Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአገሪቱ ባንኮች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የአምስት ሚሊዮን ብር እራት እንዲያዋጡ ብሔራዊ ባንክ ጠየቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመጪው ግንቦት ወር ለሚያዘጋጁትና በሳህን አምስት ሚሊዮን ብር ለሚያስከፍለው እራት፣ ሁሉም የአገሪቱ ባንኮች እንዲያዋጡ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቀረበ፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፈለት ደብዳቤ የፋይናንስ ተቋማት ለሸገር ማስዋቢያ ፕሮጀክት የተሳትፎ መዋጮአቸውን ገቢ እንዲያደርጉ መጠየቁን ገልጿል፡፡ እያንዳንዱ ባንክም በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በኩል ለፕሮጀክቱ ለማዋጣት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጾ፣ ሁሉም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ በተከፈተው ሒሳብ በኩል መዋጮአቸውን ገቢ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ሁሉም ባንኮች እያንዳንዳቸው ለእራቱ የአምስት ሚሊዮን ብር እንዲያዋጡ መጠየቁ በፋይናንስ ተቋማት ጥያቄ የፈጠረ ሲሆን፣ በቅርቡ የባንኮች ማኅበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት ለተጀመረው ለዚሁ ፕሮጀክት ከ2010 የሒሳብ ዓመት የተጣራ ትርፋቸው 1.5 በመቶውን በማስላት እንዲያዋጡ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህም ባለፈ የባንኮች ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አነሳሽነት በአምቦ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም ካለፈው ዓመት የተጣራ ትርፋቸው 0.5 በመቶ፣ እንዲሁም ከተለያዩ ሥፍራዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች በተመሳሳይ ካለፈው ዓመት ትርፋቸው 0.5 በመቶ እንዲያዋጡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ ከልማት ባንክ በስተቀር በአገሪቱ ያሉ ባንኮች ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ያዋጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፋይናንስ ተቋማቱም ጥያቄ ያነሱት ለሦስቱ ፕሮጀክቶች ከሚያዋጡት በተጨማሪ ለእራት ግብዣው ብሔራዊ ባንክ አዋጡ በማለቱ ነው፡፡

  በቅርቡም የሰባት ባንኮች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚሳተፉበት የባንኮች የዳይሬክተሮች የምክክር መድረክ፣ የባንኮች ማኅበር ለሦስቱ ፕሮጀክቶች እንዲያዋጡ የጠየቀበት መንገድ ሕጋዊ ሥርዓት መከተል እንዳለበት ተጠይቋል፡፡ የምክክር መድረኩ አባላት ለባንኮች ማኅበር በጻፉት ደብዳቤም፣ ማኅበሩ በደብዳቤ ባንኮች ለሦስቱ ፕሮጀክቶች የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲያዋጡ ሐሳብ ያቀረበበት ሒደትና ውሳኔ፣ ሕግን ያልተከተለና ማኅበሩ ከተሰጠው ገደብ ያለፈ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ የምክክር መድረኩ ደብዳቤ አክሎም የባንኮች ማኅበር ያቀረበው የገንዘብ ድጋፍ እያንዳንዱ ባንክ በየቦርዱ ጥያቄው ቀርቦለት እንደ አቅሙና አስተዳደራዊ ሁኔታው ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠቁሟል፡፡

  የገንዘብ ድጋፍ የተጠየቀባቸው ፕሮጀክቶችም ቀደም ብለው በጀት እንዲያዝላቸው የቀረቡ ባለመሆናቸው በጉዳዩ ላይ መምከር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ ውሳኔ መገኘት እንዳለበትም የምክክር መድረኩ ገልጿል፡፡

  ብሔራዊ ባንክ ለሁሉም ባንኮች የጻፈውን ደብዳቤ አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ ለማናገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች