Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከያኒው የጥበብ ቤተ መዘክር ጌታቸው ደባልቄ (1928 - 2011)

ከያኒው የጥበብ ቤተ መዘክር ጌታቸው ደባልቄ (1928 – 2011)

ቀን:

በኢትዮጵያ በ1950ዎቹና በ60ዎቹ መጀመርያ በኪነ ጥበባት ዘርፍ እንደ ወርቃማ  ዘመንነት ይጠቀሳል፡፡ በቴአትር፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕል፣ ወዘተ ላቅ ያሉ ጠቢባንና ከያንያን፣ ደራስያን መፈጠራቸው ይወሳል፡፡

በዚያን የጥበብ ነፀብራቅ ዘመናት ውስጥ ብቅ ካሉት ሁለገብ ከያንያን አንዱ ጌታቸው ደባልቄ ይገኝበታል፡፡ የሙዚቃና የቴአትር ባለሙያ፣ ገጣሚና ደራሲ አዘጋጅም ነበር፡፡ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ኪነ ጥበቡን አገልግሏል፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት (1923 – 1967) ብሔራዊ የአገር ፍቅርንና ጀግንነት ስሜትን ለማጠናከርና ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ቁምነገሮችን እያዝናኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ ሙዚቃና ቴአትር ያላቸውን ጉልበት ስላመነበት ለያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ለዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ምሥረታ እንደ ጥንስስ የሚቆጠረውን የሙዚቃና የቴአትር ቡድንን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሥር በ1940ዎቹ አጋማሽ ሲያደራጅ ከታቀፉት ከያንያን አንዱ ጌታቸው ደባልቄ እንደነበር በኪነ ጠቢቡ ደበበ እሸቱ የቀረበው ገጸ ታሪክ ያስረዳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባ የመጀመርያው ዘመናዊ ቴአትር ቤት በ1948 ዓ.ም. በንጉሠ ነገሥቱ ስም ሲቋቋም ለቴአትር ቤቱ የመጀመርያ ዳይሬክተር የነበሩት ኦስትሪያዊው ፍራንስ ዞልቬከር በሙዚቃና ቴአትር ዘርፍ ካሠለጠናቸው የቴአትር ቤቱ መሥራች ባለሙያዎች መካከል 20 ዓመት ያልሞላው ጌታቸው ደባልቄ አንዱ ነበር፡፡

ለቴአትር ቤቱ የመጀመርያ በሆነውና በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት ቢትወደድ መኰንን እንዳልካቸው ተደርሶና በፍራንስ ዞልቬከር ተዘጋጅቶ በቴአትር ቤቱ ምረቃ ዕለት መክፈቻ ሆኖ በቀረበው ዳዊትና ኦሪዮን በተባለው ተውኔት፣ ጌታቸው ደባልቄ ከመጀመርያዎቹ ተዋንያን መካከል አንዱ ነበር፡፡

በቴአትር ቤቱ በተዘጋጁ ተውኔቶች ከያኒው ጌታቸው ከተወነባቸው ተውኔቶች መካከል የፍራንስ ዞልቬከር ሥነ ስቅለት ወይንም ወደ ክብር ጎዳና፣ የከበደ ሚካኤል አኒባል፣ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ቴዎድሮስ፣ የኬርቮክ ናልባንዲያን ጎንደሬው ገብረ ማርያም፣ የሞልዬር የፌዝ ዶክተር የፀጋዬ ገብረ መድህን የከርሞ ሰው፣ ሀሁ በስድስት ወር፣ የጎጎል ዋናው ተቆጣጣሪ፣ የመንግሥቱ ለማ ጠልፎ በኪሴ፣ የአያልነህ ሙላት ሻጥር በየፈርጁ፣ የሻምበል ፈቃደ ዮሐንስ ርጉም ሐዋርያ እንዲሁም ቀደም ሲል በማዘጋጃ ቤቱ የሙዚቃና ቴአትር ቡድን ውስጥ አባል በነበረበት ጊዜ ድንገተኛ ጥሪ፣ ዕድሜ ልክ እስራትና የፍቅር ጮራ የተሰኙትን ተውኔቶች ጨምሮ ጌታቸው ደባልቄ ከተጫወተባቸው 52 ተውኔቶች መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡

ጌታቸውና ኪነ ጥበብ የተዋወቁት በአዲስ ዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ዓመታት ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ ያዘጋጃቸው በነበሩ መዝሙሮች ጌታቸው በዘማሪነት ንቁ ተሳትፎ የነበረው ከመሆኑም በላይ፣ በትምህርት ቤቱ የወላጆች ቀን በተከበረ ዕለት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር በነበሩት በአቶ ቀነአ በጂ ተጽፎ በተዘጋጀው የአርበኞች ታሪክ ተውኔት ላይ ተዋናይ ሆኖ ተጫውቷል፡፡

