Friday, May 24, 2024

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዕድገት ለምን ጎዶሎ ሆነ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ መርሁን ሰንቆ በ1983 ዓ.ም. የፖለቲካ ሥልጣንን በኢትዮጵያ የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ፣ የሥልጣን መንበሩን በያዘ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነቱን ለመግለጽ ከተጠቀመባቸው መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት፣ እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፉን ኢትዮጵያውያን በነፃነት እንዲሰማሩበት ሕግ መደንገጉ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በተመሳሳይ ወቅት ነፃነትን ያገኙት እነዚህ ሁለት ሙያዊ ዘርፎች ባህሪያቸው የተለያየ ቢሆንም፣ ሁለቱም ግን በአንድ አገር ፖለቲካዊ ማኅበረሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ የጎላ ተፅዕኖ ማሳደር የሚያስችል የራሳቸው የሆነ ኃይልና ጉልበት አላቸው፡፡

በአንድ ተመሳሳይ የጊዜና የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ በተወለዱት እነዚህ ሁለት የሙያ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ውጭ የሆነ ሀብትን እንዳይጠቀሙ በሕግ ተገድበው፣ በተፈቀደላቸው መስክ ከሞላ ጎደል ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ያደረጉት ጉዞ ሲመዘን ልዩነቱ የሰማይና የምድርን ያህል መሆኑን በድፍረት መግለጽ ይቻላል፡፡

 ነባር ከሆኑት የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ፣ ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ግድም በተለያዩ ዓመታት የተመሠረቱ 16 የግል ባንኮች በአሁኑ ወቅት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ 16 ባንኮች እስከ 2011 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ በከፈቷቸው  3,472 ቅርንጫፎቻቸው ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 311.2 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ አጠቃላይ የካፒታል መጠናቸው ደግሞ 34.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ በዚህ ዓመት አጋማሽ ተመዝግቧል፡፡ በመሆኑም የፋይናንስ ዘርፉ ዛሬ የአገሪቱ ግዙፍ ኢንዱስትሪ መሆን ሲችል፣ አብሮት በአንድ ወቅት የተወለደው የመገናኛ ብዙኃን (የጋዜጠኝነት) ዘርፍ ግን ከ26 ዓመታት በላይ ዕድሜን ቢያስቆጥርም በጨቅላነቱ የቀነጨረ፣ ወደ ሚዲያ ኢንዱስትሪነት ሊቀየር ይቅርና ሚናውንም መለየት የተሳነው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

የጀርመን መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ፍሬደሪክ ኤበርት ስቲፍተንግ የአዲስ አበባ ቢሮ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ሚና ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታ›› በሚል ርዕስ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የፎርቹን ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት የሆነው ‹‹ኢንዲፕንደንት ኒውስ ኤንድ ሚዲያ›› ኩባንያ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት፣ በአንድ ተመሳሳይ ወቅት በእኩል ሥራ የጀመሩት የሚዲያና የፋይናንስ ተቋማት ስኬት ለምን የሰማይና ምድር ያህል ተራራቀ? የፋይናንስ ዘርፉ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ወደ መሆን ሲሸጋገር የሚዲያ ዘርፉ ባለበት ለምን ቆሞ እንደቀረ ይጠይቃሉ፡፡ ሁለቱም ዘርፎች የካፒታል ምንጫቸውን ከኢትዮጵያ ብቻ እንዲያደርጉ በሕግ ተገድበው የሥራ መስኮቹ ቢፈቀዱላቸውም፣ የሚዲያ ዘርፉ ግን የካፒታል ደሃ ሆኖ እንደጀመረ ይገልጻሉ፡፡ የሚዲያ ዘርፉ በካፒታል ደሃ ሆኖ እንዲጀምር ያደረጉት ፖለቲካዊ ምክንያቶች መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም እንደ ጨቅላነቱ እየዳኸ እንዲገኝ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ሲጠቀልሉም፣ ‹‹ሚዲያው ሥልጣን የሚያይበት፣ ሥልጣንም ሚዲያውን የሚያይበት፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ሚዲያውን የሚያይበት አተያይ የማይታረቁ ጽንፎች በመሆናቸው ነው፤›› ይላሉ፡፡

ይኼንንም በዝርዝር ሲያብራሩ የግል ሚዲያው ሲጀምር የፖለቲካ ሥልጣን ለውጥ አመጣለሁ ወይም ማምጣት አለብኝ ብሎ ከመንግሥት ወይም ከሥልጣን ጋር ግብግብ ውስጥ እንደገባ፣ በዚህ የተጀመረው ነገር አሁንም ዕይታውን እንዳልቀየረ ይገልጻሉ፡፡

በተቃራኒው ደግሞ መንግሥት ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የግል ሚዲያውን የሚያየው እንደ ጠላት እንደሆነ፣ ከዚህ ባላንጣ ጋር መሥራት አይቻልም ብሎ በማመን በቁጥጥሩ ሥር ያሉትን የመንግሥት (የሕዝብ) መገናኛ ብዙኃን የሥልጣን መገልገያ መሣሪያው እንዳደረጋቸው፣ በዚህም ምክንያት የግልና የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት ግንባር ለግንባር ሆነው ፍልሚያ ውስጥ በመግባታቸው፣ በኢትዮጵያ የሚዲያ ተቋምና የሚዲያ ኢንዱስትሪ መገንባት እንዳልተቻለ ያስረዳሉ፡፡

የግሉ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ የሚያገለግሉ ጋዜጠኞችም ሙያዊ ሥነ ምግባርንና ብቃትን የተላበሱ እውነተኛ መረጃ አቅራቢዎች ሳይሆኑ፣ ጦርኛ (Militant) ጋዜጠኞች ናቸው ይሏቸዋል፡፡

አቶ ታምራት በጥናታቸው ያቀረቡትን ይኼንን ሐሳብ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ የተለያዩ የኢሕአዴግ ሰነዶች በግልጽ ያንፀባርቋቸዋል፡፡

ለአብነት ያህል ከሚጠቀሱት ውስጥ በ1993 ዓ.ም. በቀድሞው የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የተጻፈው ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመራርና የአሠራር ጥበብ›› ሰነድ፣ ‹‹በአገራችን ያሉትን ሚዲያዎች ሁኔታ ስንመለከት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ልዕልና በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ችግሮች እንዳሉባቸው እንመለከታለን፤›› ይላል፡፡

በማከልም የሚዲያ ዘርፉ ከባለቤትነት አንፃር ሲታይ ቁልፍ ሚና አሁንም በመንግሥት እጅ የሚገኝ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ ዘርፉ ሲገመገም ግን ሚዲያ እንደ ቁልፍ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ማሰራጫ ሆኖ ተሽመድምዷል ሲሉ ጽሑፉ ይገልጻል፡፡ የግል ሚዲያዎች ከሕግ ውጪ የሚሠራ እስከሆነ ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጫወቱት አዎንታዊ ሚና ሊኖር ስለማይችል በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ በአስተዳደራዊ መንገድም ጭምር ‹‹በጥብቅ እንታገላቸዋለን›› ይላል፡፡ በመንግሥት ሚዲያዎች ውስጥ የተመደቡ አመራሮችና አዘጋጆች የጋዜጠኝነት ብቃታቸው በእጅጉ የዘቀጠ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባቸውም ሽባ የሆነ፣ ወይም ፀረ አብዮታዊ ዴሞክራሱ መሆኑን ያስረዳል፡፡

‹‹በዚህ ረገድ የተቀላጠፈና ዘላቂ መሻሻል ካላመጣን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ልዕልና የማምጣት ትግላችን ሊራመድ አይችልም፡፡ ስለዚህም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በጥልቀት የገባቸውን አመራሮችና ኤዲተሮች ለመመደብ መንቀሳቀስ አለብን፤›› ሲል የአቶ መለስ ጽሑፍ ያሳስባል፡፡

