Saturday, May 18, 2024

የፍትሕ ሥርዓቱን ቁመና ገልጦ ያሳየው ፍትሕን ፍለጋ ጉዞ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሕገ መንግሥቱ ያጎናፀፋቸውን ፍትሕ የማግኘት መብት ያጡ ወይም የተነፈጉ የተወሰኑ ግለሰቦች ላለፉት አሥር ዓመታትና አሁንም ባለመታከት እያደረጉት የሚገኘው የፍትሕ ፍለጋ ጉዞ የት ደረሰ? በጉዟቸው መሀል ያገኙዋቸው ምላሾች ተቃርኖ ስለሕግ ተርጓሚው የፍትሕ አካል ቁመና ምን ይናገራል? የሚለው የዚህ ዘገባ ትኩረት ነው። አንቀጽ 37 እንደ መነሻ

የአሪቱ የበላይ ሕግ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 37 ሥር ማንኛውም ሰው ፍትሕ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል። ሕገ መንግሥቱ ለአገሪቱ ዜጎች የሚሰጠውን ፍትሕ የማግኘት መብት በአንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ አንድ ድንጋጌው ላይ እንደሚከተለው አሥፍሮታል፡፡

 ‹‹ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው፤›› በማለት ይደነግጋል።

ፍትሕ ከማግኘት መብት ተፃራሪ የቆመው ሌላው ‹‹አንቀጽ 37››

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅን መነሻ በማድረግ፣ የተቋሙን ሠራተኞች በተለየ ሁኔታ ለማስተዳደር የሚያስችል ደንብ እንዲያወጣ ውክልና የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2000 ዓ.ም. የባለሥልጣኑ ሠራተኞች የሚተዳደሩበትን ደንብ ቁጥር 155/2000 በማፅደቅ፣ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታወጅ አድርጓል። ይህ ደንብ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበት የሚችልበትን በሕግ የማይገሰስ ሥልጣን፣ በአንቀጽ 37 ሥር ባሉ ድንጋጌዎች ያጎናፅፈዋል፡፡ በዚህ ደንብ አንቀጽ 37 ንዑስ አንቀጽ አንድና ሁለት ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው።

 ‹‹በዚህ ደንብ በሌላ ሁኔታ የተደነገገው ቢኖርም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረንና እምነት ያጣበትን ሠራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈጻጸም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት ይችላል፤›› በማለት ንዑስ አንቀጽ አንድ ሲደነግግ፣ በንዑስ አንቀጽ ሁለት ሥር ደግሞ፣ ‹‹በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ መሠረት ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ መመለስ አይችልም፤›› በማለት ደንግጓል።

እነዚህ የሕገ መንግሥቱና የደንቡ ድንጋጌዎች በአንቀጽ ቁጥራቸው (37) ይመሳሰሉ እንጂ፣ በተግባር ግን ፈጽሞ ተፃራሪ መሆናቸው በግልጽ ይታያል፡፡ የመጀመርያው ፍትሕ የማግኘት መብትን ሲያጎናፅፍ፣ ሁለተኛው ግን ይነፍጋል፡፡ ደንብ ቁጥር 155/2000 ፀድቆ በሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በደንቡ አንቀጽ 37 ድንጋጌ በርካታ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች ሰለባ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል የተወሰኑ የቆረጡ ሠራተኞች በተናጠልና በጋራ ሆነው ከ2001 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዘንድሮ ድረስ ጥያቄያቸውን ሳይተው ፍትሕ ፍለጋ ላይ ይገኛሉ።

ደንብ ቁጥር 155/2000 ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለ በዓመቱ ባልተረዱት ምክንያት ከሥራቸው የተሰናበቱት የባለሥልጣኑ ባልደረቦች እነ አሸናፊ አማረና ሌሎች፣ በየካቲት ወር 2001 ዓ.ም. በወቅቱ በነበረው የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ክስ መሥርተው ነበር።

በወቅቱ የመሠረቱት ክስ እንደሚያስረዳው በማያውቁት ምክንያት በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ውሳኔ ከሥራ መሰናበታቸውን ሲሆን፣ እንዲሁም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ያለ ምክንያት ከሥራ መባረራቸውን ሽሮ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲወስን የሚጠይቅ ነበር።

