Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ  ምንዛሪ  ተመን  በገበያ  እንዲወሰን  መንግሥት  ማቀዱ ተሰማ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ የሚወሰንበት አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት ዘላቂ ወይም የረዥም ጊዜ ዕቅድ መያዙ ተሰማ።

አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ከሚደረግበት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት እንዲያበቃ፣ በፍላጎትና አቅርቦት የገበያ መርህ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲወሰን መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል።

በገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደሩ ላይ በመንግሥት የተወሰነው ይህ የስትራቴጂ ለውጥ በፍጥነት ተግባራዊ የሚደረግ ሳይሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት በቀጣይ በዘላቂነት የሚተካ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል። ይህ የሚሆንበት ምክንያትም በቂ ዝግጅት የሚያስፈልግ በመሆኑ ነው።

ወደዚህ የውጭ ምንዛሪ የገበያ ሥርዓት ለመሸጋገር የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይኤምኤፍ ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት “Fixed Foreign Exchange Market” የሚባል ሲሆን፣ ዶላር የመግዛት አቅምን መሠረት በማድረግ የብር የምንዛሪ ዋጋ ተመን ላልተወሰነ ጊዜ በቋሚነት በአንዴ የሚወሰንበት፣ የሚጣልበት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ብር ከመግዛት አቅሙ በላይ ከፍተኛ ዋጋ እንዲይዝ እንዳደረገው የአይ.ኤም.ኤፍ መረጃ ያመለክታል። በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የአይኤምኤፍ መረጃ እንደሚያስገነዝበው፣ የኢትዮጵያ ብር ዶላርን የመግዛት አቅም ከትክክለኛ የመግዛት አቅሙ በ20 በመቶ ከፍ ብሎ እንደሚገኝና ይህም የኤክስፖርት ዘርፉን እንደማያበረታታ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በገበያ መርህ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ የገበያ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባው ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያሳስብ መቆየቱንና ተቀባይነት አለማግኘቱን ይጠቁማል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት እዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ሕግ እንዲወሰን ማድረግ ተገቢና ዘለቄታዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ያስረዳሉ።

ስለውሳኔው እንደማያውቁ የተናገሩት ባለሙያው፣ በገበያ ወደሚመራ የውጭ ምንዛሪ የገበያ ሥርዓት መሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ።

 ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ይኼንን በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓት መተግበር የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን በመጥቀስ፣ በፍጥነት ሊተገበር የሚችል ዕቅድ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ወደዚህ የግብይት ሥርዓት ለመግባት ቀዳሚ ከሚባሉት ቅድመ ሁኔታዎች ዋነኛው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት መያዝ እንደሆነ የሚያስረዱት እዮብ (ዶ/ር)፣ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ በገበያ እንዲወሰን ማድረግ የብር ምንዛሪ ተመን በከፍተኛ ደረጃ የማናር ውጤትን በማስከተል፣ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል፣ የዕዳ መጠንን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያንርና አጠቃላይ ውጤቱም ማክሮ ኢኮኖሚውን እንደሚያዛባ በመጥቀስ በአሁኑ ወቅት ሊተገበር የሚችል አለመሆኑን አስረድተዋል።

ብሔራዊ ባንክ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በአሁኑ ወቅት ያለው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለሁለት ወር ከቀናት የውጭ ግዥዎች እንደሚበቃ፣ ይኼንንም በጥንቃቄና የመሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦቶችን በማስቀደም ወጪ እንደሚደረግ ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች