Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልወንዘ ዓባይ

ወንዘ ዓባይ

ቀን:

. . . ያዲሱ ትውልዳችን አስተሳሰብና ዝንባሌ እጅግ ደርቆ የገረረም ባይሆን፣ እርጥብ አይደለም፡፡ እንደ ዓባይ ያሉ የዓለሙ ቤተ ውኃዎች፣ ቀስ በቀስ የሞት አፍንጫ እያሸተቱ (ውኃቸው እያነሰ) እንደመጡ፣ ግንዛቤ አለው፡፡ በኤፍራጥስና በጤግሮስ ጭን ሥር ተሞላቃ ያደገችው ባቢሎን፣ በሥልጣኔ አብባ እንደ ነበር፣ ከታሪክ አንብቧል፡፡ የውኃ ማሕፀኖች ሥልጣኔን ሊወልዱ እንደሚችሉ ጠርጥሯል፡፡ ታድያንን የራሱ ዓባይ ዥረት ዝንተ ዓለም እየዘፈነና እያቅራራ፣ ደንኑና አረሁን ጥሶ ወደ ቆላ ሲወርድ ዝም ብሎ ማየት የሚዋጥለት አይሆንም፡፡ ስለሆነም ‹‹መላ-በሉ›› ማለቱ አልቀረም፡፡ የ‹‹እናስቀረው-ያጣላል››ም ዚቅ፣ ሳይገባው አልቀረም፡፡ ‹‹ሰላም እንዳይኖረን›› ካረጉን ምክንያቶችም አንዱ ነው ይል ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ፣ ‹‹አገር ያፈራውን ሲሳይ፣ የአገሩ ዜጋ የማይጠቀምበት ከሆነ፣ የአገር ሕዝብነት ትርጉም ምንድን ነው?›› ብሎም ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ‹‹ውኃችን አፈር ይዞ እንዳይሄድ ወንፊት ይዤ ልቅረብም›› ይል ይሆናል፡፡ . . .

‹‹የምድሪቱን ፀጋ፣ ውኃን ሆነ ዓየራት፣

ሣር ቅጠሉን ሳይቀር፣ ማዕድን እፀዋት፣

- Advertisement -

መጠቀም እንድችል፣ በጋራ በኅብረት፣

ኧረ ሰዎች በሉ፣ ድረስ ነፊ ወንፊት፣

አገሩ ተዝቆ፣ ተንዶ ሳይሸፍት፣

ዶማና አካፋ፣ ያ ዓባይ ሆኖበት፣

እንደቡልዶዘርም፣ ነድሎ ገፎ ወስዶት፣

ራቁቱን ሳይቀር፣ ዓባይ ተወን በሉት!

አገር ባዶ ሳይሆን፣ አፈር አልባ ግተት

አፈሩን ማጋዙን፣ ቢተወው ምናልባት!!

አንድ ልዩ ዘዴ፣ መፈጠር አለበት! . . .›› እያለ የሚዘፍነውም፣ የዓባይ ዋልጌነት ቀስቅሶት ይሆናል፡፡ ከሌሎች አስተያየቶቹ ሁሉ፣ ይህን ሐሳቡን በሚገባ ሊያስተናግዱለት ይገባል፡፡ በጋርዮሽ ለመጠቀም የሚያስችል ዘዴ! . . . በርግጥ ይኸኛው አስተያየት ጥሩ አማራጭና አመርቂነትም ያለው ነው፡፡

ከሠላሳ ዓመታት በፊት በብዕር ስሙ ገሞራው ተብሎ የሚታወቀው ባለቅኔው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ በኖረበትና ባረፈበት በስዊድን መዲና ስቶክሆልም ባሳተመው ‹‹እናትክን!›› በሉልኝ! በተሰኘው መጽሐፉ ያሰፈረው ኃይለ ቃል ነው፡፡

ገሞራው በስደት ዓለም ውስጥ ሆኖ ለኢትዮጵያ ያልበጀውን ለባዕዳን ስለጠቀመው ዓባይ ወንዝ እንዴት እንዴት ሲል አንጎራጉሯል፡፡ የውኃ ጥማት ለፈጀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሮሮአዊ ስንክሳር ነበር በመጽሐፉ መክተቡን ያስገነዘበው፡፡

ሕዝበ ኢትዮጵያ ‹‹ውኃችን አፈር ይዞ እንዳይሄድ ወንፊት ይዤ ልቅረብም›› ይል ይሆናል ብሎ የተነበየውን ከ22 ዓመታት በኋላ እርሱ በሕይወት እያለ ዕውን የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በጉባ የመሠረት ድንጋይ መጣሉና ሥራው መጀመሩ ነው፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ‹‹የሚሌኒየም ግድብ›› በሚል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካይነት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የግድቡ ሥራ ስምንተኛ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡

በክብረ በዓሉ አጋጣሚ የወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው የግድቡ ፕሮጀክት ክንዋኔ 66 በመቶ ደርሷል፡፡ ኤፍቢሲ እንደዘገበው፣ በአሁኑ ወቅትህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አካል የሆነውና ግድቡ የሚያስፈልገውን 74 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ለመያዝ የሚያስችለው ኮርቻ ግድብ ግንባታ 95 በመቶ ሲጠናቀቅ፣ 174 ሜትር ከፍታ ያለውና የግድቡ ግራ ክፍል የሆነው ግንባታም ተፈጽሟል፡፡

እንደዘገባው፣ ለግድቡ በአጠቃላይ 16 ተርባይኖች የሚገጠሙለት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የሁለት ተርባይኖች ገጠማ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች ከሁለት ዓመት በኋላ 750 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዓባይ-ናይል

ገሞራው፣ ለመሆኑ ፈለገ-ዓባይ ወይም ሪቨር ናይል፣ ምን ያህል በታሪክ የታወቀ ወንዝ ነው? በሺሕ ዘመናት በሚቆጠር የህላዌ ዕድሜው ምን ዓይነት ጠቀሜታ አበርክቷል? ባለበት ክፍለ ዓለም ውስጥስ በመከሰቱ፣ ምን ዓይነት ጣጣ አስከትሏል? ዛሬስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ብለው ጠይቀው ስለ ዓባይ ማንነት ፈልቅቀው በማውጣት እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡

ከጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ ኔይሎስ ከሚለው ቃል ስሙን እንዳገኘ ሊቃውንት ይተርካሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከላቲን ቋንቋ ኒሉስ ከሚል ቃል የተገኘ ነው ይላሉ፡፡ ከግሪኩም ይሁን ከላቲኑ፣ ይህ ታላቅ አፍሪቃዊ ወንዝ ናይል የሚል ስያሜ እንደያዘ ለዘመናት ነበረ፣ አለ፣ ይኖራልም፡፡ በዓለም ያሳወቀው ሌላ ባሕርዩ ሳይሆን በቁመተ-ረዥምነቱ የዓለምን ታላላቅ ወንዞች ሁሉ ስለሚያስከነዳ ነው፡፡ ከመንታ ቦታዎች ምንጮች ተነስቶ፣ አራት ሰፋፊ አኅጉራትን አቆራርጦ ማደርያ ቤቱ በሆነው የሜዲቴራንያን ባሕር እስኪደርስ ድረስ፣ 6,690 ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዝ ማራቶናዊ ወንዝ ነው፡፡ ሜዲቴራንያን ባሕር ከመድረሱ በፊት፣ በተለይ ለሁለት ታላላቅ አገሮች-ነብያና ምስር (ሱዳንና ግብፅ) ከፍተኛ የሲሳይ ድልብ አቅራቢ ሆኖ በቅንነት ሲያገለግል መኖሩ ይነገርለታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው ‹‹ጥንታዊው የምድረ ግብፅ ሥልጣኔ ያለ ዓባይ (ናይል) ወንዝ ጭራሽ አይታሰብም›› እየተባለ በየታሪኩ ገጾች የተመዘገበው፡፡ ምናልባትም በባሕረ-ሜዲቴራንያን አካባቢ በመሥረጉ፣ አውሮፓንና መካከለኛ ምሥራቅን እያጣቀሰ፣ ካሮፓ ጣልያንን ከመካከለኛው ምሥራቅ ቱርክን ኮርኩሮ፣ በባለምንጮቹ አገሮች ላይ፣ ወስፈንጥር ሲቀስት ያስኖረው!!

ናይል የሚለው ቃል የሁለቱ አፍሪቃውያን ወንዞች የወል ስም ነው፡፡ አንደኛው ናይል ነጭ ናይል የሚለው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ዓባይ ብለን የምንጠራው ሰማያዊ ናይል (ጥቁር ናይል) ነው፡፡ ነጭ ናይል ካኔራ የሚባል ወንዝ ከሚመነጭበት ቦታ ፈልቆ፣ የቪክቶሪያን ሐይቅ ቆርጦ ሲመጣ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከጣና ሐይቅ አጠገብ ከሚገኝ አንድ ምንጭ ፈልቆ፣ ሐይቀ ጣናን ሰንጥቆ፣ የሚውዘገዘገው ዓባይ ወንዝ ካርቱም ከተማ ላይ፣ ወንድሙን ነጭ ዓባይ ያገኘዋል፡፡

ስመ ገናናው ዓባይ ለሥልጣኔ፣ ለባህል፣ ለእምነት ታላቅ ምንጭና ብሔራዊ ኩራት ለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩባትን ኤዶም ገነት ከከበቡት ዓበይት አፍላጋት (ታላላቅ ወንዞች) አንዱ ዓባይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን አፈታሪክ በአርኪዮሎጂና በአንትሮፖሎጂ ጥናትም መደገፉም ይነገራል፡፡

አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ «ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት» ዓባይን እንዲህ ይፈቱታል፡፡ «አባትያ፣ የወንዞች አባት ከአራቱ ወንዞች አንደኛው መዥመሪያው ወንዝ ታላቅ ዠማ፣ በግእዝ አዋልድ ፈለግ አባዊ ይባላል፡፡ እሱም በዳሞት ሰኮላ ሚካኤል ከሚባል አገር ከደንገዛ ተራራ ሥር ፈልቆ ጐዣምን ይከባል፣ ምንጩም ግሼ ዓባይ ይባላል፤ በጣና ላይ ዐልፎ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ምስር [ግብፅ] ይኼዳል፡፡ ፈሳሹም ሰማይ መስሎ ስለሚታይ ጥቁር ዓባይ ይሉታል፡፡»

ገነትን የሚከቡት ወንዞች በምሥራቅ ኤፍራጥስና ጤግሮስ፣ በምዕራብ ኤፌሶንና ግዮን መሆናቸው በድርሳናት ተጽፏል፡፡ ግዮን ጥቁር ዓባይ ነው የሚሉ ቢኖሩም እንደ አለቃ ደስታ አገላለጽ ዓባይን ኤፌሶን ሲሉት በደቡባዊ አፍሪቃ አካባቢ ኒያንዛ ከሚባል ሐይቅ የሚወጣው ነጭ ዓባይን ግዮን ብለው ይጠሩታል፡፡

በውጮች ዘንድ የኢትዮጵያ ዓባይ ከጣና ሐይቅ የሚነሣውን ብሉ ናይል ከማዕከላዊ አፍሪካ የታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የሚወጣውን ኋይት ናይል ሲሉት ሁለቱ ወንዞች ሱዳን ካርቱም ተገናኝተው ወደ ግብፅ በሚያደርጉት ጉዞ ናይል በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ፡፡ ከግሪክ ኒሎስ የተገኘው ናይል ፍችውየወንዝ ሸለቆ ማለት ነው፡፡

ለግብፃውያን ዓባይ ሕይወታቸውም መሠረታቸውም ነው፡፡ በጥንታዊው ታሪክ ጸሐፊ ሔሮዶቱስ እንደተገለጸው «ግብፅ የዓባይ ስጦታ» በመባል ትታወቃለች፡፡ በጥንታውያን ግብፃውያን ውኃ ኡዋት (Uat) ተብሎ ሲጠራ፣ ፍችውም አረንጓዴ ማለት ነው፡፡ ውኃና አረንጓዴ ተመሳሳይነት እንዳላቸውና የነፍስ መገለጫም እንደሆነ በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ ሊዶር ከሮቭኪን፣ የጥንቱ ዓለም ታሪክ ባሉት ጽሐፋቸው፣ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ከየት እንደሚመነጭ ባለማወቃቸው የዓባይ አምላክ ከሰማይ በባልዲ እየቀዳ ቁልቁል ወደ መሬት እንደሚያንቆረቆርላቸውና የጐርፍ ማጥለቅለቅ የሚያጋጥመውም የሚንቆረቆርላቸው የውኃ መጠን ሲጨምር እንደሆነ ያምኑ ነበር፡፡ በመሆኑም ማሳቸውን ያለመልምላቸውና ሕይወታቸውን ይጠብቅላቸው ዘንድ ዓባይን ዘወትር ይማፀኑት፣ ምስጋናቸውን ይዘምሩለትና ውዳሴያቸውን ያቅራሩለት ነበር፡፡ ለዓባይ ወንዝ ይዘመር ከነበረው መዝሙር ከፊሉ እነሆ!

ለግብፅ ተሐድሶ ልትሰጥ ለመጣኸው ዓባይ፣

ክብርና ምስጋና ይገባሃል፣

ስትዘገይብን ሕይወት ሁሉ ቀጥ ይላል፣

ስትቆጣ ነጐድጓድ ያስገመግማል፡፡

ዓባይ ከተፍ ሲል መሬት በደስታ ትፈካለች፣

ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ በፍሥሐ ይፈነድቃሉ፡፡

የተትረፈረፈ ሲሳይ የምትመግበን አንተው ነህ፣

የተዋቡ ነገሮችን ሁሉ ታቀርብልናለህ፣

ወጣቶችና ሕፃናት በደስታ እየዘመሩ፣

ንጉሣችን ዓባይ እንኳን ደህና መጣህ ይሉሃል፡፡

ትንሣኤ ያገኘው የዓባይ አምላክ አፈታሪክ ከዓባይ ጋር የተያያዘ ወግ አለው፡፡ በግብፅ በበጋ ወራት ሞቃት ነፋስ ለሃምሳ ቀናት ያለማቋረጥ እየነፈሰ አካባቢውን ሁሉ ድርቅና ቸነፈር ያላብሰዋል፡፡ ተፈጥሮ ቀጥ ፀጥና ለጥ ያለች ትመስላለች፡፡ ከዚያ በኋላ ከባሕሩ የሚነፍሰው ቀዝቃዛ አየርና የዓባይ ጎርፍ ለአካባቢው አዲስ ሕይወትና ብሩህ እፎይታ ይለግሳሉ፡፡ ተፈጥሮ ትንሣኤ እንዳገኘች ሁሉ ዳግም ሕያው ትሆናለች፡፡

ዓባይና ኢትዮጵያ

ዓባይ ከኢትዮጵያውያን ሕይወት ጋር ጥልቅ ትስስር አለው፡፡ በተለይ የታላቁ ወንዝ መጋቢ በሆኑት አካባቢዎች የሚኖረው ኅብረተሰብ ከእምነቱ ጋር የሚያያይዘው ብዙ ነገር አለው፡፡ ለዓባይ የንግሥ በዓል ሁሉ የሚያደርጉለት አሉ፡፡ ከተረትና ምሳሌ ጋር አቆራኝተው ሕይወታቸውንም ይገልጹበታል፡፡ ይሔሱበታልም፡፡ በአረንጓዴው ዘመቻ ወቅት «ምድሪቱን አረንጓዴ እናለብሳታለን» የሚለውን አብዮታዊ ጥሪ የሰማ አንድ ገበሬ «አንተ የአገሬ ውሃ አረንጓዴ አትልበስ፤

