Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› ስያሜውን እንዳይጠቀም የተላለፈበትን ውሳኔ ተቃወመ

‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› ስያሜውን እንዳይጠቀም የተላለፈበትን ውሳኔ ተቃወመ

ቀን:

ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ኮርፖሬሽን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረበበት ክስ፣ ስያሜውን እንዳጠቀም ውሳኔ የተላለፈበት ‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› ውሳኔው ሕግን መሠረት ያላደረገ ነው ሲል ተቃውሞውን ገለጸ፡፡

የሆቴሉ ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› የሚለው የንግድ ስም እንጂ የንግድ ምልክት አይደለም፡፡ ይኼንን የንግድ ስም ያገኙት ደግሞ በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት በማስመዝገብ፣ ‹‹ተቃዋሚ ካለ›› በማለት በጋዜጣ ጥሪ አስደርገው ነፃ መሆኑን በማረጋገጥ የተሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስያሜውን በሚመለከት ቀደም ባሉት ዓመታት የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ክሶች ቀርበውባቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ስማቸው፣ ፍርድ ቤቶቹ አስፈላጊውን ምርመራ ካደረጉና ከሕጉ ጋር ካገናዘቡ በኋላ ውድቅ አድርገውት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን ውሳኔ ያስተላለፈው ፍርድ ቤትም ያቀረቡትን የሰነድና ሌሎች ማስረጃዎች በአግባቡ ሳይመዝን በማለፍ በመሆኑ፣ ጉዳዩን በቀጣይ ለበላይ ፍርድ ቤቶች አቅርበው መብታቸውን ለማስከበር በሒደት ላይ በመሆናቸው ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

ፍርድ ቤቱ ስያሜውን በማናቸውም አኳኋን፣ ማለትም በድረ ገጽ በመገልገያ ንብረቶችና ሌሎች ሁኔታዎች እንዳይጠቀም ውሳኔ ያስተላፈለው፣ ‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ኮርፖሬሽን›› ከስድስት መታት በፊት የንግድ ምልክቱን በመጠቀም የመብት ጥሰት እንደተፈጸመበት በመግለጽ በመሠረተው ክስ ምክንያት ነው፡፡

‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› በአዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26 ድንጋጌ ክልከላ የተጣለበትን የንግድ ምልክት፣ ከጥቅምት 7 ቀን 1999 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለም አቀፍ እንግዶችን ጭምር በማሳሳት ከንግድ ሕግ ውጪ በመነገድ ያላግባብ ጥቅም ማግኘቱን በክሱ ማቅረቡን ውሳኔው ያስረዳል፡፡

ለሕጋዊ ሽፋን ሲባል አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤትን በማሳሳት ተመዝግቦ የአገር ውስጥ ንግድ ምልክት ሰርተፊኬት መቀበላቸውንም በክሱ አክሏል፡፡

‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› በሰጠው ምላሽ የንግድ ስም ከአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት መጠየቁን ሳይክድ፣ ሕጋዊ ጥያቄ በማቅረብ የንግድ ስያሜ እንደተሰጠው አስረድቷል፡፡ የንግድ ምልክቱ (ሎጎ) ግን ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ኮርፖሬሽን ከሚጠቀምበት የተለየ መሆኑንም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሁለቱ ወገኖች የመከራከሪያ ነጥቦች በመነሳት ከሳሽ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስመዝግቦ፣ ባለቤት በሆነበት የንግድ ምልክት ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባን መብት ተከሳሽ ጥሷል ወይስ አልጣሰም? የሚል ጭብጥ ይዞ መመርመሩን ውሳኔው ያስረዳል፡፡ ከሳሽ የንግድ ምልክት ጥበቃ መብቱ እንደተጣሰበት እንጂ፣ የምልክቱ (ሎጎው) መብቱ እንደተነካበት ባለመክሰሱ ተከሳሽ የሰጠው ምላሽ ከእሱ ጋር ተያያዥነት የለውም ብሏል፡፡ በአዋጁ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26 መሠረት የንግድ ምልክት መብት ጥሰት እንደተፈጸመበትና ሊካስ የሚገባው መሆኑንም በውሳኔው ጠቁሟል፡፡ ንግድ ምልክቱን እንዲጠቀም ተፈቅዶለት ከሚገኘው ትርፍ ከፍተኛው የሮያሊቲ ክፍያ እንዲሰጠው ተስማምቶ ቢሆን ኖሮ፣ ተሠልቶ ሊከፈለው ይችል እንደነበር ጠቁሞ፣ ሆቴሉ ያተረፈው ትርፍ ታስቦ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልጿል፡፡

ሆቴሉ ተጣርቶ የሚያገኘውን ዓመታዊ ትርፍ ምን ያህል እንደሆነ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲያሳውቅ ተጠይቆ፣ ሒሳቡን በአግባቡ የሚገልጽ ባለመሆኑና ዜድ ሪፖርት (ዓመታዊ ማጠቃለያ ሽያጭ ሪፖርት ሰነድ) ያልተያያዘ በመሆኑ፣ ትርፉን ነጥሎ ማወቅ እንደማይቻል መግለጹን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

ከሚመለከተው ተቋም ማስረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ተከሳሹ እንዲከፍል ማድረግ የሚቻለው፣ ከውል ውጪ ባለ ግንኙነት የሚገዛውን የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2102 መሆኑንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም ክፍያውን በትክክል እንዲፈጽምና ከሳሽ እንዲከፍለው ካቀረበው አንድ ሚሊዮን ብር ውስጥ 750,000 ብር ካሳ ተከሳሽ እንዲከፍል ውሳኔ መስጠቱን ሰነዱ ያሳያል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...