Thursday, June 20, 2024

ከሶማሌ ክልል ሁከት ጋር በተያያዘ ታስረው የነበሩት ነጋዴ በሙስና ተከሰሱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና በሌሎች የዞንና የወረዳ ከተሞች ውስጥ በነበረው ግድያ፣ አካል ማጉደል፣ ማፈናቀል፣ የሃይማኖት ተቋማት ቃጠሎ፣ ንብረት ዘረፋና ውድመት ምክንያት ተጠርጥረው የተያዙት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) እና ሦስት ግለሰቦች የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

በወቅቱ በክልሉ አጋጥሞ የነበረውን ሁከት በፌስቡክ ገጻቸው በማባባስና የተለያዩ ቀስቃሽና አባባሽ ጽሑፎችን በቲሸርት ላይ በማተም ተጠርጥረው ከሦስት ወራት በፊት የታሰሩ ቢሆንም፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተጨባጭ ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ባለመቻሉ ክስ ሊመሠረትባቸው ስላልተቻለ ፍርድ ቤት በ80 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዶላቸው ነበር፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ከእስር ሳይፈቱ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ ግለሰቡ በክልሉ ከሚገኘው የኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዲ ዩሱፍ፣ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድና የቢሮው የፋይናንስና የሎጂስቲክስ የሥራ ሒደት ባለቤት ጋር በመመሳጠር የ15.3 ሚሊዮን ብር ሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤት ገልጾ ዋስትናውን አስከልክሏቸዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ የሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ መሆናቸውን የገለጸው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረበባቸው ክስ፣ ለክልሉ የመጀመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 578,274 መጻሕፍት በ18,990,000 ብር አትመው ለማስረከብ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር ውል መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡

ከቢሮው ጋር ለገቡት ውል በክልሉ የሚገኘው ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋስትና መስጠቱንም ጠቁሟል፡፡ ቅድሚያ ክፍያ 15,306,803 ብር በተለያዩ ቼኮች የተፈጸመላቸው ቢሆንም፣ መጻሕፍቱ ታትመው ሊቀርቡ አለመቻላቸውንና ዋስትና የገባውም ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ እንደ ውሉ ሊያስፈጽም አለመቻሉን በክሱ አብራርቷል፡፡ መጻሕፍቱ በወቅቱ ባለመቅረባቸው በመማር ማስተማር ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሞ፣ አራቱም ግለሰቦች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀል ልዩ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 (1ሐ እና 3) ላይ የተደነገገውን በመተላለፋቸው፣ በፈጸሙት የመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጀቶች ሥራን በማያመች አኳኃን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ክሱን ለተከሳሾች በችሎት አንብቦ የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ የማረሚያ ቤት አያያዛቸውን በሚመለከት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ እንደተናገሩት፣ ስማቸው በፌስቡክ ስለጠፋ እስር ቤት ያገኟቸው ሌሎች እስረኞች አንገታቸውን አንቀዋቸው (አንገታቸውን ለችሎቱ አሳይተዋል) ሊገድሏቸው ነበር፡፡ በመሆኑም አንቀዋቸው የነበሩ እስረኞች ቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ስለሄዱ፣ ወደዚያ ከተላኩ ለሕይወታቸው እንደሚያሠጋቸው በመናገራቸው፣ በቃሊቲ እስር ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -