Sunday, May 19, 2024

ኢሕአዴግን በአገር አቀፍ ፓርቲ የመተካት ተስፋና ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔር አገር እንደ መሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን፣ በድርጅቶች በተለይ ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት ነው፡፡››

ከላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ መርህ በ1999 ዓ.ም. የፀደቀውና አሁንም በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ)፣ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተወሰደና የግንባሩ አደረጃጀት መሠረታዊ ዘውግ ነው፡፡

ምክንያቶቹንም ሲያብራራ ኢሕአዴግ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶች በአንድነት ያዋቀሩት ግንባር ሲሆን ብቻ፣ በፅኑ የሚታገልለትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነትና አንድነትን የማስጠበቅ ዓላማ በተግባር ሊተረጉምና ሊያረጋግጥ እንደሚያስችለው ይገልጻል፡፡

‹‹በመሆኑም የሕዝቦቻቸውን መብት የማስጠበቅ ዓላማን ያነገቡና በቀላሉ የሕዝባቸውን ድጋፍ የሚያገኙ የብሔር ብሔረሰብ ድርጅቶችን ብቻ በግንባሩ ዙሪያ አሳልፎ ይንቀሳቀሳል፤›› ሲል የመተዳደሪያ ደንቡ የኢሕአዴግን የድርጅታዊ መዋቅር መርህ ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የአደረጃጀት መርህ ዘለዓለማዊ እንዳልሆነ የኢሕአዴግ የተለያዩ አመራሮችና የግንባሩ ፈጣሪ የሆኑት፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የኢሕአዴግ አስተሳሰብ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ ሲፀናና የተደላደለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ሲደርስ፣ ኢሕአዴግ ተዋህዶ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ እንደሚሆን በይፋ ከተናገሩት መሀል አቶ መለስ ዜናዊ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡

ይኼንኑ የአቶ መለስን ግልጽ አቋም በቅርቡ በማስታወስ ከገለጹ የፖለቲካ ተንታኞች መካከል የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብና በጥልቀት የሚመራመሩት ፕሮፌሰር አሌክስ ደዋል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በኦገስት 2018 “The Future of Ethiopian Developmental or Political Market Place?” በሚል ባቀረቡት የዳሰሳ ጥናት ላይ አቶ መለስ ኢሕአዴግ ተዋህዶ አንደ አገር አቀፍ ፓርቲ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ይህ የሚሆነው መሟላት የሚገባቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መደላድሎች ሲረጋገጡ መሆኑን እንደ ነገሯቸው አመልክተዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለመሸጋገር የሚያስችሉ እንዲሆኑ ከሚያምንባቸው መደላድሎች አንዱ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወደ መካከለኛ ገቢ መሸጋገር ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ኢሕአዴግን ከማዋሀድ ባለፈም የሚመራበትን ርዕዮተ ዓለም በመቀየር ወደ ሊበራሊዝም ለመሸጋገር እንደሚያስችለውም ይነገር ነበር፡፡

ነገር ግን ለዚህ ሽግግር የሚያበቁ ናቸው የሚላቸው ምቹ መደላድሎች ሳይሟሉ ከግንባርነት ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለመሸጋገር በማሰብ ሥራ የጀመረው፣ በ2007 ዓ.ም. ባካሄደው የግንባሩ ጉባዔ ይኼንኑ የሚመለከት ውሳኔ በማሳለፍና ጉዳዩን የሚያጠና ኮሚቴ በማቋቋም ነበር፡፡

ይኼው ኮሚቴ ላለፉት አራት ዓመታት ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲያካሂድ የነበረውን ጥናት ማፋጠን የጀመረው ግን ከ2010 ዓ.ም. በኋላ መሆኑ ይነገራል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው ሽኩቻና መጠላለፍ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የኢሕአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ላይም ይኸው የውህደት ጉዳይ ኮሚቴው ባቀረበው ያልተጠናቀቀ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ ላይ የቀረበውና ሪፖርተር ያገኘው የውይይት ሰነድ የግንባሩን መዋቅራዊ ለውጥና ድርጅታዊ ውህደት የተመለከተ ጥናት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ያስረዳል፡፡

ይኼንን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ በግንባሩ ጽሕፈት ቤት የጥናትና ምርምር የሥራ ክፍል ሥር ተዋቅሮ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን የሚገልጸው ይኸው ሰነድ፣ ኮሚቴው ባካሄደው ጥናትም የግንባሩን መዋቅራዊ አደረጃጀት በተመለከተ ሦስት አማራጮችን በጥናቱ ማመላከቱን ይገልጻል፡፡

ጥናቱ በመጀመርያ አማራጭ ኢሕአዴግና አጋሮቹን አንድ ላይ ለማዋሀድ ጊዜው ገና መሆኑን አመላክቷል፡፡ ይህም ማለት ኢሕአዴግና አጋሮቹን ለውህደት የሚያበቃው ቅድመ ሁኔታ አለመሟላቱን የሚያመላክት እንደሆነ ያብራራል፡፡ በሁለተኛ አማራጭነት የቀረበው ደግሞ የኢሕአዴግ መሥራች ድርጅቶችም ሆነ አጋር ድርጅቶች አሁን በሚገኙበት አቋም ሆነው አንድ የጋራ አገር አቀፍ ፓርቲ ይመሥርቱ የሚል ነው፡፡ በሦስተኛ አማራጭነት የቀረበው ደግሞ አሁን ያሉት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች (የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች) የብሔራዊ ድርጅቶቻቸውን አባላት ይዘው አንድ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይመሥርቱ የሚል ነው፡፡

በቀረቡት ሦስት አማራጮች ላይ የመከረው 11ኛው የድርጅቱ ጉባዔ የግንባሩን አደረጃጀት ፈትሾ የማስተካከል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የተግባባ ሲሆን፣ ይህ የመዋቅር ማስተካከያ የኢሕአዴግ የግንባር አደረጃጀት ‹‹አሁን ያለንበትንና ከፊታችን የሚጠበቅብንን የትግል ምዕራፍ በአግባቡ ሊያሳካ ይችላል ወይስ አይችልም?›› የሚለውን ጉዳይ አፅንኦት በመስጠት እንዲፈጸም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በመሆኑም በጥናቱ በቀረቡት አማራጮች ላይ ዝርዝር ውይይት በየደረጃው ጊዜ ወስዶ በማካሄድ ከተቻለ ከሚቀጥለው ጉባዔ በፊት እንዲጠናቀቅ፣ ካልተቻለ ደግሞ በሚቀጥለው ጉባዔ (የድርጅቱ ጉባዔ ከሁለት ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የጊዜ ልዩነቶች የሚካሄድ ነው) ቀርቦ እንዲወሰን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ይህ ውሳኔ በመስከረም ወር ከተላለፈ በኋላ ኮሚቴው ተጨማሪ የማጣራት ሥራዎችን ማከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችና ድርጅቶቹ ከሚወክሏቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ያደረጉት የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቂት ወራት ውስጥ ኢሕአዴግንና አጋር ድርጅቶችን በማዋሀድ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ እንደሚመሠረት ይፋ አድርገዋል፡፡

ብሔርን መሠረት አድርገው የተዋቀሩት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ አጋር ድርጅቶች ከስመው፣ በእነሱ የሚዋቀር አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ በወራት ውስጥ እንደሚመሠረትና ኢሕአዴግ የሚለው መጠሪያም እንደሚቀየር አስታውቀዋል፡፡

ይህንን ውህደት ለመፈጸም የሚያስችል ጥናት መደረጉን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የጥናት ሰነዱ ለሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች በቅርቡ እንደሚላክና በተናጠል ውይይት ተደርጎበት ውህደቱ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

ይህ መሆኑም ሌላውን የፖለቲካ ማኅበረሰብ በማማከል የኢሕአዴግ መሥራች በሆኑት አራት ፓርቲዎች ውሳኔ ብቻ የሚመረጥ የአገር መሪ እንዳይኖር፣ እንዲሁም ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚወክሉ የፖለቲካ ልሂቃን የሚሳተፉበትና የሚወስኑበት ፖለቲካዊ አስተዳደር እንደሚያሸጋግር አስረድተዋል፡፡ ይህ ሲሆንም ለበርካታ ዓመታት በአጋር ድርጅቶች አማካይነት ሊቀርብ የነበረ የእኩልነት (ፖለቲካዊ) ጥያቄ መልስ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡

የውህደቱ ተስፋና ሥጋቶች

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት ኢሕአዴግንና አጋር ፓርቲዎችን በማዋሀድ አንድ አገራዊ ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመመሥረት ዕቅድ፣ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን አዲስ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢሕአዴግ ላይ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመያዝ ስለተቸገሩ የመረጡት መንገድ እንደሆነ ሲገልጹ፣ የብሔረሰቦቻቸውን ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለማስከበር ቅድሚያ የሰጡ የፖለቲካ ልሂቃን ደግሞ ‹‹ለምን አሁን?›› ሲሉ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአንድ ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ በመሆናቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ኢሕአዴግን በጥቂት ወራት ውስጥ በማዋሀድ ጉዳይ በተጠቀሰው የጊዜ ዓውድ ውስጥ ወደ ተግባር ይቀየራል የሚለውን ከማመን ይልቅ፣ በምክንያት ሳይሆን በኃይል እየተመራ ያስቸገራቸውን የፖለቲካ ሁኔታ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለማስታገስ የወረወሩት አጀንዳ እንደሆነ ነው የምገምተው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ደግሞ በዚህ ዓይነት ጉዳዮች የተካኑ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ በመዋሀድ ወደ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲነት መሸጋገር ይቻላል ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ አጫረባቸው እንጂ፣ ታስቦበትና በምዕራፎች ተከፋፍሎ ቢፈጸም ኢትዮጵያ ላለችበት የፖለቲካ ቀውስ ፍቱን መፍትሔ እንደሚያመጣ የፖለቲካ ተንታኙ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

ኢሕአዴግ ከጥንስሱ ጀምሮ ወደፊት ወደ ተዋሀደ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲነት እንደሚለወጥ ሲያመላክት እንደነበር፣ ነገር ግን ወደዚህ ውህደት ለመምጣት የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና አባላት በግንባሩ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም፣ በመርህና በአስተሳሰብ መብሰልን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጡና ይኼንን ቅድመ ሁኔታ ማሟላት ባለመቻሉ ውህደቱን ከዓመት ዓመት ሲገፋው እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡

‹‹አሁን ምን ተገኝቶ ነው ኢሕአዴግ ወደ ውህደት የተጣደፈው?›› ሲሉ የሚጠይቁት እኚሁ ተንታኝ፣ ‹‹ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ የማንኛውም ፓርቲ መሠረታዊያን የሚባሉት የፖለቲካ ፕሮግራም (ርዕዮተ ዓለም)፣ የአደረጃጀት መዋቅርና ዲሲፕሊን በኢሕአዴግ ውስጥ በተናጉበት ወቅትና ሕወሓት አኩርፎ ቁጭ ባለበት፣ በአዴፓና በኦዴፓ መካከል ይፋ ያልወጣ ፉክክር ባለበት፣ ደኢሕዴን በራሱ ችግሮች በተጠመደበት ወቅት በምን መሠረት ላይ ነው ኢሕአዴግ ያውም አጋሮችን አካቶ የሚዋሀደው?›› ሲሉ ተግዳሮቶቹን በጥያቄ መልክ ያቀርባሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅታዊ የፖለቲካ ትርክቶችን አቅጣጫ ለመዘወር ፈልገው የተናገሩት እንደሆነ የሚያምኑትም በዚህ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ወደ ውህደት ለመምጣት በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ በአጋሮች መካከል በርዕዮተ ዓለም ደረጃ በቅድሚያ የአመለካከት አንድነት ሊኖር እንደሚገባ፣ በኢኮኖሚ አመለካከት፣ በፌዴራሊዝምና በመሰል ጉዳዮች ላይ መግባባት ሊኖር እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

አለበለዚያ ‹‹ወደ ውህደት መምጣት የማትፈልጉ መውጣት ትችላላችሁ›› ዓይነት አካሄድ፣ ወደ ክፍፍልና የተዳከመ መንግሥትን ሊያመራ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ግን የኢሕአዴግ ወደ ውህደት መምጣት በበቂ መሠረት ላይ እስካልተፈጸመ ድረስ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ወደ ሌላ በጎ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ያስረዳሉ፡፡

ታስቦበትና ችግር በማይፈጥር ሁኔታ ውስጥ ሰከን ብሎ ከተፈጸመ፣ አገሪቱን ሰቅዞ ከያዛት የብሔርና የማንነት ፖለቲካ ወደ ርዕዮተ ዓለም ወይም የፍላጎት ፖለቲካ የሚያሸጋግርና የኢትዮጵያ ፖለቲካን መፈወሻ መድኃኒት ስለመሆኑ ጥርጥር እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሲሆን ብሔራዊ ማንነትና ከእዚህ ጋር የሚያያዙ ጥያቄዎች ይደፈጠጣሉ ማለት እንዳልሆነ የሚያስረዱት እኚሁ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማጣቀስ በሚዋሀደው ኢሕአዴግ ውስጥ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን የተከተለ የመብቶች ጥያቄን ለማስከበር ንዑስ አደረጃጀቶችን መፍጠር እንደሚቻል አሳስበዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳዳት ነሻ ውህደቱ የሚፈጸመው፣ የኢሕአዴግ ጉባዔ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት ጥናት መካሄዱንና ጥናት በለያቸው ጭብጦች ላይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች በቅርቡ በተናጠል ሆነው ከማኅበራዊ መሠረቶቻቸው ጋር ውይይት እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የፖለቲካ ትርክት አቅጣጫ ማስቀየሪያ ሳይሆን፣ ታቅዶና በኢሕአዴግ ጉባዔ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች ውስጥ በጋራም ይሁን በተናጠል ሊገለጹ የሚችሉ ችግሮች ቢኖሩም እነዚህ ችግሮች ውህደቱን እንደማያደናቅፉ፣ እንዲያውም የውህደቱ መምጣት ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ ረገድ የራሱን ዕገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ውህደቱ የሚፈጸመው የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባህርያት ሳይለቅ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሳዳት፣ ‹‹ውህደቱ የብሔር፣ የቋንቋ ማንነቶችንና ፌዴራሊዝሙን ይንዳል የሚሉ ሥጋቶች ያሏቸው ወገኖች ቢኖሩም፣ እነዚህ የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባህርያት በውህደት በሚወልደው አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ውስጥም የሚቀጥሉ መሠረታዊያን ናቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ውይይቱ በቅርቡ እንደሚጀመርና ዳብሮ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሒደቱን ተከትሎ ውሳኔ እንደሚያገኝም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -