛት፣ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም አክለዋል፡፡

ከአንድ አቅራቢ ብቻ በቀጥታ ለአገሪቱ የሚገዙ መድኃኒቶችን ከግዥ መመርያ ውጪ ግዥ በመፈጸም 79 ሚሊዮን 479 ሺሕ ዶላር ግዥ በመፈጸም ከፍተኛ ጉዳት የፈጸመው ደግሞ፣ በአቶ ኃይለ ሥላሴ ይመራ የነበረው የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ በሕጋዊ መንገድ በግልጽ ጨረታ ከዝቅተኛ አሸናፊ መግዛት የሚቻልን የመድኃኒትና መገልገያ መሣሪያ በሕገወጥ መንገድ ግዥ በመፈጸም 92 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በውስን ጨረታ የ23 ሚሊዮን ዶላር መድኃኒቶችን በመግዛት፣ በተጨማሪም የመድኃኒት መጋዘን ግንባታ ማስፋፊያ በማለት እጥፍ ክፍያ በመፈጸም 15 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ዋና ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል፡፡

የአራቱም ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ግብረ አበሮቻቸው ላይ ምርመራ መደረጉን፣ ኃላፊዎቹ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ምዝገባ አዋጅ መሠረት ያስመዘገቡትንና ከገቢ በላይ አካብተው የተገኘውን ሀብት የመለየት ሥራ ተሠርቶ፣ ከፍተኛ ሀብት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ቤታቸውም ሲበረበር የተለያዩ የቤት ካርታዎችና የባንክ ደብተሮች መገኘታቸውን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ ከጠቀሷቸው ተጠርጣሪዎች መካከል 21 የሚሆኑት ዓርብ ሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዳታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው፣ በግላቸው ጠበቃ አቁመው መከራከር እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳታቸውና ቃለ መሃላ በመፈጸማቸው፣ መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ አቁሞላቸው ሚያዝያ 7 እና 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤት ከቀረቡት ውስጥ ከግዥና ንብረት ማስወገድ አቶ ተስፋዬ ብርሃኑ፣ አቶ ሰለሞን ዓይን ይመር፣ አቶ ዮሴፍ ራፊሶ፣ አቶ ተክለ ብርሃን ገብረ መስቀል፣ ትሩፋት ነጋሽ፣ አቶ ዘሪሁን ስለሺ፣ ከንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አቶ መንግሥቱ ከበደ (ዋና ሥራ አስፈጻሚ)፣ ከመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት አቶ ኃይለ ሥላሴ ቢሆን፣ አቶ የማነ ብርሃን ታደሰ፣ አቶ ሙከሚል አብደላና አቶ ሱፊያን ኑሩ ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...