Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበማዕድናት ግብይት ላይ ከፍተኛ ቁጥጥርና ቅጣት የሚጥል አዋጅ ሊወጣ ነው

በማዕድናት ግብይት ላይ ከፍተኛ ቁጥጥርና ቅጣት የሚጥል አዋጅ ሊወጣ ነው

ቀን:

የግብይት ሕጉን የሚተላለፉ ንብረታቸው ይወረሳል

እስከ 150 ሺሕ ብርና አሥር ዓመት እስራት ቅጣት ይጥላል

የማዕድናት ግብይትን በከፍኛ ቁጥጥር የሚያስተዳደርና ከተቀመጠው የግብይት ማዕቀፍ ውጪ በሚንቀሳቀሱ ላይ ንብረት ከመውረስ አንስቶ፣ እስከ አሥር ዓመት ጽኑ እስራትና እስከ 150 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት የሚጥል ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

- Advertisement -

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሚያዚያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው የተወያየበት ይህ የማዕድን ግብይት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ በመግቢያ ሀተታው፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት መንግሥትና ሕዝብ በመሆናቸው የማዕድን ሀብት ከተመረተ በኋላ የሚኖረውንም የግብይት ሥርዓት በሕግ ቁጥጥር እንዲደረግበት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መዘጋጀቱን ይገልጻል።

በሥራ ላይ የሚገኘው የማዕድን ግብይትን የሚያስተዳድረው አዋጅ የከበሩ ማዕድናትን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ ሁሉንም ዓይነት የማዕድን ምርቶች እንዲያጠቃልል ተደርጎ የተዘጋጀ ነው። በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ለአንድ ዓይነት የማዕድን ፈቃድ የወሰደ ሰው፣ ሁሉንም ዓይነት የማዕድን ግብይት በዚያው በአንድ ፈቃድ የሚሠራበትን ሁኔታ ረቂቅ አዋጁ ይከለክላል።

በዚህም መሠረት በማዕድን ግብይት የተለያዩ ሰንሰለቶች ውስጥ ለመሳተፍ፣ የማዕድን አቅራቢነት ፈቃድ፣ የማዕድን ዕደ ጥበብ ፈቃድ፣ የማዕድን ማጣራት ፈቃድ፣ የማዕድን ማቅለጥ ፈቃድ፣ የማዕድን ንግድ ፈቃድ፣ የማዕድን ላኪነት ፈቃድ ሥልጣን ካለው የመንግሥት አካል በሕግ የሚጠየቀውን መመዘኛ አሟልቶ ማግኘትን ይጠይቃል። የማዕድን ማጥራት፣ የብረትና ብረት ነክ ማዕድናት ማቅለጥና የማዕድን ላኪነት የንግድ ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈለጉትን የፈቃድ ዓይነቶች የፌዴራል መንግሥት የሚሰጥ ሲሆን፣ የተቀሩት በክልል መንግሥታት እንደሚሰጡ በረቂቁ ተመልክቷል።

የማዕድን ንግድ ፈቃድ ከከበሩና በከፊል ከከበሩ ማዕድናት ተሠርተው የመጨረሻ ቅርፃቸውን የያዙ ጌጣጌጦች በጅምላ ገዝቶ፣ በአገር ውስጥ ገበያ የመሸጥ መብትን የሚሰጥ ነው።

 የማዕድን ላኪነት ፈቃድ ደግሞ የመጨረሻ ቅርፃቸውን የያዙ የወርቅና የብር ማዕድናትን፣ በጥሬ ወይም ሙሉ በሙሉ የተሰናዱ የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናትን፣ እንዲሁም በጥሬውና እሴት የጨመሩ ሌሎች ማዕድናትን ወደ ገበያ የመላክ መብት የሚሰጥ ነው። የዕደ ጥበብ ፈቃድ የወሰደ ሰው ለሥራ የሚያስፈልገውን ጥሬ ወርቅ ወይም ብር ከባንክ ወይም ሕጋዊ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ብቻ እንዲገዛ ረቂቁ ግዴታ ይጥላል።

የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው ወይም በፈቃዱ ያልተመለከቱ ሥራዎችን ማከናወን በረቂቁ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

ተገቢውን ፈቃድ ሳያወጣ ወይም የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሳይኖረው በከበሩ ወይም በከፊል በከበሩ ወይም ብረት ነክ ማዕድናት ግብይት ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው፣ በእጁ የሚገኙ ማዕድናትና ተያያዥ መሣሪያዎች ወይም ማሽኖች እንደሚወረሱበትና ከ50 ሺሕ እስከ 100 ሺሕ ብር ቅጣትና እስከ ሰባት ዓመት እስራት እንደሚቀጣ በረቂቁ ተመልክቷል።

የአቅራቢነት ፈቃድ የተሰጠው ሰው ወርቅ ወይም ብር ለብሔራዊ ባንክ ወይም በሕግ ሥልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ ያስተላለፈ እንደሆነ፣ ወይም የተሳሳተ ጥራት ያለው ወርቅ ወይም ብር ለባንኩ ካቀረበ፣ ከተሰጠው ፈቃድ ጋር የተያያዙ ንብረቶቹና በይዞታው የሚገኙ ማዕድናት እንደሚወረሱና ከ100 ሺሕ እስከ 150 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮና እስከ አሥር ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት እንደሚጣልበት በረቂቁ ተካቷል።

ረቂቁን የተመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለዝርዝር ዕይታ ለተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...