Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከመከላከያ ሠራዊቱ ውጪ የሆኑ ሕግ አስከባሪ አካላት መታጠቅ የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት...

ከመከላከያ ሠራዊቱ ውጪ የሆኑ ሕግ አስከባሪ አካላት መታጠቅ የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት የሚወሰን ሕግ ተረቀቀ

ቀን:

ከ21 ዓመት በላይ የሆነ ጤነኛ ሰው ለግለሰብ የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ ፈቃድ በማውጣት ሊታጠቅ ይችላል

በጦር መሣሪያ ንግድና በድለላ ለሚሰማሩ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ይሰጣል

ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በስተቀር ሌሎች በክልል መንግሥታትና በፈዴራል መንግሥት የተደራጁ ሕግ አስከባሪ አካላት፣ መታጠቅ የሚችሉትን የጦር መሣሪያ ዓይነት የሚወስን ረቂቅ ሕግ ተጠናቆ ለውይይት ቀረበ።

- Advertisement -

ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር በተዋቀረ የሕግና ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ የቴክኒክ ዕውቀት ባላቸው የባለሙያዎች ቡድን ሲሆን፣ የሕግ ሰነዱ ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል።

ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ የሕግ ሰነድ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር አዋጅ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፣ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የአገርንና የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የዜጎችንና የሕዝቦችን መብትና ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተረቀቀ መሆኑን የሰነዱ መግቢያ ያስገነዝባል። በማከለም ግለሰቦች የታጠቋቸው የጦር መሣሪያዎች የኅብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ብቻ ሊውል የሚቻልበትን አሠራር መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ እንዲሁም በሥራ ላይ ባሉ ሕጎችና አሠራሮች ያልተሸፈኑ ጉዳዮችን በዝርዝር ሕግ መደንገግና ወጥነት ያለው ሥርዓት መፍጠር በማስፈለጉ ሕጉ መዘጋጀቱን የሕግ ሰነዱ መግቢያ አንቀጾች ያስረዳሉ።

ረቂቅ ሕጉ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት የሚፈቀድ የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛትን የሚደነግግ ሲሆን፣ የሕግ (ፀጥታ) አስከባሪ አካላት ለሚለውም የሕግ ትርጓሜ አካቷል።

‹‹ሕግ አስከባሪ ማለት የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሲሆኑ፣ በፖሊስ አካላት የአካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር የሚደራጁ የግል ታጣቂዎችን ይጨምራል፤›› ሲል ሕጋዊ ትርጓሜ ይሰጣል፡፡

እነዚህ ሕግ አስከባሪ የፀጥታ አካላት ሊታጠቁ የሚችሉት የጦር መሣሪያ ዓይነቶች በመወሰንም የጦር መሣሪያ ዓይነቶቹን ይዘረዝራል።

በዚህም መሠረት ሕግ አስከባሪ የፀጥታ አካላት በረቂቅ ሕጉ ተወስኖ እንዲታጠቁ የተፈቀደላቸው የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ሽጉጥ፣ አውቶማቲክ ያልሆነ ወይም ግማሽ አውቶማቲክ የሆነ ጠብመንጃ፣ ቦምብና ሌሎች ተያያዥ ዕቃዎች ሊሆኑ እንደሚችል ረቂቁ ይገልጻል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት ‹‹አውቶማቲክ ያልሆነ ጠብመንጃ›› ማለት አንድ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የማይችል ማለት ሲሆን፣ ‹‹ግማሽ አውቶማቲክ ጠብመንጃ›› ማለት ደግሞ አንድ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የሚችል እንደሆነ በረቂቁ የቃላት ትርጉም ክፍል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

በዚሁ የረቂቁ የቃላት ትርጓሜ መሠረት ‹‹ሙሉ አውቶማቲክ ጠብመንጃ›› ማለት ከአንድ በላይ አፈሙዝ ኖሮት ምላጩ ሲሳብ የሚተኩስና አንድ ጊዜ ሲተኮስ በራሱ ማቀባበል የሚችል ሲሆን፣ ይኼንን ዓይነት መሣሪያ የክልል የሕግ አስከባሪ አካላት መታጠቅ እንደማይችሉ በረቂቅ ሕጉ በክልከላነት ተቀምጧል።

ይሁን እንጂ የፌደራል ፖሊስ አባላት ለሥራቸው በሚያስፈልገው መጠን ከቀላልና ከአነስተኛ የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ውስጥ ተመርጦ እንዲታጠቁ ሊፈቀድ እንደሚችል፣ የዚህም ዝርዝር የረቂቅ አዋጁን መፅደቅ ተከትሎ በሚወጣ ደንብ እንደሚወሰን ይገልጻል።

በሌላ በኩል የሰላም ሚኒስቴር ለእያንዳንዱ የሕግ አስከባሪ ተቋም እንደ ሁኔታው ለሥራው የሚያስፈልገውንና የሚፈቀደውን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና አስተዳደር በተመለከተ ዝርዝር የአፈጻጸም መመርያ በማውጣት እንዲወስን ረቂቅ ሕጉ ሥልጣን ይሰጠዋል።

የፀጥታ አስከባሪ ተቋም አባላት የጦር መሣሪያ የሚይዙት በተቋማቸው ለሥራቸው አስፈላጊ ሆኖ ሲሰጣቸው እንደሆነ የሚገልጽ ረቂቅ ድንጋጌ የሕግ ሰነዱ የያዘ ሲሆን፣ እነዚህ የሕግ አስከባሪ አባላት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የተቋማቸውን የደንብ ልብስ መልበስ ወይም ፈቃዳቸውን ወይም እንደ አግባብነቱ የሥራ መታወቂያ ወረቀት መያዝ እንደሚኖርባቸውም ያመለክታል።