አቶ ታምራት ባቀረቡት የጥናት ወረቀት በግሉ ሚዲያና ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት መካከል የተፈጠረው ባላንጣነትና ግብግብ እስካሁን እንደቀጠለ፣ የመንግሥት የሚዲያ ተቋማትም ሥልጣን ላይ ያለው ኃይል መጠቀሚያ መሣሪያ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ የግል ሚዲያዎችን በማዳከም የመንግሥት ሥልጣን ወገን የበላይነትን እንደያዘ፣ ማኅበረሰቡም ስለሚዲያ ግዴለሽ እንደሆነ አድርጎ መንግሥት የሚገነዘብ መሆኑ ዘርፉን በድምር ውጤት እንዳዳከሙት ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29 ማንም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት የመናገር መብት እንዳለውና የሚዲያ ነፃነትም በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግለት እንደሚደነግግ አስታወሰው፣ ይሁን እንጂ የወጣቶችን ደኅንነትና የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር ለመጠበቅ ሲባል፣ እንዲሁም የጦርነት ቅስቀሳ የማይቻል መሆኑን በመግለጽ የመናገር የሚዲያ ነፃነት ላይ የተገለጹት ገደቦች ብቻ ጥሎ ነፃነትን እንዳጎናፀፈና ነፃነቱም በሕግ ጥበቃ የተደረገለት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ የአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል እ.ኤ.አ. በ2005 የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉን ሲያሻሽል በሕገ መንግሥቱ ጥበቃ የተደረገበትን የመናገርና የሚዲያ ነፃነት የሚሸረሽር ድንጋጌ ማስቀመጡን፣ በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ሕገ መንግሥቱ የሚሰጠውን ነፃነት የሚሸረሽሩ 33 የሚሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች በተለያዩ ሕጎች ተካተው በሕግ አውጪው መፅደቃቸውን ያስረዳሉ፡፡

እነዚሀን ጉዳዮች በመጠቀም መንግሥት ተቀናቃኝ ናቸው የሚላቸውን የግል ሚዲያ ጋዜጠኞች በመክሰስ ማሰሩን፣ ይኼንን ፍራቻም ስደትን የመረጡ መኖራቸውን አውስተዋል፡፡

የግሉ ሚዲያም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ ሙያተኞች ሙያዊ ብቃትና ክህሎት፣ እንዲሁም የሙያውን ሥነ ምግባር ጠብቀው ይንቀሳቀሱ ነበር ማለት እንደማይቻል፣ በዚህም ምክንያት ሥልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር ግብግብ ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡

የአገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ በአጠቃላይ የጠራ ተልዕኮና ግብ ከጋዜጠኝነት ሙያ አንፃር እንዳልነበረውና አሁንም እንደሌለው፣ ይህንንም ሁኔታ በሥራ ላይ ያሉትን የክልል የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

አገሪቱ ላለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት የሚዲያ ፖሊሲ እንደሌላት የሚገልጹት አቶ ታምራት፣ የሚዲያ ዘርፉ በአንድነት ሆኖ የራሱን ተልዕኮና ግብ ያለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት መወሰን የነበረበት ቢሆንም ይኼንንም ማድረግ እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ ተወያይ የነበሩ ባለሙያዎች አቶ ታምራት ባነሱት ሐሳብ ላይ ተንተርሰው የተለየዩ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትና አሁንም በሚዲያ ዘርፍ በግላቸው የሚንቀሳቀሱት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ በሰጡት አስተያየት አቶ ታምራት ያነሷቸው የሚዲያ ዘርፉ ችግሮች መኖራቸው እውነት ቢሆንም፣ በሚዲያ ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩ ሙያተኞች የአገሪቱ የፖለቲካ ማኅበረሰብ አንድ አካል ከመሆናቸው የሚመነጭ ችግር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

ለዚህ ችግር መፍትሔ ማበጀት ተገቢ እንደሆነ እምነታቸውን የገለጹት ወ/ሮ ሰሎሜ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ይኼንኑ ችግር መደጋገም ግን ፋይዳው እንደማይታቸው፣ ‹‹ጋዜጠኞውን ከሌላ ፕላኔት እንደመጣ ዕፁብ ነገር አድርጎ እንደማሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በሚዲያ ዘርፍ ላይ ከፈጠረው ጫና ባልተናነሰ የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎች በሕግ ሳይከለከሉ፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ የሚገደዱ ወይም የለመዱ በመሆናቸው፣ በዘርፉ ተቋማዊ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካ ልሂቁ ራሱ የተለየ ሐሳብ ለመስማት የማይፈልግበት ሁኔታ ውስጥ የሚዲያ ባለሙያው ‹ጎመን በጤና› ብሎ ራሱን ሳንሱር እንደሚደርግ፣ አንዳንዶች ደግሞ በግል ተቋም ደረጃም ጥቅማቸው እንዳይጎዳ ወይም ጥቅም ፍለጋ ራሳቸውን ሳንሱር እንደሚያደርጉ አውስተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የመጡት ሌላው ተሳታፊ በሚዲያ ተቋማትና በገንዘብ ተቋማት መካከል በአቶ ታምራት የተደረገው ንፅፅር፣ የሚዲያ ዘርፉ ውስጥ ያለውን ችግር ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ ያምናሉ፡፡

የሚዲያ ዘርፉ ከመንግሥት ጫና የሚደረግበት ቢሆንም፣ የሚዲያ ዘርፍ ሙያተኞችና ዘዋሪዎች ማንነትን በደንብ መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹የግሉ ሚዲያ ውስጥ ያሉት ጋዜጠኞች እነማን ናቸው?›› ሲሉ የጠየቁት ተሳታፊው፣ ‹‹ማደግ አለበት ተቋማዊ ሊሆን ይገባል ብለን የምንናገርለት የጋዜጠኝነት ሚዲያ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ተቋማት ሚዲያዎችን መለየት አለብን፤›› ሲሉ ዘርፉ ጎራው የተደበላለቀ መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የሚዲያ ዘርፍ ሙያን ተላብሶ ተቋማዊ ብሎም የሚዲያ ኢንዱስትሪ እንዲሆን ምን መደረግ ይገባዋል የሚለው ጉዳይ ተወያዮች በመጠኑ የዳሰሱት ጉዳይ ነበር፡፡

አቶ ታምራት ባቀረቡት ሐሳብ የሚዲያ ዘርፉን ተቋማዊ አቅም ለመገንባትና ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ዘርፉን የተመለከተ የጠራ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በእሳቸው እምነትም ብዝኃነትን ማስተናገድ የሚችል፣ ተቋማዊነትን ለመገንባት የሚረዳ፣ ዴሞክራቲክ ኮርፖሬት ሚዲያ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ይህ ፖሊሲ እሳቸው እንደሚፈልጉት የሚመጣ ከሆነ፣ የሚዲያው ሚና ምን መሆን እንዳለበት ሊወስን እንደማይገባና ይህን ኃላፊነት ለዘርፉ መተው እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ይኼንን ማድረግ ከተቻለ የፋይናንስ ምጩን ከራሱ ከገበያው ማግኘት የሚችል፣ ሙያዊ ብቃትና ብዝኃነት ያለው ኮርፖሬት የሚዲያ ዘርፍ መገንባት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ተሳታፊ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት ጋዜጠኛ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት መርሳ ሚዲያ የተባለ የጥናትና ማማከር አገልግሎት ድርጀት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ሰማእዝጌር በሰጡት አስተያየት፣ የመንግሥት ተፅዕኖ ሚዲያውን እንዳያዳክመው፣ ሚዲያውም የራሱን ስህተቶች በራሱ እያረመ የሙያ ብቃቱን እንዲያሳድግና ተቋማዊነትን እንዲገነባ የጋዜጠኝነት የሙያ ማኅበራትን፣ እንዲሁም የሙያተኞቹ የአቻ መማክርት (Media Council) መመሥረት የግድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -