Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹ፀብ አጫሪና የጥላቻ ድርጊቶች ጎጂ በመሆናቸው ተማምነንና ተግባብተን ውድቅ ልናደርጋቸው ይገባል›› ...

‹‹ፀብ አጫሪና የጥላቻ ድርጊቶች ጎጂ በመሆናቸው ተማምነንና ተግባብተን ውድቅ ልናደርጋቸው ይገባል›› አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ ተመራጩ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት

ቀን:

የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን መልቀቂያ ተቀብሎ፣ ፕሬዚዳንት አድርጎ የመረጣቸውን ኢኮኖሚስቱን አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ሾመ፡፡ ተሿሚው ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ አሁን እየታዩ ያሉት ፀብ አጫሪና የጥላቻ ድርጊቶች ኋላ ቀርና ጎጂ ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ የአገሪቱን ሕዝቦች ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ተግባብቶና ተማምኖ ውድቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ዓርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸውን አስመልክተው ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ከምንም በላይ የምትጠቀመው ከሰላም ነው ብለዋል፡፡ አሁን እየታዩ ያሉትን ፀብ አጫሪና የጥላቻ ድርጊቶችን ውድቅ በማድረግ፣ በምትካቸው የሠለጠኑ የቅራኔ አፈታት ሥልቶችን ተግባር ላይ በማዋልና ከከረረ የፖለቲካ ውጥረት በመውጣት፣ አስተማማኝ ሰላም የሠፈነባትና ዜጎች በሙሉ ነፃነት የሚንቀሳቀሱባት አገር ለማድረግ ዝግጁ መሆን አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሲሾማቸው የተጣለባቸው አደራና ኃላፊነት ከባድ፣ የሚያስጨንቅና በውስብስብ ችግሮች የተተበተበ ቢሆንም፣ የአማራን ሕዝብ መምራት ዕድልና ኩራት በመሆኑ በጣም ደስ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአማራ ሕዝብ በነፃነቱና በአገሩ ጉዳይ የማይደራደር፣ ሕግን የሚያከብርና ፈሪኃ እግዚአብሔር ያደረበት፣ ለሰው ልጆች ክብር የሚሰጥ፣ ያለውን የሚያካፍልና የሚሰጥ ሩኅሩኅ ሕዝብ ነው፤›› ብለው፣ ላለፉት ዓመታት በተፈጸሙ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የፍትሕ መጓደል ችግሮች ገፈት ቀማሽ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ሕዝቡና አዴፓ ከሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶችና ሕዝቦች ጋር በመሆን ባደረገው ከፍተኛ ትግል፣ ክልሉ አሁን ለደረሰበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ቀደም ሲል የተከናወኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ፣ በቀጣይ ማስተካከያ የሚፈልጉ የተለያዩ የልማት ዘርፎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ያሉትን አዎንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎች በመገምገም ፈጣን የሥራ ሥምሪት እንደሚከናወንም አክለዋል፡፡

- Advertisement -

ፕሬዚዳንቱ የክልሉ መንግሥት ትኩረት አድርጎ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጠው፣ ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር በየደረጃው መዘርጋትና ጠንካራ የለውጥ አመራር መገንባት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥታቸው በክልሉ እየታዩ የሚገኙ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችና እሰጥ አገባዎችን በማስወገድ፣ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍንና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በብቃት እንዲጠናቀቁ፣ የክልሉ ነዋሪዎች ሕይወት እንዲሻሻል፣ በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎና ድጋፍ በልዩ ትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጎልበት የማምረቻ ኢንዱስትሪ በማስፋፋት፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የቆየውን ዘርፈ ብዙ አንድነትና ወንድማማችነት ለማደስ፣ ለጋራ ሰላምና አንድነት ተግባብቶና ተዋዶ መሥራት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት መሆኑንም አምባቸው (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመሆን ተደጋግፎ መሥራት ለመላው ሕዝብ ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚቋደሱበት፣ ዜጎች ከሰቀቀን ተላቀው በነፃነት የሚዘዋወሩበት የሚያደርግ አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት መንግሥታቸው እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩት ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ የክልሉን ሕዝብ በመሩባቸው ዓመታት የክልሉን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ በዚህም የከተሞች ዕድገት፣ የመሠረተ ልማት፣ ኢንቨስትመንት ፍሰትና የአገልግሎት አሰጣጥ እመርታ ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ገዱ አርሶ አደሩን በመስኖ ልማት ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረጋቸውን፣ ከ200 በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ ማድረጋቸውን፣ በጤናው ዘርፍ መከላከልን መሠረት ያደረገ ውጤታማ ሥራ እንዲከናወን ማድረጋቸውንና በክልሉ የሆስፒታሎችን ቁጥር ከ20 ወደ 80 በመቶ ከፍ እንዲሉ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ድህነት፣ ሥራ አጥነትና ኑሮ ውድነት አሁንም የክልሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ ተንሠራፍቶ የቆየው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ አድሏዊ አሠራርና ምዝበራ የክልሉ ሕዝቦችን አብሮ የመኖርና የጋራ እሴት በማጥፋትና አገሪቱን ለከፋ ችግር ዳርጓት ቆይቷል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ገዱ፣ ይኼም ሕዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩና አብሮነታቸው እንዲሸረሸር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ይኼንን ድርጊት ለመቀልበስ በተደረገ ጥረት በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ መምጣት ቢችልም፣ አገራዊ ለውጡን ለመቀልበስና የቀድሞውን መረብ ለመመለስ በሚደረግ ጥረት፣ የዜጎች መፈናቀልና ግጭት መቀስቀሱን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር በመሆን አድሏዊ አሠራርንና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን ለመቀልበስ ባደረገው ትግል ድል ማስመዝገቡንም አቶ ገዱ አክለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመንና 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ እያለ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ዓርብ የካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ለአማራ ክልል ምክር ቤት መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡ ምክር ቤቱም ከተወያየበት በኋላ መልቀቂያውን በመቀበል በምትካቸው ከኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩትን አምባቸው መኮንን (ዶር)፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መርጧል፡፡ እሳቸውም ሹመቱን ተቀብለው ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ለመሥራት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

አምባቸው (ዶ/ር) የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቅምት ወር ባዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ በተለይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ይሾማሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሳይሾሙ መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ ካቢኔ የማዋቀሩ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላም፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው ሊሾሙ እንደሆነ ሲነገር የቆየ ቢሆንም፣ በተለይ የክልሉ የፖለቲካ አራማጆችና የቅርብ ጓደኞቻቸው፣ ‹‹ብዙ በመሥሪያህ ሰዓት በዚህ ቦታ መሾም የለብህም፤›› በማለት በመቃወማቸውና ተቃውሞውም በአብዛኛው የክልሉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ሳይሰየሙና ሳይመደቡ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

አምባቸው (ዶ/ር) ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳላቸው፣ ቆራጥ አመራርና ተራማጅ ሐሳብ አፍላቂ፣ ለአገርና ለሕዝብ ተቆርቋሪና እውነተኛ ታጋይ መሆናቸውንም በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡፡ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ፖሊሲና ኢኮኖሚክስ፣ በዓለም አቀፍ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ከደቡብ ኮሪያ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ከእንግሊዝ አገር የመጀመርያ፣ የሁለተኛና የሦስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በክልሉ በተለያዩ ቢሮዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች፣ በፌዴራል ደረጃ በሚኒስትርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች መሥራታቸው ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...