Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጀማሪ ኢንዱስትሪዎችን እንደሚያግዝ ተስፋ የተጣለበት የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ አዋጅ ሊሻሻል ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጀማሪ ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀርፍ ተስፋ የተጣለበት የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ አዋጅ (ሊዝ ፋይናንሲንግ) በቆየባቸው የትግበራ ዓመታት፣ በችግር ላይ ችግር በመፍጠሩ እንዲሻሻል ሊደረግ ነው።

ይህ አዋጅ የጀማሪ ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመፍታት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፉ፣ መንግሥት ላቀደው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር አገር በቀል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አቅም እንዲያገኝ ታስቦ የፀደቀና ወደ ትግበራ የገባ ነው።

በዚህም መሠረት ጀማሪ ኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጓቸውን የካፒታል ዕቃዎች ማለትም የማምረቻ ማሽነሪዎች ለማሟላት የፋይናንስ እጥረት ወይም የአቅርቦት ችግር የሚገጥማቸው በመሆኑ፣ በልማት ባንክና በአነስተኛና ጥቃቅን የብድር ተቋማት በኩል የሚያስፈልጓቸው ማሽነሪዎች እንዲቀርቡና ጀማሪ ኢንዱስትሪዎቹ በረዥም ጊዜ የኪራይ ውል የንብረቶቹ ባለቤቶች የሚሆኑበትን አሠራር ያበጀ ነበር።

 ጀማሪ ኢንዱስትሪዎች በዚህ ሥርዓት ለመጠቀም ለሚቀርብላቸው የማምረቻ መሣሪያ አጠቃላይ ዋጋ 20 በመቶውን ማስያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ቀሪውን በሚያደርጉት የኪራይ ውል ስምምነት መሠረት በረዥም ጊዜ ክፍያ በማጠናቀቅ ማምረቻ መሣሪያውን ንብረታቸው ማድረግ ነው። የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ከስድስት ሰዎች በላይ ሆኖ መደራጀትና የሚሰማሩበትን ዘርፍ አዋጭነት በጥናት ለይቶ መቋቋምን ይጠይቃል።

በዚህ መሠረት በተለያዩ ክልሎች በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው የማምረቻ መሣሪያዎችን በኪራይ የወሰዱ ቢሆኑም፣ በርካቶቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ ማሳካት አቅቷቸው ለተረከቡት የማምረቻ መሣሪያ ዕዳ በመክፈል ላይ ናቸው።

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክለው በዚህ ዕድል ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ አብዛኞቹ በሥራቸው ውጤታማ መሆን ባለመቻላቸው፣ በአሁኑ ወቅት የተቋቋሙበትን የንግድ ካፒታል ለዕዳ ክፍያ ለማዋል ተገደዋል። ሚኒስቴሩ ባደረገው ዳሰሳም እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ካፒታላቸውን ዕዳ የከፈሉ ድርጅቶች ተበራክተዋል።

የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት የማምረቻ መሣሪዎቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ኢንዱስትሪዎቹ በጠየቁት ስፔስፊኬሽን መሠረት ያልቀረቡ፣ እንዲሁም ያገለገሉ ማሽነሪዎች የተላለፉላቸው በመሆናቸውና በቂ አገልግሎት ሳይሰጡ ለብልሽት በመዳረጋቸው ነው።

ጉዳዩ የሙስናና የአስተዳደር ችግር ይዘት ቢኖረውም ለዚህ ችግር በር የከፈተው አዋጁ በመሆኑ እንዲሻሻል ማስፈለጉን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪም በአዋጁ መሠረት የሚቀርቡ የማምረቻ መሣሪዎች የዋጋ መጠን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እንዳይሆን የተገደበ በመሆኑ፣ ከጀማሪ ኢንዱስትሪዎቹ ፍላጎትና  ከወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ጋር የተገናዘበ አለመሆኑ ሌላው የትግበራው ፈተና መሆኑን የተደረገው ጥናት ያመለክታል።

 በመሆኑም አነስተኛ የብድር ተቋማት ለሚያቀርቧቸው የማምረቻ መሣሪያዎች የተቀመጠው አንድ ሚሊዮን ብር ጣሪያ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል በተመሳሳይ ልማት ባንክ ከ500 ሺሕ ብር በላይ በሆነ ካፒታል ለተቋቋሙ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚያቀርበው የማምረቻ ማሽነሪ ላይ ለውጥ እንዲደረግና ተቋማቱ የተመሠረቱበት ካፒታል መሥፈርት ዝቅ እንዲል በማሻሻያነት ተካቷል። በተጨማሪም የማምረቻ መሣሪያዎቹን የሚያቀርቡ ተቋማትና የመንግሥት የኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋቅሮች፣ በዚህ ዕድል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች የማምረቻ መሣሪያዎቹን ተክለው ሥራ መጀመራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ እንዲጣል በማሻሻያ ሐሳብነት ቀርቧል።

በእነዚህና በሌሎች የማሻሻያ ይዘቶች ላይ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የመጨረሻ ውይይት ካደረጉ በኋላ እንደሚፀድቅ ለማወቅ ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች