Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ የሚሰጥበት መመርያ ሥጋት አጭሯል

  በአዲስ አበባ የነዋሪነት መታወቂያ የሚሰጥበት መመርያ ሥጋት አጭሯል

  ቀን:

  በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አጥ ወጣቶች የነዋሪነት መታወቂያ እንዲያገኙ በከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ የተላለፈው መመርያ፣ በነዋሪዎች ላይ ሥጋት አጭሯል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች የነዋሪነት መታወቂያ ስለሌላቸው መንግሥት በሚያመቻቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን በመጥቀስ፣ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር የመታወቂያ ችግር እንዲፈታላቸውና የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በክፍላተ ከተሞች መጠየቁን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡ በዚህም ጥያቄ መሠረት የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ በመመርያ ቁጥር 3/2010 መሠረት ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች አሠራሩን በመጠበቅ፣ በሚገኙበት ወረዳ የመታወቂያ አገልግሎት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጣቸው መመርያ አስተላልፏል፡፡

  ሆኖም ይህን መመርያ ተከትሎ በአዲስ አበባ ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በጅምላ የነዋሪነት መታወቂያ መሰጠቱ በነዋሪዎች ላይ ሥጋቱን አጭሯል፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም ማንኛውም ሰው የከተማዋን የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት ማሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች ለአብነት በፊት ከሚኖርበት አካባቢ ማምጣት ያለበት የመሸኛ ደብዳቤ፣ ሥራ አጥ ወጣቶቹ ተደራጅተው የነዋሪነት መታወቂያ ሲወስዱ እንደ መሥፈርት አለመቀመጡ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

  ጉዳዩን በተመለከተ የኤጀንሲውን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አብዱራሂምን ሪፖርተር ጠይቋቸው፣ ለሥራ አጥ ወጣቶቹ የነዋሪነት መታወቂያ የሚሰጥበት አግባብ በመመርያ ቁጥር 3/2010 መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ ያሉ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋም ወጣቶቹን ለማደራጀት እንደ መሥፈርት ካስቀመጠው መካከል የነዋሪነት መታወቂያ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች በጠየቁት መሠረት መመርያው መተላለፉን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሥራ አጥ ወጣቶቹ በሚገኙበት ወረዳ ያሉ ኃላፊዎች ወጣቶቹ ነዋሪ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ፣ የነዋሪነት መታወቂያ እንደሚሰጣቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ሌላ ማንኛውም ሰው ግን በከተማዋ የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት በፊት ከሚኖርበት አካባቢ የመሸኛ ደብዳቤ ማምጣት የመሥፈርቱ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  በአዲስ አበባ በተለያዩ ወረዳዎች መመርያውን ተከትሎ በጅምላ የከተማዋ ነዋሪዎች ላልሆኑ ግለሰቦች መታወቂያ እየተሰጠ መሆኑን፣ በተለይም በቅርቡ አገራዊ ምርጫ ስለሚደረግ ነዋሪዎች መታወቂያ የሚሰጥበትን መመርያ ከምርጫው ጋርም እያያያዙት ነው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በአገሪቱ ከአንድ በላይ የመኖርያ ቤት ቢኖረው የነዋሪነት መታወቂያ ሊያገኝ የሚገባው በቋሚነት በሚኖርበት ቦታ ሲሆን፣ ይህ ማለት ግለሰቡ ምርጫ የሚመርጥበት፣ መንግሥት ቢፈልገው የሚገኝበትና ሌሎች አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን በሚያገኝበት ቦታ የነዋሪነት መታወቂያ እንደሚያወጣ ይታወቃል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ነዋሪ የሆነ ሰው መጥቶ በዚህ መመርያ መሠረት የነዋሪነት መታወቂያ ቢያገኝ እንዴት ትቆጣጠሩታላችሁ በማለት ለአቶ መሐመድ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ በመመርያው መሠረት የነዋሪነት መታወቂያ በሚሰጣቸው ሰዎች የሚመጣውን አደጋ ኃላፊነት የሚሸከሙት በየአካባቢው ያሉ የወረዳ የአስተዳደር ኃላፊዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ መመርያው የወጣው የመልካም አስተዳደር ችግር የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ መሆኑን አስታውቀው፣ በነዋሪነት መታወቂያ አሰጣጥ ላይ ለሚነሱ ማናቸውም ችግሮች ተጠያቂዎቹ የወረዳ አስተዳዳሪዎቹ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

   በተለይ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች ቀጣዩን ምርጫ ለማሸነፍ የሚፈልግ አካል በከተማዋ የጅምላ የመታወቂያ ዕደላ እያደረገ ነው የሚል ሥጋት እንደሚያነሱ አቶ መሐመድ ተጠይቀው፣ ‹‹ሥጋቱ ልክ ነው፣ ሥጋቱም የሁላችንም ነው፡፡ ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ ይሠራ የሚለው ጉዳይ በሚገባ መታየት አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ተረድቶ የማይሠራ ኃላፊ ካለ በኋላ ተጠያቂነቱ የሚመጣው እዚያው አካል ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ይህ ሥጋት መኖሩን መንግሥት ካወቀና የመታወቂያ አሰጣጡ የሥራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሆነ፣ ያለ መታወቂያ ወጣቶቹ ለምን ተደራጅተው መንግሥት ባመቻቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አይሆኑም ተብለው ተጠይቀው፣ ‹‹የነዋሪነት መታወቂያው እንዲሰጥ መመርያ ያስተላለፍነው ግለሰቦች ባቀረቡልን ጥያቄ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ሲጠይቁን ያስቀመጥነው መሥፈርት አለ፡፡ አገልግሎቱን እንድንሰጥ የጠየቀን ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ለወጣቶቹ በራሱ የሥራ ዕድሉን መስጠት ይችላል፡፡ የሥራ ዕድሉን ለመስጠት ግን የነዋሪነት መታወቂያ ስጡልኝ በማለቱ ነው አገልግሎቱን እየሰጠን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ሒደት ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂነቱን የሚወስደው ተቋሙ ይሆናል ብለዋል፡፡

  በቅርቡ ከዚህ መመርያ ጋር ተያይዞ የጅምላ መታወቂያ ዕደላ መኖሩን ለሚዲያ ይፋ ያደረጉ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ሠራተኛ ከሥራ ታግደው ከቀናት በኋላ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 1 ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ደሳለኝ ተጠይቀው፣ ሠራተኛዋ ታግደው የነበሩት የተሳሳተ መረጃ ለሚዲያ በማሠራጨታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስ በወረዳቸው ለ916 ሥራ አጥ ወጣቶች የነዋሪነት መታወቂያ መስጠታቸውን ገልጸው፣ ይህንንም ያደረጉት ከክፍለ ከተማው በወረደ መመርያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቅርቡ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ለሥራ አጥ ወጣቶቹ የሚሰጠው የነዋሪነት መታወቂያ ለጊዜው ቢቆምም፣ በወረዳው ላሉ ሥራ አጥ ወጣቶች መታወቂያዎች በጅምላ ተሠርተው ወደፊት እየተጣራ መሰጠቱ እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 እስካሁን 916 መታወቂያዎች በዚህ አሠራር ይሰጡ እንጂ፣ በሌላ ወረዳ እስከ አምስት ሺሕ መታወቂያ መሰጠቱን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ እሳቸውም ግን በዚህ መመርያ መሠረት የሚሰጠው የጅምላ መታወቂያ ክፍተት እንዳለው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...