Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን ዋስትና በማስያዝ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት እንዲቻል የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ ዜጎች ከገንዘብ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል ረረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ታወቀ።

የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን በዋስትናነት በማስያዝ ባንኮች ብድር እንዲያቀርቡ የሚያስችል አሠራር ለመጀመር መታቀዱን ገልጸው ነበር።

ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ለማረጋገጥ ተችሏል። የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያስረዳው በአገሪቱ ዘመናዊ የብድር ሥርዓት ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በብድር መያዣነት ውለው ተጨማሪ ጥቅም ማመንጨት የሚችሉበት አሠራር ባለመኖሩ፣ የአገሪቱን ዕምቅ ሀብት በሙሉ ወደ ኢኮኖሚያዊ ልማት መለወጥ አልተቻለም።

ይህ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩም ከገንዘብ ተቋማት ብድር ለማግኘት በዋስትናነት የሚቀርቡት እንደ የመኖሪያና የአገልግሎት ሕንፃዎች፣ የንግድ ተቋማት፣ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች የመሳሰሉት ብቻ ሆነው መገደባቸውን ይገልጻል፡፡ የአገሪቱን አጠቃላይ ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ተንቀሳቃሽ ንብረቶች በዋስትና መቅረብ የሚችሉበት የሕግ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ እንዳደረገው ረቂቁ ያስረዳል።

ረቂቁ ፀድቆ ወደ ትግበራ ሲገባም የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ግዑዝ ወይም ግዑዝ ያልሆኑ ንብረቶችና ሀብቶች፣ ሰብሎች፣ የመገልገያ መሣሪያዎች፣ የባንክ ተከፋይ ሒሳቦች፣ የተረጋገጡ የገቢ ገንዘብ ማስረጃዎች በዋስትና በማቅረብ ከገንዘብ ተቋማት ብድር ማግኘት እንደሚያስችል ያመለክታል።

ከዚህ በተጨማሪ ዋጋ የሚያወጡ የእንስሳት ሀብቶችና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ሀብቶች ለብድር ዋስትና በማስያዝ፣ ዜጎች ወይም ባለሀብቶች ከልማዳዊው ወይም ነባሩ የገንዘብ አቅርቦት አማራጭ ሌላ አዲስ የኢንቨስትመንት ካፒታል ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጠር ረቂቁ ይገልጻል።

ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀትም ዋስትናው የተጠበቀ ዘመናዊ የብድር ሥርዓትን በማስፋፋት ግለሰቦችና ተቋማት ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በዋስትና በማስያዝ፣ አዲስ የብድር ምንጭ እንዲያገኙና በዚህ በሚፈጠረው አዲስ ካፒታልም ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት፣ በሒደቱም በከተሞች ላይ ያተኮረውን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት ማስፋፋትና የበለጠ ማሳደግ ስለሚያስችል እንደሆነ በማብራሪያ ገጾቹ ያስገነዝባል፡፡

ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ተጨማሪ ካፒታል እንዲፈጥሩ ከልማዳዊ የዋስትና አሰጣጥ ወደ ሕጋዊና ተዓማኒነቱ የተረጋገጠ የዋስትና ሥርዓት እንዲገቡ፣ እንዲሁም ብድር የተወሰደባቸው ንብረቶች በሌላ ወገን ወይም በሌላ አካባቢ ዕዳቸውን ከፍለው ሳይጨርሱ ሌላ ብድር እንዳይወሰድባቸው ለማስቻል፣ ሁሉን አቀፍ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ማዕከል እንደሚከናወንም ይገልጻል።

ለዚህም ሲባል የዋስትና መዝገብ ጽሕፈት ቤት እንደሚቋቋም፣ የሚቋቋመው የምዝገባ ጽሕፈት ቤት ሥልጣንና ተግባር፣ ዋስትና ሰጪ ዋስትናን ለማስመዝገብ ማሟላት የሚጠበቅበት ተግባራትና መሥፈርቶች፣ የዋስትና መዝገብ ጽሕፈት ቤቱ የተመዘገቡ ዋስትናቸውን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግና በሕግ አግባብ መረጃ መስጠት እንደሚጠበቅበት ያመለክታል። ረቂቅ አዋጁ በዚህ ዓመት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች