Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናእነ አቶ በረከት ስምዖን ፍርድ ቤት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠየቁ

እነ አቶ በረከት ስምዖን ፍርድ ቤት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠየቁ

ቀን:

ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ታስረው የሚገኙት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ ወደ ፍርድ ቤት ሲገቡና ሲወጡ ክብረ ነክ ስድብ እየተሰነዘረባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ጠየቁ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት እንዳመለከቱት፣ የአማራ ክልል ሕዝብ በሕግና በሥርዓት የሚመራ ታላቅና ኩሩ ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን እነሱን የሚሳደቡትና ተገቢ ያልሆነ ተግባር እየፈጸሙ ያሉት፣ ሆን ተብሎ የተሰማሩ ጉልበተኞች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያደረገ የሚገኘው የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በርካታ ሰነዶችን ከመሰብሰቡም በተጨማሪ ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ የኦዲት ሥራውን ለማጠናቀቅ እየሠራ ነው፡፡ የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ሽያጭና አሠራር ውስብስብ ከመሆኑም በላይ፣ ሆን ተብሎ ሰነዱ በፋብሪካው እንዳይቀመጥ በመደረጉ ለኦዲት ሥራው አስቸጋሪ እንደሆነበት አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

ኦዲቱ የሚደረገው በክልሉ ዋና ኦዲት መሥሪያ ቤት ቢሆንም፣ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የኦዲት ቡድኑ ሥራውን መቼ ማጠናቀቅ እንደሚችልም የጊዜ ሰሌዳ ጭምር እንዳቀረበለትም አክሏል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሆን ብሎ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ እየጠየቀ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እየተጋፋ መሆኑን የተናገሩት አቶ በረከት፣ 90 በመቶ ምርመራ ማጠናቀቁን፣ መረጃ መሰብሰቡንና ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ ማግኘቱን ለክልሉ ባለሥልጣናት ጭምር መግለጫ ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መጠየቅ ቢኖርበት እንኳን የክስ መመሥረቻ ጊዜ መሆን ሲገባው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ ባለመሆኑና እነሱም እየተጉላሉ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤቱ ሊፈቅድለት እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡ ሌላው አቶ በረከት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ከረዥም ጊዜ እስር በኋላ ጠበቆች ያቆሙ ቢሆንም፣ ሆን ተብሎ በተሰማሩ ጉልበተኞች ማስፈራራትና ዛቻ ስለደረሰባቸው ሊቆሙላቸው እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ጠበቆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር እያስፈራሯቸው በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊሰጥላቸው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አቶ ታደሰ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ምርመራውም ሆነ ኦዲቱ እስካሁን አለመጠናቀቁ የሚያሳየው የአቅም ውስንነትን ነው፡፡ የከሰሳቸው የክልሉ አመራር በመሆኑ፣ ምርመራው ሆን ተብሎ እየተጓተተ በእስር እንዲቆዩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ለምርመራ ቡድኑ እስካሁን የተሰጠው ጊዜ በቂ ሆኖ በነፃ ሊሰናበቱ እንደሚገባም አክለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ 90 በመቶ ምርመራው ተጠናቋል መባሉ ትክክል መሆኑንና ለቀሪዎቹ ሥራዎች ግን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ፣ ተደጋጋሚ ቀጠሮ የሚሰጠው ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠትና ጉዳዩን በሚገባ ሁኔታ ለማጣራት መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ስምንት ቀናት ፈቅዷል፡፡

በተጨማሪም በጠበቆቻቸውና በቤተሰብ ላይ ጫና ደርሷል መባሉን ፍርድ ቤቱ ትኩረት በመስጠት፣ ‹‹አቅም ካለው ማንም ሰው በጠበቃ የመወከልና የመቅጠር መብት አለው፡፡ ሀብት ከሌለው ደግሞ መንግሥት ጠበቃ አቁሞለት መከራከር ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ነው፤›› ካለ በኋላ፣ በጠበቃና በቤተሰብ ላይ ጫና የፈጠሩትን፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ ሲወጡና ሲገቡ መሰደባቸው አግባብ ባለመሆኑ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ተከታትሎ ዕርምጃ እንዲወስድና እንዲያስተካክል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የኦዲት ምርመራውን አጠናቆ ለመጋቢት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...