Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ የፈጸሙ መንግሥታዊ ተቋማት የሁለት ወራት ጊዜ...

ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ የፈጸሙ መንግሥታዊ ተቋማት የሁለት ወራት ጊዜ ገደብ ተሰጣቸው

ቀን:

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት 2002 እስከ 2009 በጀት ዓመት ድረስ ባከናወናቸው የኦዲት ሥራዎች ሕግ በመጣስ የመንግሥትን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ከፍለዋል ብሎ የለያቸው በርካታ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ ገንዘቡን እንዲያስመልሱ ወይም በሕግ እንዲጠየቁ የሁለት ወር የጊዜ ገደብ ተሰጣቸው።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በተጠቀሱት ዓመታት ባከናወናቸው ኦዲቶች በተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ሕግ ተጥሶ ወጪ ስለመደረጉ ካሳወቁ በኋላ፣ ተቋማቱ ሕግን በመጣስ የፈጸሙትን ክፍያ እንዲያስመልሱ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህንንም ለመከታተል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልዩ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ኮሚቴውም ሕግ ጥሰው ክፍያ ፈጽመዋል ተብለው የተለዩት ተቋማት ያላግባብ ወጪ የተደረጉ ክፍያዎች ለመንግሥት ተመላሽ መደረጋቸውን በተመለከተ፣ ከተቋማቱ አመራሮች ጋር ሕግ አስከባሪ የመንግሥት ተቋማት በተገኙበት ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

- Advertisement -

 በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ በኦዲት ግኝት መሠረት ያላግባብ በመከፈላቸው ለመንግሥት ተመላሽ ይደረጉ ስለተባሉት ዋና ዋና ክፍያዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ በሰጡት ማብራሪያ ሕግና ሥርዓት በመጣስ የተፈጸሙ ክፍያዎች፣ ሕግና ሥርዓት ሳይኖር አስገዳጅ በሆኑ ወይም ባልሆኑ ምክንያቶች የተፈጸሙ ክፍያዎች፣ መከፈል ከሚገባው በላይ ያላግባብ የተፈጸሙ ክፍያዎች፣ በውሉ መሠረት በወቅቱ ላልቀረበ ዕቃና ላልተፈጸመ አገልግሎት እንዲከፈል ያልተደረገ የጉዳት ካሳ እንደሚገኙባቸው አስረድተዋል፡፡

 2002 እስከ 2009 ዓም ድረስ በተደረጉ ኦዲቶች የተለዩ ሕግ የጣሱ ክፍያዎችን የፈጸሙ ተቋማት በየዓመቱ እየተለዩ፣ ገንዘቡን እንዲያስመልሱ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ያለመፈጸሙን ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል።

ዋና ኦዲተሩ በተጠቀሱት ዓመታት ሕግ በመጣስ የተፈጸሙ ክፍያዎችን በየኦዲት ዓመቱ ዘርዝረው አቅርበዋል። በዚህም መሠረት 2002 በጀት ዓመት 54.3 ሚሊዮን ብር፣ 2003 በጀት ዓመት 12.4 ሚሊዮን ብር፣ 2004 በጀት ዓመት 188.6 ሚሊዮን ብር፣ 2005 በጀት ዓመት 333 ሚሊዮን ብር፣ 2006 በጀት ዓመት 180.7 ሚሊዮን ብር፣ 2007 በጀት ዓመት 656.5 ሚሊዮን ብር፣ 2008 በጀት ዓመት 397.8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም 2009 በጀት ዓመት 278.1 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 2.1 ቢሊዮን ብር ሕግ በመጣስ ክፍያ መፈጸሙን አስረድተዋል። ከእነዚህ ውስጥ እስካሁን የተመለሰው 50 ሚሊዮን ብር እንደማይሞላ ገልጸው፣ ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

 ተቋማቱ ገንዘቡን አለማስመለሳቸው ብቻ ሳይሆን ከዓመት ዓመት የሕግ ጥሰቱ በሌሎች ተቋማትም መቀጠሉን፣ ሕጋዊ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ ጥሰቶችን እንዲፈጽሙና ለሕግ አለመገዛት እንዲስፋፋ ማድረጉን አመልክተዋል።

ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪም በወቅቱ ሳይሰበሰብ የቀረ ቅድመ ክፍያ፣ ከደመወዝና ገቢ ላይ መቀነስ የነበረበት የገቢ ግብር፣ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ላልተሠራ ሥራ የተከፈለ ደመወዝና ክፍያ፣ እንዲሁም ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር የተያያዙ ያልተሰበሰቡ ሒሳቦች መኖራቸውንም ዋና ኦዲተሩ በውይይቱ ወቅት ጠቁመዋል፡፡

 በዚህ ረገድም በገቢዎች ሚኒስቴር ላይ 2002 እስከ 2009 በጀት ዓመት ድረስ በተደረገ ኦዲት ያልተሰበሰበ 12.5 ቢሊዮን ብር መገኘቱን፣ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ተቋሙ እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የተሰበሰበው አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በተሰብሳቢ ገንዘቡ ላይ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ አጠንክረው ተናግረዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የልዩ ኮሚቴው ሰብሳቢና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ምክር ቤቱ በመንግሥት የተመደበው በጀት ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን የመከታተል፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል። በመሆኑም ከፌዴራል ዋና ኦዲተርና ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጋር በመሥራት ያላግባብ የተከፈሉ ገንዘቦች ወደ መንግሥት እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መመለስ ያለባቸውን የመንግሥት ገንዘቦች ማስመለስ ባልቻሉ የሚመለከታቸውን ተቋማት አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎችን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከተቋማቱ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ መመካከሩ ይጠቅማል ተብሎ ውይይቱ መሰናዳቱን አፈ ጉባዔው ጠቁመዋል።

ተጠያቂ ከማስደረግ አስቀድሞ የተቋማቱ አመራሮች ሁኔታውን በመፈተሽ በተባለው ጊዜ ውስጥ ለማስተካከል የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ለመመካከር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ዓቃቤ ሕግ አቶ ገለታ ስዩም በበኩላቸው፣ ተቋማቸው በፌዴራል ዋና ኦዲተር 2009 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት መሠረት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ወደ ሕግ ለማቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ወደ ሕጋዊ ዕርምጃ ከመግባቱ አስቀድሞ ተቋማቱ አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ ለማድረግ የተዘጋጀው መድረክ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

 ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንደተናገሩት የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ በተደረገው ማጣራት፣ በፋይናንስ ኦዲት ግኝት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑ 170 ተቋማትና በክዋኔ ኦዲት ግኝት ደግሞ 20 ተቋማት፣ በአጠቃላይ 196 ተቋማት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል

ሁሉንም በአንድ ጊዜ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ እንደ ግኝቶቹ ክብደት ቅደም ተከተል እንደወጣላቸውና በመጀመሪያ ዙር፣ 15 የፌዴራል ተቋማትና 20 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ 35 ተቋማት እንደተለዩ አስረድተዋል፡፡

ተጠያቂ የሆኑት ተቋማት አመራሮች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ወደ ዕርምጃ ከመገባቱ አስቀድሞ በተሰጠው ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ገንዘቡን በተጨባጭ ማስመለስ ስለመቻሉ፣ እንዲሁም ከአስገዳጅናአስቸኳይ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ በክፍያዎች አፈጻጸም ላይ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በደንብ ማጤን ይገባል ብለዋል፡፡

የኦዲት ግኝቱ ትክክል ቢሆንም ጉዳዩን ወደ ክስ ከመውሰድ ይልቅ፣ ግኝቶቹ በቀጣይ እንዳይከሰቱ የሚያደርጉ ሕጎችና አሠራሮችን ከመፍጠር አኳያ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ መወያየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳይ ከሥራ ባህሪያቸው አኳያ በተለየ ሁኔታ መታየት አለበት ብለዋል፡፡

 ይሁን እንጂ ተቋማቱ ያላግባብ የከፈሉትን ገንዘብ እስከ ሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ እንዲያስመልሱ፣ ካልሆነ ግን ወደ ክስ እንደሚገባ የጊዜ ገደብ በአፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ተሰጥቷቸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...