Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ዕጩዎች የሚመለመሉበት መመርያ ተሻሻለ

ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ዕጩዎች የሚመለመሉበት መመርያ ተሻሻለ

ቀን:

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል ረቂቅ ቀርቧል

የፌዴራል ዕጩ ዳኞችን የመመልመልና ወጥ ሥርዓት ለመዘርጋት መመርያ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ፣ በሥራ ላይ የነበረውን የምልመላ መመርያ በመገምገም ማሻሻሉ ታወቀ፡፡ ጉባዔው ማሻሻያ ካደረገበት አንዱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች የሚመለመሉበት መሥፈርት ነው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአገሪቱ ከፍተኛ የዳኝነት አካል በመሆኑ፣ ለዳኝነት የሚቀርቡት ጉዳዮች በሥር ፍርድ ቤት በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ የቀረበባቸውና የሕግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል የሚባሉ በመሆናቸው፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚመለመሉ ዳኞች በየትኛውም የዳኝነት ደረጃ የዳበረ ልምድና መሠረታዊ የሕግ ዕውቀት ችግር የሌለባቸው መሆን እንዳለባቸው ጉባዔው ባሻሻለው መመርያ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በተሻሻለው መመርያ መሠረት የዕጩ ዳኞች ምልመላ ሒደት የሚጀመረው ከቃል ፈተና መሆኑንም አክሏል፡፡

- Advertisement -

ምልመላው ጥረት የሚያደርግባቸው ነጥቦች ዕጩ ዳኛው ማስረጃን የመተንተንና የመመዘን ብቃት፣ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ጥራት፣ በዳኝነት ሥራ ላይ ያለው ትጋት፣ ሀቀኛ መሆን፣ በነፃነት የመዳኘት ቁርጠኝነት፣ በሥራ ዘመኑ በሰጣቸው ዳኝነቶች ባለጉዳዩ የረካባቸውና የሚተማመንባቸው መሆናቸው፣ በሥነ ምግባሩና በባህሪው የተመሠገነና መልካም ሰብዕና የተላበሰ መሆን እንደሚገባው በመመርያው አስፍሯል፡፡

ለቃል ፈተና የሚመረጡ ዕጩ ዳኞች በዳኝነት ሥራ ላይ የነበራቸው የሥራ አፈጻጸምን መነሻ በማድረግ በተገልጋይ፣ በቅርብ ኃላፊና በሥራ ባልደረቦች ጥቆማ እንደሚጀመር ጉባዔው ያሻሻለው መመርያ ይጠቁማል፡፡ የዕጩ ዳኞቹ ግለ ታሪክ እንደሚጠና፣ በሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሰጡባቸው መዛግብት ይዘት እንደሚመረመርና እንደሚተነተንም ያስረዳል፡፡

ጉባዔው የሚሰጠውን የቃል ፈተና በከፍተኛ ውጤት ያለፉ ዕጩ ዳኞች በሕዝብ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ከተደረገ በኋላ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደሚሾሙ ጉባዔው በመመርያው የምልመላ መሥፈርትና ሒደቱን አብራርቶ አስቀምጧል፡፡

ጉባዔው በአዋጅ ቁጥር 684/2002 በተሰጠው ሥልጣን መሠረትም፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞችን የመመልመል ሥራ መጀመሩንም ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 24/88 ለማሻሻል ረቂቅ በማዘጋጀት፣ መጋቢት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የዳኝነት ሥርዓቱን ለማጠናከር የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በአስተዳደርና በበጀት ራሳቸውን ችለው ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለሕዝቡ ማድረስ እንዲችሉ፣ ላለፉት 23 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየውን አዋጅ ማሻሻል ማስፈለጉን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ ተናግረዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁን እንዲያዘጋጅ ጉባዔው ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን፣ የቀድሞውን አዋጅ ማሻሻል የተፈለገው፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚሾሙ ዳኞች ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዳኞች ነፃነትን ገለልተኛነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በማስፈለጉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ 18 አንቀጾችን የያዘ ሲሆን፣ በአዲስነት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ 40 አንቀጾችን በመያዝ በርካታ ድንጋጌዎችን እንዳካተተ ኮሚቴው ተናግሯል፡፡

የጉባዔውን አጠቃላይ አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር፣ የዳኞችን ሹመት፣ የዳኝነት የሥራ ዘመን፣ ኃላፊነት፣ የዳኞች መብትና ገደቦች፣ የፍርድ ቤቶች የፋይናንስና የሰው ኃይል አስተዳደር ነፃነትን የተመለከቱ አንቀጾችን እንዳካተተም ተገልጿል፡፡

የፍርድ ቤቶች የዳኝነት ተግባራት ለሕዝብና ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት ሆነው ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ፣ ማንኛውንም ተከራካሪ ወገን ያለ አድልኦ በእኩልነት የማስተናገድ ሥርዓት መኖር እንዳለበት በረቂቁ ተመላክቷል፡፡ በተለይ ደግሞ በወንጀል ተከሰው በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ መያዛቸውን የመከታተል ኃላፊነት የሚሰጥ ድንጋጌም እንደሚኖረውም ወ/ሮ መዓዛ አክለዋል፡፡

የሥነ ምግባር ጥሰት የፈጸመ ዳኛ ተጠያቂ እንደሚሆን፣ የሥነ ምግባር ጥሰት ተፈጽሟል ብሎ የሚያምን ማንኛውም ሰው ክስ ማቅረብ እንደሚችል በረቂቁ ተካቶ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

ክስ የቀረበበት ዳኛ ክሱን የማወቅና የመከላከል መብት እንዳለውና የሚወሰድበት የዲሲፕሊን ዕርምጃ ሕግን መሠረት ያደረገ መሆን እንዳለበት፣ ከሳሽም የተሰጠውን ውሳኔ የማወቅ መብት እንዳለው በድንጋጌው መካተቱን ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ላለፉት 22 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...