Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበአዲስ አበባ ጉዳይ ለመወያየት በተጠራ ስብሰባ የተሳተፉ ወጣቶች ታስረው ተለቀቁ

በአዲስ አበባ ጉዳይ ለመወያየት በተጠራ ስብሰባ የተሳተፉ ወጣቶች ታስረው ተለቀቁ

ቀን:

‹‹ስለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?›› በሚል መሪ ቃል እሑድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት፣ በባልደራስ የቤተ መንግሥት ጡረተኞች አክሲዮን ማኅበር አዳራሽ ውስጥ ተገኝተው የነበሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች፣ ‹‹የመረበሽ አዝማሚያ አሳይተዋል›› በማለት የፌዴራል ፖሊስ ተይዘው የታሰሩ ቢሆንም፣ በማግሥቱ ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈቱ፡፡

ወጣቶቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ለአንድ ቀን ታስረው የተለቀቁት ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ እስክንድር ነጋ ‹‹ስለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?›› በማለት፣ በተለይ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ባስተላለፈው የምክክር መድረክ ጥሪ ላይ የተገኙ ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በምክክር መድረኩ ላይ ከተሳተፉና ምክክሩ በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ወደ አካባቢያቸው በመመለስ ላይ እያሉ አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ሲደርሱ፣ አንዳንድ ወጣቶች በአካባቢው ያሉ የንግድ ተቋማትን የመረበሽ ‹‹አዝማሚያ›› በማሳየታቸው፣ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል፡፡ እንዲታሰሩ የተደረገው በራሳቸው በወጣቶቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስና በኅብረተሰቡም ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ መሆኑን አክለዋል፡፡ ለወጣቶቹ የተሰጠው ምክር ምን እንደሆነ ኮሚሽነሩ ባይናገሩም፣ አስፈላጊው ምክር ከተሰጣቸው በኋላ ሁሉም ወጣቶች መፈታታቸውን ተናግረዋል፡፡

አንድ ሰው የፈጸመው ድርጊት ሳይኖር ግምት ወስዶ በቁጥጥር ሥር ስለማዋል የሚቻልበት የሕግ አግባብ ሳይኖር ፌዴራል ፖሊስ በየትኛው ሥልጣኑ እንዳሰራቸው ግልጽ አለመሆኑን፣ ሰውን ያለ ፍርድ ቤት መያዣና ምንም ዓይነት ድርጊት ሳይፈጽም በእስር ማቆየት፣ አገር አቀፍንም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መጣስና የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ለወጣቶቹ መታሰር ምክንያት የሆነው ‹‹ስለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?›› የምክክር ዝግጅት የተካሄደው፣ ከላይ እንደተገለጸው በቤተ መንግሥት ጡረተኞች አክሲዮን ማኅበር አዳራሽ በባልደራስ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡

አዳራሹ ከ1,000 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ ባይችልም፣ ምክክሩን ለመታደም በሥፍራው የተገኘው ሕዝብ ግን በሺዎች የሚቆጠር ነበር፡፡ በወቅቱ በጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል በሚገኝ ጠባብ ሥፍራና ዋና መተላለፊያ መንገድ ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙትን የከተማ ነዋሪዎች ስብስብ የተመለከቱ ከፍተኛ ሥጋት ገብቷቸው ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በመገናኛ ብዙኃን ባስተላለፈው መግለጫ፣ በከተማው ስለሚደረግ ሰላማዊ ሠልፍም ሆነ ስብሰባ የሚያውቀው እንደሌለ፣ እንዳልተፈቀደና ምንም ዓይነት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አለመመደቡን በማስታወቁ ነው፡፡ ነገር ግን በዕለቱ የምክክር መድረኩ ይደረጋል በተባለበት ባልደራስ አዳራሽ መግቢያ በር ላይ ጥቂት ፖሊሶች ቆመው የቻሉትን ያህል ሕዝቡን ለማስተናገድ ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ምናልባትም ረብሻ መነሳቱ አይቀርም ወይም ይነሳል የሚል ሥጋት ያደረባቸው የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስና አድማ በታኝ ፖሊስ በአካባቢው በሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቅጥር ግቢ በተሽከርካሪ ላይ በመሆን፣ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ መውጫ፣ ወደ ቀበና ብረት ድልድይና ወደ አዋሬ መሻገሪያ አካባቢ በጥንቃቄና በተጠንቀቅ ቆመው ተስተውለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ በተለያዩ የፕሮግራሙ አዘጋጆች ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ የተጀመረ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡

ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ እስክንድር ባደረገው ንግግር የከተማው አስተዳደር በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ ስም ለመደራደር የሕግ፣ የፖለቲካም ሆነ የሞራል ውክልና እንደሌለው በመግለጽ፣ የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን አከላለል በሚመለከት፣ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርቡ አዲስ አበባን ወክለው በኮሚቴ ውስጥ የተካተቱትን የከተማ አስተዳደሩ አባላት ላይ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡

ዋና ድክመታቸው ድርጅት የሌላቸው መሆኑን የጠቆመው አቶ እስክንድር፣ በዕለቱ የተሰበሰቡት የከተማ ነዋሪዎች የሚጠይቃቸው ውክልና መሆኑንም አስረድቷል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ ማንም ልዩ ጥቅም እንደሌለው የጠቆመው አቶ እስክንድር፣ ልዩ ጥቅምን በሚመለከት ምርጫ መቼም ቢሆን ቢካሄድ በአንድ ቀበሌ አንድ ወንበር እንኳን ማሸነፍ እንደማይቻል አክሏል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለኝ የሚልን ለመታገል እንደራጃለን፤›› ያለው አቶ እስክንድር፣ የማይደግፉ ክልሎች ቢኖሩም የሚደግፉም ስላሉ ለመታገል ግን ክልል ድረስ ሄደው እንደሚቀሰቅስ ተናግሯል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥን ምክንያት አድርጎ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎች መደረጋቸውን የጠቆመው አቶ እስክንድር፣ የክልሉ መንግሥት ተቃውሞውን ተከትሎ መግለጫ ቢያወጣም ከሠልፉ በስተጀርባም እጁ ያለበት ለመሆኑ ተመራማሪ መሆን እንደማያስፈልግም አክሏል፡፡

የወሰን ድርድርና የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ምንም የሚገናኛቸው ነገር ስለሌለ፣ ዕጣ የወጣላቸው የከተማው ነዋሪዎች ቤቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ይኼም የፌዴራል መንግሥቱ ኃላፊነት መሆኑንና በተለያዩ የማስፈራሪያ ድርጊቶች የተካሄዱት ሠልፎች ኢትዮጵያዊነትን ስለማይወክሉ፣ መንግሥት በይፋ ወጥቶ ሊያወግዝ ይገባል ብሏል፡፡

የወሰን ድርድሩን በሚመለከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሹማምንት የዕለት ከዕለት ሥራ ከመሥራት ባለፈ፣ አዲስ አበባን ወክለው ሊደራደሩ የሚችሉና በከተማው ነዋሪ የተመረጡ ከንቲባዎች ስለሌሉ፣ በምርጫ የሚመደብ ከንቲባ እስከሚመጣ ድረስ ድርድር መካሄድ እንደሌለበት አስረድቷል፡፡ አሁን ከተማዋን ከሚመመሯት ግለሰቦች ጋር ችግር እንደሌለበት የጠቆመው አቶ እስክንድር፣ የሚያጣላው አስተሳሰባቸው መሆኑን አክሏል፡፡ አሁን ያሉት የከተማዋ አስተዳዳሪዎች አዲስ አበባን ሊሠሩባት ሳይሆን ሊሠሩላት የመጡ መሆናቸው፣ ቀደም ብለው ከ20 ዓመታት በላይ ከተማዋን ያስተዳድሩ የነበሩ ባለሥልጣናትን ማስታወስ በቂ መሆኑን አስታውሷል፡፡

የወሰን ድርድር ለማድረግና ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ የተዋቀረው ኮሚቴ ስብጥር የሚሳየው ለድርድር ሳይሆን ለድራማ መሆኑን እንደሆነም አክሏል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት መፅደቁን፣ ያፀደቀው ግን ሕዝብ እንዳልሆነና ማን እንዳፀደቀው ይታወቃል ብሏል፡፡ ምርጫ ከተደረገ በኋላ ኢሕአዴግ ‹‹ሥልጣኔን በሕዝብ ለተመረጠ መንግሥት አስረክባለሁ›› ብሎ ስለነበር፣ ምርጫ መደረጉን፣ ኢሕአዴግን ወክለዋል የተባሉት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በሕዝብ ተመርጠዋል ለተባሉት አቶ መለስ ዜናዊ መዶሻቸውን እንዳስረከቡና አሁንም ሊሠራ የታሰበው ድራማ ተመሳሳይ መሆኑን አቶ እስክንድር አብራርቷል፡፡

አዲስ አበባን የሚመኛት ለአፍሪካ መዲናነት እንጂ ለአንድ ብሔር እንዳልሆነ የጠቆመው አቶ እስክንድር፣ ይኼንን የሚሉት ጥቂቶች የተከበረውንና አብሮ መኖር የሚፈልገውን የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ከሁሉም አቅጣጫ የሚመጣው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ ከአፍሪካና ከዓለም አገሮች የሚመጡ እንኳን ነዋሪ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ በመጨረሻም ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ ወጥቷል፡፡ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿና የኢትዮጵያ እንጂ ማንኛውም ክልል ልዩ ጥቅም ሊጭንባት የማትችል ከተማ መሆኗን፣ በአዲስ አበባ ወሰንና ሥፍራዎች ላይ በምርጫ የሚመጣ አስተዳደር እስኪኖር ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይኖር፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ በሚቀጥለው ምርጫ ልዩ ጥቅም ለሚል አካል ድምፅ እንዳይሰጥና ለምክክር የሚጠራ ማንኛውም እንቅስቃሴ ሰላማዊ መሆኑን መወሰናቸውንና በሙሉ ድምፅ መስማማታቸውን የሚገልጽ ፒቲሽን በማሰባሰብ፣ ለመንግሥት ገቢ እንደሚያደርጉ በመግለጽ የምክክር መድረኩን አጠናቀዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...