Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበመንግሥት በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮም ገበያ ለውድድርና ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የሚያደርግ ሕግ...

በመንግሥት በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮም ገበያ ለውድድርና ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት የሚያደርግ ሕግ ሊወጣ ነው

ቀን:

ኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማቶቹን ለሌሎች እንዲያጋራ ሊገደድ ይችላል

በመንግሥት በባለቤትነት በብቸኝነት ተይዞ የቆየውን የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ ለውድድር ክፍት የሚያደርግ፣ ማንኛውም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ኩባንያ ፈቃድ አውጥቶ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች ውስጥ በጤናማ የውድድር መርህ መሳተፍ እንዲችል የሚፈቅድ ሕግ ተረቆ ለሕግ አውጪው ፓርላማ ተላከ።

‹‹ስለቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የወጣ አዋጅ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ረቂቅ ሕግ ለፓርላማው ተልኮ ለይፋዊ ውይይት ፕሮግራም እንደተያዘለት፣ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥም ለውይይት እንደሚቀርብ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

- Advertisement -

የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያውን እንደገና ለማዋቀርና በውድድር ላይ የተመሠረተ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር መንግሥት የወሰነ በመሆኑ፣ የሕግ ማዕቀፉ መዘጋጀቱን ይኸው ረቂቅ ሰነድ በመግቢያ ሐተታው ያመለክታል።

የአገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያ ለማንኛውም ፍላጎት ላለው አካል በእኩል ክፍት እንዲሆን ለማድረግ ረቂቅ ሕጉ በምዕራፍ ዘጠኝ ሥር ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ባስቀመጠው አንቀጽ ደንግጓል።

 ስለኢንቨስትመንት በሚል የተቀመጠው ይህ የረቂቅ ሕጉ ድንጋጌ፣ ‹‹በሌላ ሕግ፣ አዋጅ ወይም ደንብ የተደነገገ ቢኖርም፣ ማንኛውም የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተር ወይም የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ባለቤትነት ፈቃድ የማግኘት መብት ይኖረዋል፤›› ይላል።

በመሆኑም ይህ ረቂቅ ሕግ የሚፀድቅ ከሆነ በሥራ ላይ በሚገኘው የኢንቨስትመንት አዋጅ ውስጥ በቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዘርፍ መሰማራትን በተመለከተ የተቀመጠውን ክልከላ፣ ወይም መንግሥት አገልግሎቱን በብቸኝነት እንዲያቀርብ በሕግ የተደረገለትን ጥበቃ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ያደርጋል።

ፈቃድ አግኝተው በቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተርነት የሚሰማሩ ኩባንያዎች፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለመስጠት የዘረጓቸውን ቋሚና ገባሪ መሠረተ ልማቶቻቸውን በተቻለ መጠን እንዲጋሩ ረቂቅ ሕጉ ግዴታ ይጥልባቸዋል፡፡

በተለይም በቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያ ውስጥ ጉልህ የገበያ ድርሻ እንዳለው የታመነበት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተር ያለውን ቋሚና ገባሪ መሠረተ ልማት፣ ተገቢ ጥያቄ ላቀረበ ሌላ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተር የማጋራት ግዴታ ይጥልበታል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት ‹‹ጉልህ የገበያ ድርሻ›› ማለት ለኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ መገልገያዎችን ወይም በገበያው ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ አቅም በመጠቀም፣ በኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዋጋ ወይም አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የማድረግ ችሎታ ነው።

በዚህ መሠረት በአገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ገበያ ውስጥ በብቸኝነት ለዘመናት የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም ለዓመታት የገነባቸውን የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች፣ ከዚህ ሕግ መፅደቅ በኋላ ለሚመጡ ሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎች የማጋራት ግዴታ ሊጣልበት ይችላል።

