Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቀድሞ የደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞብኛል በማለት ይግባኝ አሉ

የቀድሞ የደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞብኛል በማለት ይግባኝ አሉ

ቀን:

በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ ይግባኝ ጠየቁ፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ያሬድ ዘሪሁን ይግባኝ ያቀረቡት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ የሕግ ስህተት ተፈጽሞብኛል ያሉበትን ምክንያት እንዳብራሩት እሳቸው ተጠርጥረው የታሰሩት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ በዚህም የምርመራ መዝገብ ተከፍቶ ተደጋጋሚ ጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠ ተጣርቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ምርመራውን ማጠናቀቁን ለፍርድ ቤቱ ሳያሳውቅ፣ በመሀል ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፖሊስ ቃል የተቀበላቸውን ምስክሮች ቃል በቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት (በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት) ማሰማት እንዳለበት ማመልከቱን በይግባኛቸው አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት የሚኖረው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 80 (1) ተደንግጎ እንደሚገኘው ከባድ የግፍ አገዳደልና ከባድ ውንብድና በፈጸመ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ እሳቸው ግን በዚህ ዓይነት ወንጀል ስላልተጠረጠሩ እንደማይመለከታቸው በወቅቱ ተቃውሟቸውን ለፍርድ ቤቱ ቢያሰሙም፣ ተቃውሟቸው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም እሳቸው የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ላይ ክስ ሲቀርብ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ መሆኑ እየታወቀ፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 2 እና 23 ድንጋጌዎችን የጣሰ ብይን መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በመርማሪ ፖሊስ የተደረገው ምርመራ ሲደርሰው ምርመራውን አረጋግጦ ክስ መመሥረት ካለበት መመሥረት ሲገባው፣ ይኼንን በማለፍ ለቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ማቅረቡ የሕጉን መንፈስ የተፃረረ መሆኑንም አክለዋል፡፡

- Advertisement -

በተጨማሪም ለቀዳሚ ምርመራ ፍርድ ቤት ምስክሮችን ማቅረብ የፈለገበትን ምክንያት ማስረዳ ነበረበት ብለዋል፡፡ ምክንያቱም የምስክርነት ቃላቸው በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችልበት ሁኔታ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 144 (1) ድንጋጌ መሠረት እንዴት ሊሆን እንደሚችል የተደነገገ መሆኑንም በማወቁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በደፈናው ሁሉንም ምስክሮች ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት በማቅረብ፣ እሳቸው ያላግባብ በእስር እንዲቆዩ ማድረጉንም አክለዋል፡፡

አቶ ያሬድ ቅሬታቸውን ለሥር ፍርድ ቤት አቅርበው እንደነበር አስታውሰው፣ የሥር ፍርድ ቤት ከወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉና ከሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 20 (1) አንፃር የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ከመስጠት አኳያ ሊመለከተው ሲገባ ዓቃቤ ሕግ በችሎት፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ከሰባት እስከ 15 ዓመታት ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል መጠርጠራቸውን ገልጿል፤›› በማለት ቅሬታቸውን ማለፉ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን በይግባኛቸው ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ያሬድ እንዳብራሩት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (4) ተደንግጎ እንደሚገኘው የተከሰሰ (የተጠረጠረ) ሰው የቀረበበትን ማስረጃ የማየትና የቀረቡበትን ምስክሮች የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ተጠርጣሪው ያቀረቡበትን ምስክሮች እነማን እንደሆኑ፣ የሚመሰክሩባቸውን ጭብጦች በምን አግባብ ሊያውቁ እንደቻሉና የምስክርነታቸው ቃል ተዓማኒ መሆኑን በመስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ እንደሚችሉ ተደንግጎ ይገኛል ብለዋል፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (1) መነሻነት ውድቅ መደረግ ይገባው የነበረን አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀጽ 4 (1ሸ እና በ) በመጥቀስ፣ የምስክሮቹ ስም፣ ማንነትና መልክ እንዳይታይ ተሸፋፍነው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይኼም ኢትዮጵያ የተቀበለችውንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ሥር የሕገ መንግሥቱ አካል ያደረገችውን ዓለም አቀፍ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ (11) የጣሰ በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡  

የምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ሊፈጸምና ሊተገበር የማይገባ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ሊፈጸም ይገባል ቢባል እንኳን በቅድሚያ ተጠርጣሪው አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣው፣ ያለ ምስክሩ ቃል በሌላ በማናቸውም መንገድ ድርጊቱን መፈጸሙ ሊረጋገጥ ወይም ሊደረስበት የማይችልና የምስክሩ፣ የቤተሰቡ ሕይወት ወይም አካላዊ ደኅንነት፣ ነፃነት ወይም ንብረት ከባድ አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነገር መረጋገጥ ከቻለ ብቻ መሆኑ ሳይረጋገጥ፣ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 804/2005 አንቀጽ 18(4)፣ የአገልግሎቱ ሠራተኛ በሥራ ላይ እያለ ያወቃቸውን አሠራሮች፣ የሥራ እንቅስቃሴና ተመሳሳይ ጉዳዮችን በሚመለከት ለማናቸውም አካል ያለ መግለጽ ግዴታ እንዳለበት ተደንግጎ እንደሚገኝ አቶ ያሬድ በይግባኝ አቤቱታቸው ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት የቆጠሯቸው በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች በተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃል እንዲያሰሙ ብይን መሰጠቱም፣ የሕግ ስህተት መሆኑን አክለዋል፡፡

አቶ ያሬድና ሌሎችም የተቋሙ ሠራተኞች በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት አብረው የታሰሩ ቢሆንም፣ የሚጠረጠሩበት ወንጀል ደረጃ፣ ዕውቀትና ድርጊት የተለያየ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ራሱ ገልጾ እያለ፣ የቅድመ ምርመራ መስማቱም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 117 እና 130 (1) መሠረት ተነጣጥሎ መስማት ሲገባው፣ አንድ ላይ መስማት መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አቶ ያሬድ በይግባኝ አቤቱታቸው ሌላው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል ያሉት የዋስትና መብታቸው መነፈጉን ነው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ተጠርጣሪዎች የቅድመ ምርመራ ሒደት ሲጠናቀቅ ክስ ስላልቀረበባቸውና ዋስትና የሚከለክል የሕግ አንቀጽ ስላልተጠቀሰባቸው፣ ዋስትና ቢጠየቁም ተቀባይነት አላገኙም፡፡ ይኼ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (7) እና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 ድንጋጌዎችን የጣሰ በመሆኑ፣ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤት የሰጣቸው ብይኖች እንዲሽሯቸው የይግባኝ አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የሥር ፍርድ ቤት የሰጣቸው ብይኖች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተፈጽሞባቸዋል ወይስ አልተፈጸመባቸውም የሚለውን ለመመርመርና ለመጠባበቅ፣ ለመጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...