Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የተከሰሱት መርማሪዎች መቃወሚያ አቀረቡ

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የተከሰሱት መርማሪዎች መቃወሚያ አቀረቡ

ቀን:

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ከሦስት ወራት በላይ ሲመረመሩ ከከረሙ በኋላ ‹‹ያልተገባ አሠራር በመጠቀም ምርመራ ማድረግ›› ተብለው የወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪዎች፣ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን አቀረቡ፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ እንዳብራሩት፣ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ ‹‹ያልተገባ አሠራር በመጠቀም ምርመራ ማድረግ›› በተለይ የግንቦት ሰባትና የኦነግ አባላትን ‹‹አሸባሪዎች›› በማለት ድብደባና የተለያዩ የማሰቃያ ድርጊቶችን እንደፈጸሙ ተገልጾ የተመሠረቱባቸው በርካታ ክሶች፣ ተመሳሳይና አንድ ዓይነት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ተከሳሾቹ ፈጸሙት የተባለው የወንጀል ድርጊት ተመሳሳይ ሆኖ ሳለ፣ ተጎጂ ናቸው ተብለው በክሱ የተጠቀሱትን ግለሰቦች በአንደኛው ክስ ላይ አንድ፣ በሌላኛው ክስ ላይ ከአንድ በላይ ተጎጂ በማለት የክስ ማብዛት መደረጉን በመቃወሚያቸው ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የእነሱን የመከላከል መብት ለማጥበብ በማሰብ ክሶቹን ቢያበዛቸውም፣ የወንጀል ሕጉ ግን እንደሚከለክል አስረድተዋል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 61 እንደተደነገገው፣ አንድ ወንጀል የማድረግ ሐሳብና ተደጋግመው የተደረጉ የወንጀል ድርጊቶች፣ በአንድ ድንጋጌ ሥር እንደሚሸፈኑና እንደ አንድ ወንጀል እንደሚቆጠሩ የተደነገገ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ድንጋጌውን በመተላለፍ ተመሳሳይ በርካታ ክሶችን ማቅረቡን ተቃውመዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በመዝገብ ቁጥር 73514 ላይ አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበትም አክለዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክሶቹን በአንድ አጣምሮ ማቅረብ ሲገባው በመነጣጠል ያቀረበው፣ የሕግ መሠረት እንደሌለውና የወንጀል ድርጊቶቹ ተፈጽመዋል ቢባል እንኳን በአንድ ሐሳብ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ሐሳብ፣ በተከታታይ የተፈጸሙ አንድ ዓይነት የወንጀል ድርጊቶች ስለሚሆኑ ‹‹ለአንድ ጥፋት አንድ ቅጣት›› በሚለው የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ሊታይ እንደሚችል በማወቁ ስለሆነ፣ ውድቅ እንዲደረግላቸው በመቃወሚያቸው ተቃውመዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ 78 ክሶችን ያቀረበው ‹‹ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን›› በሚል መሆኑን ጠቁመው፣ በወንጀል ሕጉ ግብረ አበር የሚል ቃል የሌለ መሆኑን፣ እነሱም በመንግሥት የታወቀ የአሠራር ሒደት ተከትለው ስለሚሠሩና የተፈጸመ ወንጀል ስለሌለ፣ በደፈናው ለማለፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ግብረ አበሮች ካሉ መያዝና በሕግ ፊት ማቅረብ ወይም በሥራው ላይ የሌሉም ከሆነ መግለጽ ሲገባው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ‹‹ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው›› የሚለውን ድንጋጌ የሚፃረር ትርጉም ለመስጠትና እነሱን ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ በመሆኑ፣ ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ወይም ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

እያንዳንዱ ተከሳሽ ግልጽ የሆነ የሥራ ቦታና ኃላፊነት የነበረው ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ወንጀሉ መቼ እንደተፈጸመ በግልጽ የማያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ድርጊቱ ተፈጽሟል በተባለበት ወቅት የተለያዩ ቦታዎች እንደነበሩና ለምን እንደተከሰሱም ግራ መጋባታቸውን በመቃወሚያቸው ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ክሶቹ ተበታትነው በመቅረባቸው የመከላከል መብታቸውን ከማጣበባቸውም በተጨማሪ፣ በሰበር ችሎት መዝገብ ቁጥር 91536፣ 38161 እና 73514 በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉ የሚቋቋምበት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተጣምረው ሲገኙ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ክሱ ግልጽና ለመከላከል በሚያመች መንገድ እንዲቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጅል ችሎት የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሾቹ ያቀረቡትን የቅድመ ክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾቹ ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ፣ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈዓይኔ፣ ዋና ሳጅን ኪዳኔ አሰፋ፣ ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን፣ ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግሥቱ ታደሰ፣ ረዳት ኢንስፔክተር ዓለማየሁ ኃይሉና ኢንስፔክተር ስንታየሁ ፈጠነ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...