Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹በዚህች ከተማ የፖለቲካና የሞራል ሕጋዊ የሕዝብ ውክልና ያለን እኛ ብቻ ነን›› ...

‹‹በዚህች ከተማ የፖለቲካና የሞራል ሕጋዊ የሕዝብ ውክልና ያለን እኛ ብቻ ነን›› እስክንድር ነጋ፣ የባለ አደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ሰብሳቢ

ቀን:

‹‹ተጨባጭ የፀጥታ ችግር በመኖሩ መግለጫው እንዲቋረጥ ተደርጓል››

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በቤተ መንግሥት ጡረተኞች አክሲዮን ማኅበር አዳራሽ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ፣ የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለ አደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) መቋቋሙንና ለእሱና ለጓደኞቹ ከሕዝብ ውክልና እንደተሰጣቸው የሚናገረው የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ፣ ‹‹ቤተ መንግሥት የምንገባው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሳይሆን የሕዝብ ጥያቄ ይዘን ነው፤›› አለ፡፡ ለዚህም የከተማው ሕዝብ የፖለቲካና የሞራል ውክልና ያለው ያቋቋሙት ምክር ቤት ብቻ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

ጋዜጠኛ እስክንድር ይኼን የተናገረው መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ለጋዜጠኞች ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ስለመከልከሉና መግለጫውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መስጠት እንደሚችሉ ስለመገለጹ፣ ያለውን አስተያየት ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ነው፡፡

‹‹እኛ የሕዝብ ድምፅ ነን፡፡ ከቤተ መንግሥት ውጪም ነን፡፡ ቤታችንም ከቤተ መንግሥት ውጪ ነው፡፡ ወደ ቤተ መንግሥት ከገባን የሕዝብ ጥያቄ ይዘን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት አንገባም፤›› ብሏል፡፡

መግለጫ መስጠት ካለባቸው የሚሰጡት በሕዝብ መሀል ሆነው እንጂ፣ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብተው መሆን ስለሌለበት ወደፊትም ቢሆን በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ሆነው እንደማይሰጡ እስክንድር አስረድቷል፡፡ ቀደም ብለው የነበሩት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት (ሕወሓቶች) እንኳን ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫ ከልክለው እንደማያውቁ የተናገረው እስክንድር፣ ይኼ አካሄድ ሊታረም እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

መጋቢት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በራስ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዴት እንደተከለከለ ያስረዳው እስክንድር፣ ቀደም ባሉት ቀናት የአዳራሽ ኪራይ ከፍለው በማኅበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ መንገዶች ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ጥሪ ተላልፏል ብሏል፡፡ መግለጫ ከሚሰጥበት አንድ ቀን በፊት መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. የራስ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ደውለው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ መምርያ ኃላፊና ምክትላቸው፣ ወደ ሆቴሉ መጥተው መግለጫው መከልከሉ እንደተነገራቸው እንደገለጹለት ተናግሯል፡፡ ይኼም የተደረገው በራሳቸው በመምርያ ኃላፊዎቹ ሳይሆን ከበላይ ኃላፊዎች ተነግሯቸው መሆኑን ኃላፊዎቹ እንደነገሯቸው እንዳስረዱት አክሏል፡፡

በዚህ በለውጥ ድባብ ውስጥ ተሁኖ ክልከላ ተደርጓል መባሉ ስላላሳመናቸው፣ እስክንድርና የቅርብ ጓደኞቹ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደውለው አንድ የሚኒስትሩን አማካሪ ሲያናግሯቸው፣ ‹‹ይኼማ ሊሆን አይችልም፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫ አይከለከልም፡፡ በትዕግሥት ጠብቁ ጋዜጣዊ መግለጫውን ትሰጣላችሁ፤›› በማለት ስልኩን ዘግተው፣ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መልሰው እንደ ደወሉላቸው ገልጿል፡፡ መልሰው ደውለውም የአንድ የከተማ አስተዳደሩን ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ኃላፊ ስልክ እንደሰጧቸው አክሏል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባል ሲደውሉላቸው እሳቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ‹‹ልትከለከሉ አይገባም፤›› በማለት የኢዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርን ስልክ እንደሰጧቸው እስክንድር ተናግሯል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው በቦታው የተገኙ ጋዜጠኞችን ለመመለስ ባሉበት ሆነው ለመንገር ቢፈልጉም፣ ፖሊሶች ‹‹አይቻልም›› በማለት በመጠኑ ገፍተው እንደመለሷቸው ጠቁሟል፡፡ ከራስ ሆቴል በስተጀርባ ከሚገኘው ለገሃርና አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ኃላፊውን ሲያነጋግሯቸው፣ ከቂርቆስ ፖሊስ መምርያ ትዕዛዝ ስለተሰጠ ሄዴው እነሱን እንዲያነጋግሩ መኖራቸውን አረጋግጠው እንደላኳቸው እስክንድር አስረድቷል፡፡

የተከለከሉበትን ምክንያት ማወቅና ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ከብሔራዊ እስከ ካዛንቺስ በደቂቃዎች ቢደርሱም፣ መኖራቸውን ገልጸው የነበሩት የፖሊስ መምርያው ኃላፊዎች ቢሯቸውን ዘግተው መሰወራቸውን አክሏል፡፡

በራስ ሆቴል አካባቢ የተሰማሩት የፖሊስ አባላት፣ ‹‹ከእናንተ ጋር በተገናኘ ሴራ መጠንሰሱን ደኅንነት ስለደረሰበት ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳይሰጥ ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል፤›› እንዳሉት የሚናገረው እስክንድር፣ ‹‹እዚህ ላይ ጥያቄ አለኝ፤›› ይላል፡፡ ‹‹ሴራ አለ የተባለው ምን ያህል ታማኝነት አለው? ሴራ አለ ከተባለ ዛሬ እዚህ (በቢሮው) ችግሩ ለምን አልተከሰተም? አንድ ዜጋ ለሕይወቱ የሚያሠጋው ሴራ ከተጠነሰሰበት ፖሊስ ሥራው ምንድነው? ለምን እኔ እንድጠነቀቅ አልተነገረኝም? ፖሊስ ይኼንን የማድረግ የሕግ ግዴታ እንዳለበት አያውቅም?›› የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ፣ ፖሊስ እያወቀ ዝም ብሎ ጥቃት ቢደርስ በሕግ ተጠያቂ መሆኑን አስረድቷል፡፡ እውነትም ሴራው ካለ የፖሊስ ሥራ በሕግም በሞራልም እንደማያስኬድም አክሏል፡፡

አንድ ሰው ሕይወቱ አደጋ ላይ መሆኑ እየታወቀ ዝም እንደማይባል የተናገረው እስክንድር፣ ‹‹እውነተኛ ሴራ ቢኖር ኖሮ ያለመስማማታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ሊያስጠነቅቋቸው ይችሉ ነበር፤›› ብሏል፡፡

አብዛኛዎቹ የባለአደራ ምክር ቤቱ አባላት ላለፉት ሰባትና ስምንት ወራት ከማስፈራራት በተጨማሪ፣ ‹‹እንገላችኋለን፣ እንቆራርጣችኋለን . . . ›› እየተባሉ የከረሙበት ስለሆነ፣ መቶ በመቶ ሴራ አይኖርም ለማለት ባይቻልም ከጋዜጣዊው መግለጫ ጋር በተያያዘ ግን ያንን ያህል ሴራ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ እንደሌለው ጠቁሟል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫው በዋናነት በአዲስ አበባ ከሚኖሩ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ፣ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ውክልና የሰጣቸውን በአሥር ሺዎች የሚቆጠር ነዋሪ ያስተላለፈውን የአቋም መግለጫ ለሕዝብ ለማስተላለፍ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ ከተላለፉት የአቋም መግለጫዎች በዋናነት የሚጠቀሱትም በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል ሊደረግ ስለታሰበው የወሰን አከላለል ድርድር፣ ከሁለቱም በኩል በሕዝብ የተመረጡ አስተዳደሮች እስከሚሰየሙ እንዲቆም መሆኑን አስረድቷል፡፡ ሌላው ደግሞ የከተሞችን የብሔር ስብጥር በሚመለከት የተጀመረው የሠፈራ መርሐ ግብር፣ በሕዝብ የተመረጡ መስተዳድሮች እስከሚሰየሙ እንዲቆም የሚል መሆኑንና ይኼንንም የአቋም መግለጫ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ማድረሳቸውን መሆኑን አስታውቋል፡፡

