Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ለስኳር ኮርፖሬሽን ለውጭ ዕዳ መክፈያና ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 13 ቢሊዮን ብር ብድር እንዲሰጥ መንግሥት ጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለስኳር ኮርፖሬሽን የውጭ ዕዳ መክፈያና ያልተጠናቀቁ የስኳር ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል 13.1 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር እንዲያቀርብ፣ መንግሥት ዋስትና መስጠቱን በመግለጽ በዚሁ አግባብ እንዲፈጸም ጠየቀ።

 ከሳምንት በፊት በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካለኝ (ዶ/ር) ተፈርሞ በዋናነት ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ እንዲሁም በግልባጭ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ  ደብዳቤ ተልኳል፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን እየገነባቸው ከሚገኙት የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ጣና በለስ ቁጥር አንድና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ፣ በመንግሥት ልዩ አቅጣጫ መሰጠቱን ደብዳቤው ይገልጻል።

ስኳር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቶቹን ለማስፈጸምና ከውጭ ለተበደረው ብድር የወለድ ክፍያ የሚውል ገንዘብ በብድር ንግድ ባንክ ካላገኘ ግዴታውን መወጣት እንደማይችል በማሳወቁ፣ በመንግሥት ዋስትና ባንኩ አዲስ ብድር ለኮርፖሬሽኑ እንዲያቀርብ ይጠይቃል።

‹‹በመሆኑም ለጣና በለስ ቁጥር አንድና ለኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካዎች ቀሪ ግንባታና ለሌሎች የስኳር ልማት ሥራዎች የሚውል ብር 5.7 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለብድርና ወለድ መክፈያ ብር 7.4 ቢሊዮን ብር፣ በጠቅላላው 13.1 ቢሊዮን ብር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀመጠውን ጣሪያ የጠበቀ መሆኑ ተረጋግጦ እንዲሰጣቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ዋስትና የሰጠ መሆኑን እንገልጻለን፤›› ሲል የተላከው ደብዳቤ ጠይቋል።

ገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና ለመስጠት በጠየቀው መሠረትም ስኳር ኮርፖሬሽን ብድሩን ለማግኘት፣ በአሁኑ ወቅት ከባንኩ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ኮርፖሬሽኑ በገጠመው ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ምክንያት በአሁኑ ወቅት የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎቹ ከሞላ ጎደል መቆማቸው እየተነገረ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ከወራት በፊት ባካሄደው የመስክ ግምገማ፣ የኦሞ ቀጥር አንድና በለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች መቆማቸውንና ሠራተኞችም እንደተበተኑ አረጋግጧል።

ይኼንንና አጠቃላይ የስኳር ፕሮጀክቶች ችግሮችን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የኮርፖሬሽኑን አመራሮች በመጥራት ቋሚ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ፣ ግንባታዎቹን ለማከናወን የሚያስፈልገው ፋይናንስ ሊገኝ ባለመቻሉ ግንባታዎቹ መቆማቸውን ገልጾ ነበር።

ስኳር ኮርፖሬሽን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ከቻይና የልማት ባንክ ላገኘው ብድር የግዴታ ክፍያና ወለድ በአጠቃላይ 4.5 ሚሊዮን ዶላር በመክፈሉ፣ ባንኩ ብድሩን በመያዙ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ መቆሙን ገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የጀመረውን የስኳር ልማት ለማስፈጸም በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበትና በከፍተኛ የባንክ ዕዳ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም፣ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ማሳካት ሳይቻል ኮርፖሬሽኑ ቢወድቅ አደጋው በዚያ ብቻ እንደማያበቃና ብድር ያቀረቡ ባንኮችንም ጭምር ይዞ ሊወድቅ እንደሚችል፣ የኮርፖሬሽኑ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዋዩ ሮባ ለቋሚ ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት አሳስበዋል።

ኮርፖሬሽኑ ግዙፍ የስኳር ልማትና የፋብሪካ ግንባታዎችን በሁለት አካባቢዎች ከጀመረ አሥር ዓመታት ገደማ ተቆጥረዋል።

በርከት ያሉ ፋብሪካዎች ግንባታ የሚካሄደው በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን (ሰላማጎ እና ኛንጋቶም ወረዳዎች)፣ በቤንች ማጂ ዞን (ሱርማና ሜኢኒት ሻሻ ወረዳዎች) እና በካፋ ዞን (ዴቻ ወረዳ) የተመረጡ አካባቢዎች ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም የኦሞ ኩራዝ የስኳር ልማት ፕሮጀክት በመባል ይታወቃል።

ፕሮጀክቱ በ100 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ በሚለማ የሸንኮራ አገዳ ተጠቅመው በቀን 60 ሺሕ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያላቸው አራት ስኳር ፋብሪካዎች እየተገነቡ ነው፡፡ በሙሉ አቅማቸው ማምረት ሲጀምሩ ሦስቱ እያንዳንዳቸው በቀን 12 ሺሕ ቶን አገዳ በመፍጨት በዓመት 205 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር፣ እንዲሁም በዓመት 28 ሚሊዮን ሊትር ኤታኖል ያመርታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህ አራት ስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ በቻይና ኮምፕላንት ኩባንያ የተገነቡት የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለትና ቁጥር ሦስት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ገብተዋል፡፡ የተቀሩት ቁጥር አንድና አምስት ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው በገንዘብ ዕጦት ተቋርጧል።

 በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተገነቡ ለሚገኙ አራት ስኳር ፋብሪካዎች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ለካፒታል ኢንቨስትመንት ማለትም ለመስኖ መሠረተ ልማት፣ ለመሬት ዝግጅት፣ ለአገዳ ልማት፣ ለቤቶች ግንባታ፣ ለፋብሪካ ግንባታና ለፕሮጀክቶች ቅድመ ኦፕሬሽንና ለሥራ ማስኬጃ 34.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ መደረጉን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት፣ ኮርፖሬሽኑ የገባበትን ቀውስና ለዚህ ግንባር ቀደም መንስዔ የሆነው ሁሉንም ግንባታዎች እንዲያከናውን በዘርፉ ምንም ዓይነት ልምድ ለሌለው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ኮንትራት መሰጠቱ እንደሆነ በዝርዝር ማስረዳታቸው ይታወሳል።

በወቅቱ ባቀረቡት ዝርዝር ሪፖርት መሠረት ኩራዝ አንድ የተባለው ፋብሪካ ኮንትራት ውል የተገባው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ የውል ማሻሻያ ሰኔ 2004 ዓ.ም. ላይ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ይህ ፋብሪካ ዘንድሮም ገና 80 በመቶ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ ይገኛል።

 ሜቴክ ይህንን ፕሮጀክት በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም. አጠናቆ ማስረከብ ይጠበቅበት እንደነበር፣ ለዚህም ሲባል የፕሮጀክቱን 97 በመቶ ክፍያ ቀድሞ መውሰዱ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ይህ ፕሮጀክት በ2010 ዓ.ም. ከሜትክ የተነጠቀ ሲሆን፣ ከንግድ ባንክ ሰሞኑን የተጠየቀው አዲስ ብድር የዚህን ፕሮጀክት ቀሪ ግንባታ ለማከናወን ነው።

በተጠየቀው አዲስ ብድር ግንባታው እንዲጠናቀቅ የተፈለገው የበለስ ቁጥር አንድ ፋብሪካ ሲሆን፣ ይህንን ፋብሪካ ለመገንባት ከሜቴክ ጋር ውል የተፈጸመው በ2003 ዓ.ም. ቢሆንም፣ መጠናቀቅ የሚገባው በ2005 ዓ.ም. መጋቢት ወር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ዘንድሮም ይጠናቀቃል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን ሜቴክ ውሉን እንዲያቋርጥ ከመደረጉ አስቀድሞ ከአጠቃላይ ግንባታ ወጪው 94 በመቶ ክፍያ እንደተከፈለው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኮርፖሬሽኑ የተሰጠውን የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ከዚህ ቀደም የወሰደ ሲሆን፣ አሁን ከተጠየቀው ብድር አብላጫው ያለበትን ዕዳ ለመክፈል የሚውል ነው። የመንግሥት ዕቅድ የተጀመሩት የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች በመጀመርያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማገባደጃ (በ2007 ዓ.ም.) ተጠናቀው፣ የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ከመመለስ በተረፈ ከስኳር ምርት ኤክስፖርት በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ የሚል ነበር።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች