Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእነ አቶ በረከት ስምዖን ክስ ተመሥርቶ ወደ ክርክር ለመግባት ሲጠይቁ ዓቃቤ ሕግ...

እነ አቶ በረከት ስምዖን ክስ ተመሥርቶ ወደ ክርክር ለመግባት ሲጠይቁ ዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠየቀ

ቀን:

ኮሚሽኑ በውጭ ሕክምና ላይ የሚገኙ ሁለት ወሳኝ ምስክሮች አሉኝ ብሏል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ ቶሎ ክስ ተመሥርቶ ወደ ክርክር እንዲገቡ የክልሉን ፍርድ ቤት ጠየቁ፡፡ የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን ቶሎ አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ በማስተላለፍ ክስ እንዲመሠረትና ወደ ክርክሩ መግባት አለበት፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ጥያቄውን ያነሱት የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በርካታ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰቡን ለፍርድ ቤቱ ካስረዳ በኋላ፣ ወሳኝ የሆኑ ሁለት ምስክሮቹ በውጭ አገር ሕክምና ላይ ስለሆኑና የዳሸን ቢራ አክሲዮን ሽያጭን በሚመለከት የተጀመረ የኦዲት ሥራ እንዳላለቀለት በመግለጽ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት በመጠየቁ ነው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የዕረፍት ቀናቱን ጭምር እየሠራ ቢሆንም፣ ከጉዳዩ ውስብስብነት የተነሳ ምርመራው በፈለጉት ፍጥነትና ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉንም አክሏል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁን የተቃወሙት አቶ በረከት፣ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ ተፈቅዶለት በነበረው 14 ቀናት ውስጥ ምርመራውን አጠናቆ መቅረብ እንደነበረበት ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ መርማሪው አዳዲስ ሐሳብ እያቀረበ እነሱ በእስር መቆየት እንደሌለባቸውም አክለዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የዳሸን ቢራ አክሲዮን ሽያጭን በሚመለከት እየተከናወነ ያለው ኦዲት እንዳልተጠናቀቀ የተናገረውን በሚመለከት፣ ፋብሪካው በየዓመቱ ኦዲት ስለሚያሠራ ሰነዱን በመውሰድ ማረጋገጥ የሚችል መሆኑንም አቶ በረከት ለፍርድ ቤቱ ጠቁመዋል፡፡ ሽያጩን በሚመለከትም ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በውጭ አገር ሕክምና ላይ የሚገኙትን የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ስም ለችሎቱ ግልጽ እንዲደረግ የጠየቁት አቶ በረከት፣ የተለያዩ ምክንያቶችና ሐሳቦችን በማቅረብ ጊዜ መውሰድ አስፈላጊና ተገቢም አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምስክሮች ከውጭ መጡ ወይም አልመጡ የእነሱ ችግር እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ታደሰ በበኩላቸው፣ ኦዲት ማስደረግ፣ ምስክሮች ማሰባሰብ፣ የተለያዩ ሰነዶችን መሰብሰብና የባንክ ጉዳዮችን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንጂ፣ በየቀጠሮ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ባቀረበው መቃወሚያ እንደተናገረው ተጠርጣሪዎቹ ኦዲት የተደረገ ሰነድ እንዳለ ቢናገሩም፣ አሁን እየተደረገ ካለው ኦዲት ጋር አይገናኝም፡፡ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የያዘው ሰነድና የኮሚሽኑ መርማሪዎች የሚፈልጉት ሰነድ የተለያየ ነው ብሏል፡፡ በውጭ አገር የሚገኙ ምስክሮችን በሚመለከትም በፍጥነት እንዲመጡለት እየሠራ መሆኑን ገልጾ፣ ስማቸውን በችሎት ለመግለጽ እንደማይችልና ሊገደድም እንደማይገባ ተናግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ  ካመነበትና መገለጽ አለበት ካለ ግን በቀጣይ ቀጠሮ መናገር እንደሚቻል አክሏል፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ማስረጃዎችን እያገኘ በመሆኑ፣ ምርመራውን አጠናቆ ለመቅረብ የጠየቀው 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን በርካታ ሰነዶችና በዕለቱ የተደረገውን ክርክር መርምሮ፣ ‹‹ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ ይገባል? ወይስ አይገባም?›› በሚለው ላይ ለመወሰን ለሰኞ የካቲት 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...