መሥርተናል ስለሚሉት ባለ አደራ ምክር ቤት ሕጋዊነት የተጠየቀው እስክንድር እንዳስረዳው፣ ሦስት ዓይነት ሕጋዊነቶች አሉ፡፡ የፖለቲካ፣ የሞራልና የአስተዳደር ሕጋዊነት ናቸው፡፡ እነሱ የፖለቲካና የሞራል ሕጋዊነት እንዳላቸው ሲገልጽ፣ ‹‹በዚህች ከተማ የፖለቲካና የሞራል ሕጋዊ የሕዝብ ውክልና ያለን እኛ ብቻ ነን፤›› ብሏል፡፡ ብዙ አይደለም በሚለው ቢስማማም ከሰባት ሚሊዮን የአዲስ አበባ ሕዝብ የአሥር ሺዎች ውክልና ያላቸው እነሱ ብቻ መሆናቸውን ደጋግሞ አስረድቷል፡፡ ‹‹ይኼ ውክልና የአዲስ አበባ ከንቲባና አስተዳደር የላቸውም፤›› ብሏል፡፡

አስተዳደራዊ ሕጋዊነትን በሚመለከት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ስላልወጣ (ኅትመት በገባንበት ጊዜ ታትሞ ወጥቷል) እየተጠባበቁ መሆኑን፣ እስከ ዛሬ ድረስ ግን እንደማንኛቸው የሲቪክ ማኅበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግሯል፡፡ እንኳን እነሱና አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ሌሎችም ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገና ሕጋዊ እንዳልሆኑ ጠቁሞ ነገር ግን ሠልፍ፣ ስብሰባና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ስለሆነ የእነሱን ልዩ የሚያደርገው ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡

‹ምክር ቤት ነን፣ ባለ አደራ ነን› እየተባለ አላስፈላጊ ነገር ከሚያደርጉ ጋር ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለሰጡት ማስጠንቀቂ የተጠየቀው እስክንድር በሰጠው ምላሽ እንደገለጸው፣ እነሱ ሕዝብ የሰጣቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ቃል ኪዳን ማፍረስ አይፈልጉም፡፡ ‹‹ቃል ኪዳኑን ማፍረስ ሕዝቡን መክዳት ነው፡፡ ለጦርነት መልሳችን ጦርነት አይደለም፡፡ ዱላና ገጀራ ላነሳብንም መልሳችን ዱላና ገጀራ ማንሳት አይደለም፡፡ ለሁሉም ነገር ምላሻችን ሰላማዊና ሕጋዊ ሐሳብን በሐሳብ መግለጽ ብቻ ነው፤›› ብሏል፡፡ የሐሳብ ጦርነትና ፍትጊያ ከሆነ ግን ለመነጋገርና የሐሳብ ፍጭት ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

እነ እስክንድር ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጡ መከልከላቸውን በሚመለከት አስተያየታቸውን የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለጹት፣ መግለጫው እንዳይሰጥ መደረጉ ትክክል አይደለም፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባን በሚመለከት የተለያዩ ሐሳቦችና እንቅስቃሴዎች በመኖራቸው፣ ተጨባጭ ሥጋት መኖሩና ውጤቱም ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል በፖሊስ ስለተደረሰበት እንዲቋረጥ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ ወደፊት ከእስክንድር ጋር በመነጋገር ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚዘጋጅም አክለዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...