ለቀረበው ክስ መልስ የሰጠው ባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተሩ በደንብ ቁጥር 155 አንቀጽ 37 ድንጋጌዎች መሠረት ከሥራ ማሰናበት እንደሚችልና የዳኝነት አካላትም ይኼንን ጉዳይ የመመልከት ሥልጣን እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ባቀረበው መከራከሪያ መሠረት የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ የተነሳውን ክርክር በተመለከተ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጠይቆ ነበር።

የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መርምሮ በየካቲት ወር 2002 ዓ.ም. ውሳኔውን ያሳለፈው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በሕግ አግባብ መወሰናቸውን በመግለጽ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ እንደማያስነሳ በመግለጽ ወስኗል።

በዚህም ምክንያት የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ በሠራተኞቹ የቀረበውን የክስ መዝገብ ዘግቷል።

እነ አቶ አሸናፊ ካቀረቡት ክስ በኋላም ቢሆን የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ከባለሥልጣኑ የተባረሩ ሌሎች ሠራተኞች በተደጋጋሚ ላቀረቧቸው የፍትሕ ጥያቄዎች ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ ሲመልስ ቆይቷል።

 በአስተዳደር ፍርድ ቤት እንዲሁም ይኸው ፍርድ ቤት ለሕገ መንግሥት ትርጉም ጉባዔ ባቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መሠረት የፍትሕ ጥያቄው የሕገ መንግሥት ትርጉም የሚያስጠይቅ አይደለም ቢባሉም፣ ሠራተኞቹ ግን ያሉትን አማራጮች በሙሉ ለመጠቀም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ወሳኔ በይግባኝ እንዲታይላቸው ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅንተው ነበር።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ትክክል እንደሆነ በማመን ውሳኔው እንዲፀና ይወስናል። በዚህም ተስፋ ያልቆረጡት ሠራተኞቹ የሕግ ስህተት ተፈጽሟል በማለት የአገሪቱ የመጨረሻ የዳኝነት አካል ወደ ሆነው ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር።

ሰበር ሰሚ ችሎቱም የወሰነው የሕግ ስህተት የለውም በማለት ነበር።

ፍትሕ የማግኘት አቤቱታው የተዳኘበት አመክንዮ

የፍትሕ ጥያቄው በመጀመርያ የቀረበለት የሲቪል ሰርቪስ ኤጀንሲ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ጥያቄውን በተገቢው መንገድ ተመልክቶታል። በተገቢው ተመልክቶታል ለማለት የሚያስችለውም በማያውቁት ምክንያት ከሥራ መባረራቸውን በመቃወም ሠራተኞቹ ላነሱት የፍትሕ ጥያቄ፣ ተጠሪ የሆነው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አቅርቦት የነበረው መከራከሪያ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ይኼንን ክስ ለማየትና ለመዳኘት ሥልጣን እንደሌለው የሚገልጽ በመሆኑ፣ የሠራተኞቹ ፍትሕ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብትን መዳኘት እንደሚችልና እንደማይችል የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለሚመለከተው የሕገ መንግሥት ትርጉም አጣሪ ጉባዔ ትርጉም እንዲሰጥበት በመጠየቁና ይህም ጉዳይ በከሳሾችና በተጠሪው ባለሥልጣን መካከል ወሳኝ የክርክር ጭብጥ በመሆኑ ነው።

 የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ለቀረበለት ጥያቄ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም የሚል ምላሽ መስጠቱና በተመሳሳይ መንገድ ተከሳሾቹ በመቀጠል ላነሱት የሕግ ስህተት አቤቱታ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ተመሳሳይ ናቸው።

ሁለቱም ለሰጡት ውሳኔ በምክንያትነት የጠቀሱት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 መሠረት ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ፍርድ ቤት ወይም ሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት ያለው ቢሆንም፣ ይኼው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 79 ድንጋጌው ደግሞ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ (አቤቱታ) ተቀብለው ውሳኔ መስጠት የሚችሉት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ በሚሆንበት ጊዜ እንደሆነ የሚደነግግ መሆኑን ነው፡፡

 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ደንብ ቁጥር 155/2000 በአንቀጽ 37 ሥር የገቢዎችና የጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በሙስና የጠረጠረውንና እምነት ያጣበትን ሠራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን አፈጻጸም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት እንደሚችል፣ በመቀጠልም በዚህ መሠረት ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ መመለስ እንደማይችል በመደንገጉና ይኼ ድንጋጌም በሕግ አግባብ የወጣ በመሆኑ፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች አቤቱታውን ማየት እንደማይችሉ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሲወስን፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም አጣሪ ጉባዔው ደግሞ የሕገ መንግሥት ጥሰት ስለሌለው ትርጉም እንደማያስፈልገው ወስኗል።

