Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ተከሰሰ

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ተከሰሰ

ቀን:

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ የ20 ዓመታት አስገዳጅ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃድ ውል በመሰረዝ፣ ለሌላ ድርጅት ሰጥቷል ተብሎ የፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተበት፡፡

ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ቀጥታ ክስ ፍትሐ ብሔር ችሎት የተመሠረተው ክስ እንደሚስረዳው፣ በኤጀንሲው ላይ ክስ የመሠረተው ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ በክሱ እንደገለጸው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ማጣ ቀበሌ ውስጥ ልዩ ስሙ አከን በተባለ ቦታ፣ ጥቅምት 3 ቀን 1996 ዓ.ም. የ20 ዓመታት አስገዳጅ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃድ መውሰዱን በክሱ ገልጿል፡፡ ጢስ ዓባይ ፈቃዱን ከወሰደ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት የማዕድን ማምረት ሥራውን በማከናወን ላይ እንደነበርም ገልጿል፡፡

ማኅበሩ ከክልሉ መንግሥት ማዕድን የማምረት ፈቃዱን እንዳገኘና ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ ብድር በመውሰድና ከፍተኛ ማሽነሪዎችን በመትከል ሥራውን እንደጀመረ ጠቁሞ፣ ለአካባቢ ነዋሪዎችም የመሠረተ ልማት ሥራዎችን መሥራቱን ገልጿል፡፡ በወቅቱ ወደ ማዕድን ሳይቱ የሚያስገባ ምንም ዓይነት መንገድ ባለመኖሩ 12 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ፣ የውስጥ ለውጥ መንገዶች ግንባታ፣ የ1.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ 500 ሜትር ውስጥ ለውስጥ የውኃ መስመር ዝርጋታ፣ የተለያዩ ከፍተኛ ማምረቻ መሣሪያዎችና የጄኔሬተር ተከላ፣ የሠራተኞች መኖሪያ ቤቶች፣ ቢሮዎችና የጥበቃ ማማዎችን በከፍተኛ ወጪ መገንባቱን በክሱ አብራርቷል፡፡

ማኅበሩ በክሱ በስፋት እንዳብራራው፣ የጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻ የአቶ ሽባባው ወሌ መሞትን ተከትሎ ተፈጥሮ በነበረው የአመራር መተካካት ክፍተት፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ሆኖ የተጠቀሰው ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በክልሉ የማዕድን ሥራ ለመሥራት ማመልከቱን ጠቁሟል፡፡ ቤአኤካ የተባለው ድርጀት ለክልሉ የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ የማዕድን ምርመራ ለማካሄድ የጠየቀው፣ ቀደም ብሎ ጢስ ዓባይ በወሰደው ይዞታ (ቦታ) ላይ መሆኑን ኤጀንሲው ሲያውቅ ጥያቄውን ወዲያው ውድቅ ማድረግ ሲገባው፣ ሒደቱን ሕጋዊ በማስመሰል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹ይገባኛል የሚል ተቃዋሚ ካለ›› በማለት ጥሪ ማድረጉ ሕገወጥ ተግባር መሆኑን አስረድቷል፡፡

ኤጀንሲው ያወጣው የጋዜጣ ጥሪ ሕገወጥ ቢሆንም ጢስ ዓባይ ግን በሁለተኛው ቀን፣ ‹‹ጥሪ የተደረገበት ቦታ በክልሉ መንግሥት በተሰጠ ሕጋዊ የማዕድን ማምረት ፈቃድ የተያዘና ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በማስያዣነት የተሰጠ ነው፤›› በማለት ተቃውሞውን አቅርቦ እንደነበር በክሱ ገልጿል፡፡ ኤጀንሲው በአዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 14(3) ድንጋጌ መሠረት፣ በ15 ቀናት ውስጥ ጢስ ዓባይ ላቀረበው መቃወሚያ መስጠት ሲገባው፣ ከሦስት ወራት በኋላ በሰጠው ምላሽ ለቤአኤካ የተሰጠው የማዕድን ምርመራ ጥያቄ ከእሱ ይዞታ ጋር የማይደራረብ መሆኑን ገልጾ፣ ማረጋገጫ ደብዳቤ ጽፎለት እንደነበርም ጠቁሟል፡፡

ነገር ግን ኤጀንሲው ኅዳር 20 ቀን 2011 ዓ.ም. የራሱን ባለሙያዎችና የቤአኤካ ተወካዮችን ወደ ጢስ ዓባይ ይዞታ በመላክ፣ በማስፈራራትና በጉልበት የችካል ሥራ መሥራታቸውን በክሱ ጠቁሟል፡፡ ጢስ ዓባይ ያለማውን የማዕድን ቦታ ለቤአኤካ በከፍተኛ ሁከት መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጾ ኤጀንሲው እንዲያስቆምለት ቢጠይቅም፣ ኤጀንሲው ፈቃደኛ ካለመሆኑም በተጨማሪ የመከተል ዞን ቡለን ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ እንደጻፈለት ገልጿል፡፡ የወረዳው አስተዳደር በጻፈለት ደብዳቤ እንደገለጸለት፣ ሲሠራ የቆየው ባልተሰጠው ይዞታ ላይ መሆኑን ጠቁሞ በይዞታው ላይ የሚገኙ ንብረቶችን በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲያነሳ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ነገር ግን ይዞታው የወረዳው ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ የከፍተኛ ደረጃ የማዕድን ማምረት ፈቃድ ውል የተሰጠ የማኅበሩ መሆኑንና በባንክም በማስያዣነት የተወሰደ እንደሆነ ማሳወቁንም ማኅበሩ በክሱ ጠቁሟል፡፡

ጢስ ዓባይ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለወረዳው፣ ለኤጀንሲውና ለክልሉ መንግሥት የደረሰበትን በደል በመግለጹ፣ ኤጀንሲው ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር የጀመረውን ሥራ ለጊዜው አግዶት እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ በመቀጠልም ለክልሉ ማዕድን ልማት ቦርድ ዕገዳው ከመነሳቱ በፊት ዝርዝር ሁኔታውን በመግለጽ አቤቱታ ቢያቀርብም፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሰብሳቢ የሆኑበት ቦርድ፣ በ1994 ዓ.ም. የወሰደውን ፈቃድ እንዲመልስና በ1996 ዓ.ም. የተሰጠውን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በመመለስ የ20 ሔክታር የቦታ ስፋት ውል እንዲገባ የሚያስገድድ ውሳኔ መስጠቱን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ በ1994 ዓ.ም. የወሰደው ፈቃድ እንደሌለ ጠቁሟል፡፡ ሌላው ድርጅት ውል በፈጸመበት ለባንክ አስይዞ ብድር የወሰደበትን ይዞታ ከመስጠት ይልቅ እንደመሰረዝ፣ ቦርዱ የፈቃድ መደራረብ እንዳለ እያወቀ የሰጠው ውሳኔ ተገቢ ስላልሆነ እንደገና እንዲታይለት ጠይቋል፡፡

ለ20 ዓመታት የሚቆይ አስገዳጅ ውልና አግባብነት ያላቸው የፌዴራልና የክልል ሕጎች ተቃራኒ የሆነ ውሳኔ ከመስጠቱም በተጨማሪ፣ ለቤአኤካ ድርጅት ይዞታ ወጪ 20 ሔክታር የቦታ ስፋት የሚገልጽ የጂኦግራፊ ኮኦርዲኔትና ካርታ ይዞ እንዲቀርብና አዲስ ውል እንዲፈጽም መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ ለሁለተኛው ድርጀት የተሰጠው ቦታ በጢስ ዓባይ ይዞታ ላይ መደረቡ በቦርድ ጭምር ተረጋግጦ እያለ ፈቃድ መስጠቱ ሕገወጥነት መሆኑንም አስረድቷል፡፡

በአጠቃላይ የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ስለማዕድን ሥራዎች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 182/86፣ የመሬት ኪራይ የፈቃድ፣ የሮያሊቲ ክፍያዎችንና ሌሎች ጉዳዮችን ለመወሰን የወጣውን ደንብ ቁጥር 117/2010 አንቀጽ 13 (1ሀ) እና ተደርቦ የተሰጠ ፈቃድ በሚኖርበት ጊዜ ፈቃድ ቀድሞ ባገኘው ሥር ይዞታው እንዲቀጥል የሚፈቅደውን አዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 37 (2)ን ድንጋጌ የሚጥስ ተግባር መሆኑን በክሱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ቤአኤካ የተባለው ድርጅት ከክልሉ ማዕድን ልማት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ከጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በያዘው ሕጋዊ ይዞታ ላይ ሕገወጥ ግንባታ በማከናወን ላይ መሆኑንና ማዕድን የማምረት ሥራ ለማከናወንና ሕጋዊ ይዞታውን ለመንጠቅ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ፣ እየተፈጸመበት ያለው ሁከት እንዲወገድለት ጠይቋል፡፡ የተፈጸሙበት የውልና የሕግ ጥሰቶች በፍርድ ቤት እንዲታረሙለት ጠይቋል፡፡ ኤጀንሲው ክሱ ደርሶት ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን፣ የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ዩሱፍ አልበሽር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...