መሠረተ ልማትን መጋራት በዘርፉ ጤናማ ውድድርን ለማስፈን በግዴታነት የተቀመጠ መርህ ቢሆንም፣ ኩባንያው መሠረተ ልማቱን የሚያጋራው በክፍያና የክፍያ መጠኑም መሠረተ ልማቱን ለመጋራት ፍላጎት ወይም ጥያቄ ካቀረበ ኩባንያ ጋር በቅን ልቦና በሚደረግ ውይይትና ስምምነት መሠረት መሆኑን ረቂቁ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የአንድ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተር ተጠቃሚዎችና የሌላ ኦፕሬተር ተጠቃሚዎች መካከል እንዲገናኙ፣ ወይም የአንዱ ኦፕሬተር ተጠቃሚዎች በሌላ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተር የሚሰጡ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚኖርባቸው ረቂቅ ሕጉ ግዴታን ይጥላል።

በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን ለማስፈንና ለማበረታታት፣ የተጠቃሚዎችን ተደራሽነትና ፍላጎት ያሟላ እንዲሆን ለማድረግ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የሚል መጠሪያ የሚኖረው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን እንደሚቋቋምም የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል።

የሚቋቋመው ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆንም ያመለክታል።

ረቂቅ ሕጉ ለባለሥልጣኑ ከሚሰጣቸው ሥልጣንና ተግባሮች መካከል የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ ለሚሰማሩ ፈቃድ መስጠት፣ መቆጣጠር፣ ፈቃድ ማሻሻል፣ ማደስ፣ ማገድ ወይም መሰረዝና ለኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚጠየቀውን ታሪፍ መቆጣጠር ይገኙበታል።

ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ጋር ተገናኝተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረጉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች ዓይነትን መቆጣጠር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለንግድ፣ ለመንግሥት፣ ለአገር መከላከያና ለብሔራዊ ደኅንነት ሥራዎች ጥቅም ላይ የሚውሉ የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ ስፔክትረም አጠቃቀምን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር መፍቀድና መቆጣጠር፣ ብሔራዊ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁጥር ፕላን ማዘጋጀት፣ መመደብ፣ ማስተዳደርና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን መቆጣጠር ከተዘረዘሩት ሥልጣንና ተግባሮቹ መካከል ናቸው።

በተለያዩ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪዎች መካከል የሚኖረውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርኮች ኢንተርኮኔክሽን መቆጣጠር፣ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን መብት ማስጠበቅና ሌሎች ለባለሥልጣኑ ከተሰጠው ሰፊ ኃላፊነቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

በረቂቅ ሕጉ መሠረት የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚስጢራዊነት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ሁሉ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል።

ይሁን እንጂ የአገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት ከቴሌኮሙዩኒኬሽን ደንበኞች ጋር የተያያዙ መረጃዎች እንዲሰጠው ሲጠይቅ፣ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ማንኛውም ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ሕጋዊ ትዕዛዝ ማክበር እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታል።

በተመሳሳይ ለብሔራዊ የደኅንነት ጉዳዮች ሲባል የወንጀል ምርመራ ወይም የአገር ደኅንነት ምርመራ ለማካሄድ ለተፈቀደለት የመንግሥት አካል፣ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በቴሌኮሙዩኒኬሽን ላይ ሕጋዊ ክትትል ማድረግ እንዲችል የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ኔትወርካቸውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የረቂቅ ሕጉ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህን በማይፈጽሙ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች ላይ ባለሥልጣኑ ቅጣት ከመጣል አንስቶ፣ የተሰጣቸውን ፈቃድ ሊሰርዝ እንደሚችል ያመለክታል፡፡

በተጨማሪም ብሔራዊ ደኅንነትን ለመደገፍ ዓላማ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኦፕሬተሮች የደንበኞች መረጃ ቋት በተሻላ ሁኔታ መያዝ እንዲችሉ፣ የሲም ካርድ ምዝገባ እንዲያከናውኑና ባለሥልጣኑ ደንበኞችን በተመለከተ የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በብሔራዊ የደንበኞች መረጃ እንዲያደራጁ የማዘዝ ሥልጣን ለባለሥልጣኑ ተሰጥቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