Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜቴክ የጀመረው ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ  የሞሮኮ ኦሲፒ ማዳበሪያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ሊጠቃለል ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት በዚህ ዓመት 15 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በ2004 ዓ.ም. የጀመረውና ከ50 በመቶ በታች የግንባታ ደረጃ ላይ የሚገኘው ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት እንቅስቃሴ ለጀመረው የሞሮኮው ኦሲፒ ኩባንያ ሊተላለፍ ነው።

የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ለሞሮኮው ኦሲፒ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ለማስተላለፍ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ግዙፍ ዕቅድ ይዞ መንቀሳቀስ በጀመረው የሞሮኮው ኩባንያ ሥር የሚጠቃለለው፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በገባው የሽርክና አሠራር መሠረት መሆኑ ታውቋል።

ይህም ማለት የሞሮኮው ኩባንያ በኢትዮጵያ በሚጀምረው የማዳበሪያ ኢንቨስትመንት ውስጥ መንግሥት በሸሪክነት ድርሻ ይይዛል።

የሞሮኮው ኩባንያ በድሬዳዋ ከተማ በ3.7 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት፣ መሬት ተቀብሎ በዝግጅት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ሜቴክ በምዕራብ ኦሮሚያ ያዩ አካባቢ የታቀደውን ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ውል የፈጸመው በ2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ የሚያስረከብ ስለመሆኑም በውሉ ላይ መጠቀሱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ምርመራ ያመለክታል። በዓመት 300 ሺሕ ቶን ዩሪያ ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሎ ግንባታው በ2004 ዓ.ም. የተጀመረው ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ በአሁኑ ወቅት የሚገኝበት የአፈጻጸም ደረጃ 46 በመቶ ነው።

ግንባታው ሲጀመር የግንባታው አጠቃላይ ወጪ 11 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ቢገመትም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በእጥፍ አድጎ ከ22 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስወጣ የፕሮጀክቱ ባለቤት የኬሚካል ኮርፖሬሽን ይገልጻል።

 ኮርፖሬሽኑ እስከ ዘንድሮ ድረስ ለሜቴክ 5.9 ቢሊዮን ብር የከፈለ ሲሆን፣ ለግንባታው ማስፈጸሚያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለወሰደው ብድር የወለድ ክፍያ ደግሞ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ አውጥቷል።

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችልና ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከሚጠይቀው ወጪ አንፃር አዋጭ እንደማይሆን በመግለጽ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት በጠየቀው መሠረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሮጀክቱ እንዲቋረጥ ባለፈው መስከረም ወር ውሳኔ በማሳለፉ፣ ኮርፖሬሽኑም ከሜቴክ ጋር የገባውን ውል አቋርጧል።

 በአሁኑ ወቅትም የፕሮጀክት ርክክብና የሀብት ግመታ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በዚህ እንዳለ የግብርና ሚኒስቴር ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ለማዳበሪያና ለተለያዩ ኬሚካሎች ግዥ 20 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቅዶለት ግዥዎች መፈጸሙን፣ ማክሰኞ ሚያዚያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አስታወቋል።

ከዚህ ውስጥ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው 1.12 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ወጪ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በቀጣይ የማዳበሪያ አቅርቦትን በአገር ውስጥ በማምረት መመለስ ካልተቻለ በየዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማውጣት፣ ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገልጿል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች