Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር...

በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተከሰሱ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕጣ ካወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምክንያት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒቴርና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ክሱን የመሠረቱት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ክፍያን መቶ በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው፣ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የተስማሙ 14 ግለሰቦች ናቸው፡፡

ከሳሾቹ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት ክስ እንደሚያስረዳው፣ መንግሥት በ2005 ዓ.ም. ባቀረበው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መርሐ ግበር ተመዝጋቢዎች ናቸው፡፡ ለመርሐ ግብሩ ማስፈጸሚያ በወጣው መመርያ ቁጥር 21/2005 አንቀጽ 16 መሠረት፣ የቤቱን ሙሉ ክፍያ (መቶ በመቶ) የከፈለ ቅድሚያ እንደሚያገኝ መደንገጉን ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረጉት ውል አንቀጽ 2(6) ሥር እንደተገለጸው፣ ‹‹የቤት ድልድል ቅደም ተከተል በደንበኞች የቁጠባ መጠን ልክ፣ በምዝገባ ጊዜና በዕጣ ይሆናል፤›› በማለት፣ ለብድር ብቁ የሆኑና ከፍተኛ ገንዘብ የቆጠቡ ቅድሚያ እንደሚኖራቸው በግልጽ በውሉ ላይ መሥፈሩን አስታውሰዋል፡፡

በመመርያው አንቀጽ 15 እና 20 ሥር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ፣ በአንቀጽ 17 ሥር ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያላቸው ሚና መቀመጡን ከሳሾቹ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣ በማውጣት ማከፋፈል ሲገባው የከተማ አስተዳደሩ መመርያውን በመጣስ እነሱ መቶ በመቶ ቆጥበው እያሉ፣ ከ40 በመቶ ጀምሮ የቆጠቡትን አካቶ ዕጣውን በማውጣት ከሕግና ከውል ውጪ የመነጨን መብት መጣሱን በክሳቸው አስረድተዋል፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስለቤቶቹ መርሐ ግብር አፈጻጸም ያወጣውን መመርያ ማስፈጸም ሲገባው፣ ያንን ባለማድረጉ የከተማ አስተዳደሩ መመርያውን ጥሶ ለፈጸመው የመብት ጥሰት ተጠያቂ መሆኑንም፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 38ን ጠቅሰው በክሳቸው አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ሦስቱም ተከሳሾች በሕግና በውል የተጣለባቸውን ግዴታ የጣሱ በመሆናቸው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 155 መሠረት ዕጣ የወጣባቸው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይተላለፉ ታግደው እንዲቆዩ ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ዕጣው የወጣው ሥልጣን በሌለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሆኑ፣ ዕጣው እንዲሰረዝላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ዕጣው ተሰርዞ ክስ የመሠረቱትና ሌሎችም መቶ በመቶ ክፍያ የፈጸሙ ካሉ፣ የዕጣ ውድድሩ በእነሱ መካከል እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. የ40/60 እና የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶ፣ በአጠቃላይ 51,229 ቤቶች በዕጣ ማከፋፈሉንና ከዕጣው አወጣጥ ጋር በተያያዘ፣ በተለይ ኮዬ ፈጬ በሚባለው ሳይት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱንና በአብዛኛው የኦሮሚያ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፍ መካሄዱን፣ ኦዴፓና ኦነግም መግለጫ ማውጣታቸውን መዘገባቸን ይታወሳል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...