ከያኒ (አርቲስት) ጌታቸው ደባልቄ የመጀመርያው የተውኔት ድርሰቱ በድሉ ዘለቀ የተሰኘውና በ1946 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሙዚቃና የቴአትር ቡድን ውስጥ በሚሠራበት ጊዜ ያቀረበው ነው፡፡ በ1953፣ በ1954 እና በ1962 ዓ.ም. ከተፎና መንጥር ያስቀመጡት ወንደላጤ፣ ደህና ሁኚ አራዳ የተባሉ ተውኔቶችን ከትሩፋቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡

 አበርክቶው በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በሙያ ዘመኑ ካዘጋጃቸው 15 ተውኔቶች መካከል የራሱ ድርሰት የሆነው ደህና ሁኚ አራዳ፣ የመክብብ ጌታቸው ትርጉም የሆነው የሞልየር የከተማው ባላገር፣ የግርማ ዘውዴ ለሰው ሞት አነሰው፣ የደስታ ገብሩ ምኞቴ፣ የመሪጌታ አዕምሮ ፈረደ ፍቅር መጨረሻና የማሞ ውድነህ አሉላ አባነጋ ይገኙባቸዋል፡፡

በግጥምና ዜማ ድርሰትም ተሰጥኦ የታደለው ከያኒው ጌታቸው ትውልድን መሻገር ከቻሉ የሙዚቃ ሥራዎቹ በግጥሙ ይዘት ለእስር የተዳረገበት ሎሚ ተራ ተራ፣ ተከታታይ ትውልዶች ያቀነቀኑት እንገናኛለን፣ አደረች አራዳ፣ የኔ ሐሳብ፣ ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ ይገኙበታል፡፡

ኪነ ጠቢቡ ያኒው ጌታቸው የጥበብ ቤተ መዘክር ያሰኘው ማስታዎሻዎቹ ለመጪው ትውልድ ለማሸጋገር መጣሩ ነው፡፡ እስር ቤት በቆየበት ጊዜ የገጠመውንና የታዘበውን ደንቆሮ በር በሚል ርዕስ መጽሐፍ ጽፎ ለኅትመት ያበቃ ሲሆን የሁለገቧ ከያኒት አስናቀች ወርቁን የሕይወት ታሪክንም አሳትሟል፡፡

ጌታቸው ደባልቄ ከኪነ ጥበብነት ባለፈ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቴአትር ክፍል ኃላፊ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ጌታቸው ገና በጮርቃ ዕድሜ በትውልድ ከተማው አዲስ ዓለም ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ፊት ቀርቦ ባቀረበው ግጥም የተሸለመው ሦስት ሽልንግ በሙያ ካደገና ከጎለመሰ በኋላ በድጋሚ ገንዘብና ወርቅ መሸለሙ ገጸ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ትልቁ ሽልማቱ በ1994 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኃን ሽልማትን በቴአትር ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ለመሆን የበቃበት ነው፡፡

የጥበብ ቤተ መዘክሩን ጌታቸው ደባልቄን በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን፣ በአገር ውስጥና በውጪ አገር የታሪክ ተመራማሪዎች፣ በጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች ዘንድ እጅግ ተወዳጅና ተፈላጊ ያደረገው ስለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ታሪክ ቋሚ መዝገብ ስለነበረ ነው፡፡ የመረጃ ምንጭ ነበርና፡፡

ከአባቱ ከአቶ ደባልቄ አምበርብርና ከእናቱ ወ/ሮ አሰገደች ወልደ ገብርኤል በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ መናገሻ አውራጃ፣ አዲስ ዓለም ከተማ ልዩ ስሙ ነጋዴ ሠፈር ሚያዝያ 20 ቀን 1928 ዓ.ም. የተወለደው ከያኒ ጌታቸው ደባልቄ፣ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከመጀመርያው ትምህርት እስከ ድጓና ጾመ ድጓ ሲዘልቅ፣ በቀለም ትምህርት በትውልድ ከተማው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን ካጠናቀቀ በኋላ በአዲስ አበባ ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃን ትምህርትን ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም እስከገባበት ድረስ ተከታትሏል፡፡

በተወለደ በ83 ዓመቱ የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ያረፈው ኪነ ጠቢቡ ጌታቸው ደባልቄ ሥርዓተ ቀብር የካቲት 24 ቀን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመድና የጥበቡ ቤተሰብ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡ ኪነ ጥበቡ ጌታቸው የሁለት ሴት ልጆችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...