 ለሁለተኛ የሕግ ዲግሪያቸው መመረቂያ የማሟያ የምርምር ጥናታቸውን “Legislative Constitutionality of the Federal Parliament on Silent Matters Under the Fdreconstitution: Based on Empirical Appraisal of Laws” በሚል ርዕስ በ2004 ዓ.ም. የሠሩት አቶ እንዳልካቸው ገረመው፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ውሳኔ ከሥራቸው በመባረራቸው ምክንያት አቤቱታ ያቀረቡት ሠራተኞች ጉዳይ ላይ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሰጠውን ውሳኔ እንደ አንድ ማሳያ ተመልክተውት ነበር።

አቶ እንዳልካቸው በዚህ ጥናታቸው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው የሰጠው ውሳኔ ከፍተኛ የሕግ ስህተት እንዳለበት ይሞግታሉ። ጉባዔው የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ አያስነሳም በማለት የሰጠው ውሳኔ ስህተት፣ ሕግ አውጪው ፓርላማ የሚያወጣው ሕግ በሙሉ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብሎ እምነት ከመያዝ እንደሚጀምር ያስረዳሉ።

ሲቀጥልም ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ስለሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የበላይነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝ ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ እንደወሰነ፣ ይህም ትልቅ የሕግ ስህተት መሆኑን በጥናታቸው አመልክተዋል።

 ‹‹ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፤›› በማለት በአንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ መደንገጉን ያስረዳሉ።

በመሆኑም አጣሪ ጉባዔው በተጠቀሰው የሠራተኞቹ አቤቱታ ምክንያት ለቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የሰጠው ውሳኔ ሕግ አውጪው ወይም በእሱ ውክልና የወጣ ሕግ ነው በሚል ሽፋን ሕገ መንግሥቱ ሲጣስ እንዳለየ እንደ ማለፍ መሆኑን፣ በዚህም ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን አጣሪ ጉባዔው አለመወጣቱን በመግለጽ በጥናታቸው ሞግተዋል።

በማከልም በሕግ አውጪው የወጣ ሕግ ማጣራት አይደረግበትም ወደሚል ጭብጥ በማድላት የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑና ማስተካከያ ካልተደረገበት ያልተገደበ የመንግሥት ሥልጣን (Unlimited Government ) እንደ መፍቀድና እንደ መለማመድ መሆኑን፣ ይህም በሕገ መንግሥት ጥበቃ ያገኘ የዜጎች መብት በሕግ አውጪው እንዲገፈፍ እንደሚያደርግ ይከራከራሉ።

በጥናታቸው ያነሱት ሌላው ነጥብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተባለውን ደንብ እንዲያወጣ በፓርላማው የተሰጠው ውክልና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 587/2000 መሠረት መሆኑን፣ ይህ አዋጅ ደግሞ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የተጠቀሰውን አከራካሪ ድንጋጌ የያዘ ደንብ እንዲያወጣ እንደማይፈቅድለት ያስረዳሉ።  

‹‹[የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን] ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ይመራል” የሚለው በአዋጅ 587 አንቀጽ 19 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ በሰፈረው ድንጋጌ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንቡን ለማውጣት ውክልና ቢሰጠውም ያወጣው ደንብ ግን ውክልናውን በሰጠው አዋጅ ላይ ባልተቀመጠና አዋጁንም በመቃረን ሠራተኞች በጥርጣሬ እንዲሰናበቱ፣ በየትኛውም የፍርድ አካል መብታቸውን እንዳይጠይቁ የሚከለክል በብዙ መልኩ ኢሕገ መንግሥታዊ ደንብ መሆኑን ይከራከራሉ።

አቤቱታው የደረሰበት ሌላ ምዕራፍና አንድምታው

 በሠራተኞቹ የቀረበው አቤቱታ አሁንም መቋጫ አላገኘም። ተመሳሳይ አቤቱታ በሌሎች ሠራተኞች በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኘው የአስተዳደር ፍርድ ቤት ቀርቦ በ2001 ዓ.ም. የሆነውን ተመሳሳይ መንገድ በመከተል፣ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቅርቧል። የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የመረመረው ጉባዔውም የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ውሳኔውን ