Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ቦይንግ በቅርቡ አደጋ የደረሰበት አውሮፕላን በሶፍትዌሩ ችግር መሆኑን አመነ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ ላይ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጥቂት እንደበረረ አደጋ የደረሰበት ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን፣ አደጋው የደረሰበት በሶፍትዌር ችግር መሆኑን ቦይንግ አመነ፡፡

  የአደጋው መንስዔ የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርት ሐሙስ መጋቢት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. የመርማሪ ቡድኑ ካስታወቀ በኋላ፣ የቦይንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴኒስ ሙለንበርግ በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው ኤምካስ የተባለው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ለአደጋው መንስዔ መሆኑን አምነዋል፡፡

  ዋና ሥራ አስፈጻሚው የአደጋው የመጨረሻው ሪፖርት በመንግሥት ባለሥልጣናት ይፋ እንደሚደረግ ገልጸው፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ መሠረት ግን ኤምካስ የተባለው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር በስህተት በሚሰበስበው መረጃ ምክንያት አደጋው መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የችግሩ ባለቤት እኛው ስለሆንን፣ እንዴት እንደምንፈታውም እናውቀዋለን፤›› ብለዋል፡፡

  አደጋው ከተከሰተ ጀምሮ የኩባንያው ከፍተኛ ኢንጂነሮችና ባለሙያዎች፣ ከአሜሪካው የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽንና ከኩባንያው ደንበኞች ጋር በመሆን የሶፍትዌር ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግሩን ለመቅረፍ እየተቃረቡ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በሚመጡት ሳምንታት ችግሩ መፍትሔ አግኝቶ የቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖች ወደ በረራ እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም በቅርቡ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት፣ የኤምካስ የበረራ መቆጣጠሪያ በበረራና በሥልጠና ማኑዋሎች ያልተካተተና በኢንዶኔዥያ ላየን ኤር አውሮፕላን ላይ አደጋ ከደረሰበት በኋላ የተገለጸ ነው፡፡ አደጋ የደረሰበት የኢቲ 302 በረራ ላይም አውሮፕላኑ ሳይታዘዝ ሦስት ጊዜ አፍንጫውን የመድፈቅ ችግር እንደተከሰተበት ገልጸዋል፡፡ አቶ ተወልደ ቦይንግ የሶፍትዌር ችግሩን ለመቅረፍ ገና በሙከራ ላይ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ችግሩ ይቀረፋል ብለው እንደማያምኑ አስታውቀዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 378 ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላኖች እንዳይበሩ የታገዱ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የችግሩ ሰለባ እንደመሆኑ መጠን የሶፍትዌር ችግር ቢቀረፍ እንኳን አውሮፕላኑን ለማብረር የመጨረሻው እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

  የአውሮፕላን አደጋው ላይ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው የምርመራ ቡድን ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአውሮፕላን አብራሪዎቹ የብቃት ችግር እንደሌለባቸው አስታውቋል፡፡ የመርማሪ ቡድኑ በአውሮፕላን አደጋው ቅድመ ሪፖርቱ አራት ነጥቦችን ያነሳ ሲሆን፣ በሐሳቦቹ ተመሥርቶ ሁለት የደኅንነት ምክረ ሐሳቦች አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት አውሮፕላኑ መብረር የሚያስችለው የፀና ሠርተፊኬት ያለው መሆኑን ገልጾ፣ አብራሪዎቹ ይኼንን በረራ ለማድረግ የሚያስችላቸው ብቃትና ተገቢው የበረራ ፈቃድ ነበራቸው ብሏል፡፡ ሪፖርቱ አክሎም አውሮፕላኑ ለበረራ ሲነሳ በትክክለኛ መስመርና ለመብረር የሚያስችለው ሁኔታ ላይ እንደነበር ጠቁሞ፣ አብራሪዎቹ አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በአምራቹ የተሰጠውን የበረራ ቅደም ተከተል ተከትለው አውሮፕላኑን በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞክሩም እንዳልቻሉ አስታውቋል፡፡

  አውሮፕላኑ በሰላም ተንደርድሮ ተነስቶ እንደነበር የገለጹት የመርማሪ ቡድኑ መሪዎችና አባሎች፣ በረራው ከተጀመረ በኋላ በተደጋጋሚ የአውሮፕላን አፍንጫ መደፈቅ ሲያሳይና አብራሪዎቹም ለመቆጣጠር ቢሞክሩም ሊቆጣጠሩት ባለመቻላቸው አደጋው መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡

  የአደጋው ምርመራ ቡድን በአደጋው ወቅት አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር የሚያስቸግረውን የአውሮፕላኑን የፊተኛው ጫፍ ወይም አፍንጫ የመደፈቅ ችግር የተለየ በመሆኑ፣ አምራቹ በበረራ ወቅት አውሮፕላኑን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የበረራ ቁጥጥር ሥርዓቱን እንዲፈትሸው ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ አምራቹ አደጋው የደረሰበትን አውሮፕላን ወደ በረራ ከመመለሱ በፊት የሚመለከታቸው የአቪዬሽን ባለሥልጣናትና ተቋማት ችግሩን የሚያስወግድ የበረራ ቁጥጥር ሥርዓት በበቂ ሁኔታ መዘርጋቱን ሊያረጋግጡ ይገባል ብሏል፡፡

  ቦይንግ 737-8 ማክስ አውሮፕላን መሠረታዊ የንድፍ ችግር እንዳለበት የሚገልጹ የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ቦይንግ የዲዛይን ችግሩን ለማስተካከል ብሎ በሚስጥር ያስጫነው ኤምካስ የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር አውሮፕላኑን ለአደጋ እንዳጋለጠው ያስረዳሉ፡፡ የቦይንግ ኩባንያ የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌሩን አስመልክቶ ለደንበኞቹ በቂ መረጃ አለመስጠቱ፣ የላየን ኤር አደጋ ባለፈው ጥቅምት ወር ከተከሰተ በኋላ እንኳ አስፈላጊውን የማስተካከያ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ሊደገም እንደቻለ ይገልጻሉ፡፡

  የፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን እንዴት ችግር ያለበት የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያ የብቃት ማረጋገጫ ሊሰጥ ቻለ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱት የአቪዬሽን ባለሙያዎች፣ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን የብቃት ማረጋገጥ ሥራውን ራሱ ቦይንግ እንዲያከናውን ፈቅዷል በማለት ይወነጅሉታል፡፡ በፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽንና በቦይንግ ኩባንያ መካከል ተገቢ ያልሆነ ግንኙነት እንደተፈጠረ በመግለጽ፣ የሥራ ግንኙነታቸው በአግባቡ እንዲጠና ይጠይቃሉ፡፡

  የአሜሪካ ፍትሕ ዲፓርትመንት የማክስ አውሮፕላን ንድፍ፣ ምርትና የብቃት ማረጋገጫ ሒደት ላይ የወንጀል ምርመራ ሥራ እንደጀመረ ይታወቃል፡፡ የትራንስፖርት ዲፓርትመንት በማክስ አውሮፕላን የበረራ ደኅንነት ላይ ገለልተኛ ምርመራ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች