Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብረዋቸው የታሰሩ ተከሳሾች በዓቃቤ ሕግ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰሙ

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብረዋቸው የታሰሩ ተከሳሾች በዓቃቤ ሕግ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰሙ

ቀን:

በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በሌሎች የክልሉ ከተሞች በደረሱ የጅምላ ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ አስገድዶ መድፈር፣ በዘር ለይቶ ማጥቃት፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎ፣ ንብረት ማውደምና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ክስ የተመሠረተባቸው የክልሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ተከሳሾች፣ በዓቃቤ ሕግ ላይ ተቃውሞአቸውን አሰሙ፡፡

ተከሳሾቹ ዓርብ መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ተቃውሞአቸውን ያሰሙት፣ እነሱ በእስር ላይ መሆናቸውን እያወቀ በፌዴራል ፖሊስ በኩል መቅረብ ያለባቸውን ተከሳሾች በሚመለከት ተከታትሎ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ መግለጽ ሲገባው፣ ከተከሳሾች እኩል የፌዴራል ፖሊስ ያቀረበውን ምላሽ መስማቱን በሚመለከት ነው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሠረተባቸው 47 ተከሳሾች መካከል አቶ አብዲ መሐመድ፣ ወ/ሮ ራሀማ መሐመድ፣ አቶ አብዱረዛቅ ሳኒና አቶ ፈራሃን ጣሂርን ጨምሮ ስድስት ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹን 41 ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ በአድራሻቸው አፈላልጎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ነበር፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ መጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በላከው ደብዳቤ ተከሳሾቹን አፈላልጎ ለማቅረብ አለመቻሉን ገልጾ፣ በአድራሻቸው ተከታትሎና አፈላልጎ ለማቅረብ ረዘም ያለ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ፌዴራል ፖሊስ የት ሄዶና አፈላልጎ እንዳጣቸው አለመግለጹ በትጋት አለመሥራቱን አያመለክትም፡፡ በቀጣይ ቀጠሮ የት ቦታ ሄዶ እንደፈለገና እንዳጣቸው ማረጋገጫ ከክልሉ ይዞ እንዲቀርብ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡ የክልሉ ፖሊስም እንዲተባበርና ተፈላጊዎቹን አፈላልጎ በመያዝ አብሮ እንዲሠራ ትዕዛዝ እንዲሰጥለትም ጠይቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ የጻፈውን ደብዳቤና ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ የሰጠውን አስተያየት የሰሙት የተከሳሾች ጠበቆች፣ አስተያየት መስጠት የጀመሩት በተቃውሞ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ችሎት ትዕዛዝ ሲሰጥ በትጋት ሠርቶ እንዲያቀርብ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ማመልከታቸውን አስታውሰው፣ ያ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ያሳሰቡት ምላሹ አሁን የተሰማው እንደሚሆን በመገመታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠበቆቹ ዓቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የት እንደደረሰና ምን ውጤት እንደተገኘ በስልክና በአካል በመገኘት ማወቅ ሲገባው፣ እንደ ተከሳሽ እኩል በችሎት አስተያየት መስጠቱና የፖሊስን ሥራ መቃወሙ አስገራሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ተገቢም እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ደንበኞቻቸው ለረጅም ጊዜያት በእስር ላይ በመሆናቸው የዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ የማፈላለጊያ ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ፣ ያልቀረቡት ተከሳሾች በጋዜጣ እንዲጠሩ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ ዓቃቤ ሕግ የሰጠው አስተያየትና ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው መሆኑንና እንዳልተቀበለው በመግለጽ፣ ሥራውን የራሱ አድርጎ መከታተል እንዳለበት አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ፖሊስ ያለው በተሰጠው አድራሻ ተከሳሾችን ሊያገኛቸው ባለመቻሉ በቂ ጊዜ ተሰጥቶት አፈላልጎ እንዲያቀርብ በመሆኑ፣ በቀጣይ በትጋትና ከክልሉ ፖሊስ ጋር በትብብር በመሥራት፣ የደረሰበትን ውጤት በማስረጃ ጭምር እንዲያቀርብ በማሳሰብ ለሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...