እጠጣህ ይሆናል ምናልባት ስመለስ» ብሎ መግጠሙ ይነገራል፡፡

ከዓባይ ጋር የተያያዙ ምሳሌያዊ አነጋገሮች፣ ዘይቤዎች አያሌ ናቸው፤ ኑሮን ይገልጣሉ፡፡ «ውኃ ቀለብ ሆኖ ሰውን ካሳደረ፣

ዓባይና ጣና አገሬ ነበረ፡፡» የኢትዮጵያን ዓባይ ከነጭ ዓባይ ለመለየት ዓባይ ጣና ተብሎ ይጠራል፡፡ የዓሳ ማኅደር ስለሆነችው ጣና፣ ድምፀ መረዋው አሰፋ አባተ፡-

 «ዓሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፣

ዶሮ መረቅማ ከወዴት አባቴ» ብሎ ያንጎራጎረው ይጠቀሳል፡፡

ሌላው ድምፃዊውም ፀሐይ ዮሐንስም ወዳጁ ያለችበት ስፍራ ዓባይ ዳርቻ መሆኑን የሚያጠይቅበት ሥራው በብዙዎች ልቡና ውስጥ አለ፡፡

«ዓባይ ነው አሉኝ ቤቷ

ዓባይ ነው አሉኝ

ልጫን ፈረሴን እኔን

ልቤ ዕረፍት ያግኝ»

ስለዓባይ በተረትና ምሳሌ ከተነገሩት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

«ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፡፡

ዓባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል፡፡

የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው፡፡

ዓባይ የተጸውዖ ስም ኾኖ ለሁለቱ ጾታ ያገለግላል፡፡ ዓባይነህ፣ ዓባይነሽ፣ ዓባይ ጋረደሽ ወዘተ. በዘይቤ ደረጃም ዓባይን በዋና የሚያቋርጥ በዓባይ ላይ የሚንፈላሰስን ለመግለጽ ዓባይ መስኩ ይሉታል፡፡

ዓባይና ጣና ለጥበብ ንሸጣ ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆኑ በምድራችን በሰውነት ኅልው ሆነው የኖሩት የአለቃ ገብረ ሐና አንዱ ጥበባዊ ሥራ ማሳያ ይሆናል፡፡

አለቃ ገብረ ሐና ለያሬዳዊው ማሕሌት ማጀቢያ ያደራጁትንና በልጃቸው የሰየሙት የተክሌ አቋቋም የሚሰኘው የአቋቋም ሥርዓት የፈጠሩት ዓባይ ጣና ሐይቅ ዳርቻ ተተክለው ከነበሩት የሸምበቆ ተክሎች ከውኃው ውስጥ ሲወዛወዙ በማየታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዓባይ ጋር የተያያዘ ጥንታዊነትንና መሠረታዊ ሕይወትን የተነተነ ግጥም ካቀረቡት  ለቅኔዎች መካከል ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ይጠቀሳሉ፡፡

«ዓባይ የምድር ዓለም ሲሳይ

የቅድመጠቢባን አዋይ

ዓባይ የጥቁር ዘር ብሥራት

የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት

የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ

ከጣና በር እስከ ካርናክ

በጡትሽ እቅፍ እንዲላክ

ለራህ ለፀሐዩ ግማድ፣ ለጣህ ለከዋክብት አምላክ

ከጥንተፍጠራን ጮራ የመነጨሽ ከኩሽ አብራክ፡፡»

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...