የሕግ አስከባሪ ተቋማቱ አባላቶቻቸው የጦር መሣሪያን እንዲይዙ የሚፈቅዱት ተቋማትን ለመጠበቅ፣ የሕግ ማስከበር ሥራ ወይም ኦፐሬሽን ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ፣ የኃይል ተግባር ሊያጋጥም ይችላል በሚል እምነት ለሥራ ሲሰማሩ፣ ለራስ መጠበቂያ ያስፈልጋቸዋል በሚል ምክንያት እንዲታጠቁ ሲያስፈልግ ብቻ እንደሆነም የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚታጠቁትን የጦር መሣሪያ ዓይነት፣ ብዛትና የአጠቃቀሙንም ሁኔታ በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን የአገር መከላከያ ተቋሙ የጦር መሣሪያ አጠባበቅ፣ አያያዝና ክምችት በተመለከተ ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበትና ለአባላት የሚሰጠውን የጦር መሣሪያና ጥይት የክትትል ሥርዓት ሊኖረው እንደሚገባ ይደነግጋል።

ይኸው ረቂቅ ሕግ ግለሰቦች የጦር መሣሪያ ለመታጠቅና ለመገልገል የሚችሉባቸውን የሕግ አግባቦችንም አካቶ ይዟል።

በዚህም መሠረት የአዕምሮ ሁኔታው የተስተካከለና አላስፈላጊ የኃይል አጠቃቀም ባህሪ የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው ተቆጣጣሪ ተቋም የታመነበት ማንኛውም ዕድሜው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ያለው ሰው፣ የጦር መሣሪያ የመያዝና የመገልገል ሕጋዊ ፈቃድ ሊያገኝ እንደሚችል ያመለክታል።

ከዚህ አኳያ የተጨማሪ መመዘኛዎች አመላካች የሆኑ መሥፈርቶች በረቂቅ ሕጉ የተካተቱ ሲሆን፣ የአደገኛ ዕፅ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበት፣ ቋሚ አድራሻና መተዳደሪያ ወይም ገቢ ያለው፣ በሙሉ ወይም በከፊል በፍርድ ወይም በሕግ ችሎታውን ያላጣ፣ የጦር መሣሪያን አጠቃቀምና በዚህ በሕግ የሚጣልበትን ግዴታ በተመለከተ ግንዛቤ ያለው፣ ወይም ትምህርት የሚወስድ ለመሆኑ በተቆጣጣሪው ተቋም የታመነበት ሊሆን እንደሚገባ ይዘረዝራል።

ለግለሰብ የሚፈቀደው የጦር መሣሪያ አንድ ሽጉጥ ወይም አንድ አውቶማቲክ ያልሆነ ጠብመንጃ ወይም አንድ ግማሽ አውቶማቲክ ጠብመንጃ ብቻ መሆኑን፣ የተፈቀደው የጥይት ብዛት የሰላም ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ እንደሚወሰን ይደነግጋል።

ራሳቸውን ለመከላከልና የአካባቢያቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ በተለምዶ የጦር መሣሪያ የሚያዝባቸው አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑና የጦር መሣሪያ የያዙ ሰዎች፣ የያዙት የጦር መሣሪያ በረቂቅ ሕጉ ለግለሰብ ያልተከለከለ የጦር መሣሪያ ዓይነት እስከሆነ ድረስ፣ ሕጉ ከፀደቀ በኋላ በሚወጣ የጊዜ ሰሌዳ በየአካባቢው ሥልጣን ወደተሰጠው ተቋም በአካል ቀርበው ፈቃድ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውና ለአንድ ሰው የተፈቀደውም አንድ የጦር መሣሪያ ብቻ እንደሆነ የረቂቁ ድንጋጌዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል የሕግ ሥልጣን በሚሰጠው አካል መሥፈርቶችን አሟልተው ፈቃድ ማግኘት የሚችሉ አካላት የጦር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ከአገር ማስወጣት፣ ማከማቸት፣ መሸጥ፣ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሠልጠን ወይም መጠገን በሚያስችላቸው የንግድ ሥራዎች መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ በረቂቅ ሕጉ ተካቷል።

በተጨማሪም በተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል ሕጋዊ ፈቃድ በማውጣት የጦር መሣሪያ ኤግዚቢሽን ለማሳየትና ከተሠሩ ሃምሳ ዓመት ያለፋቸው የጦር መሣሪያዎችን በቅርስነት ለመያዝ፣ የጦር መሣሪያ በአገር ውስጥ የመደለል ሥራ ለማከናወን እንደሚቻል ያመለክታል።

ሪቂቅ ሕጉን የተመለከቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደኅንነት ባለሙያዎች፣ የሕግ ሰነዱ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና በአገሪቱ የሚስተዋለውን የተዝረከረከ የጦር መሣሪያ አያያዝና አጠቃቀም ፈር ሊያስይዝ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ረቂቅ ሕጉን ልዩ የሚያደርገው በፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የክልል መንግሥታት ኃይልን የመጠቀም ሕጋዊ መብት በልኩ በማስቀመጥ፣ የፌዴራል መንግሥት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ከፍ ያለ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻሉ።

ረቂቅ ሕጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት ከዳበረ በኋላ የሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን ጠብቆ ዘንድሮ  እንደሚፀድቅ ለማወቅ ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...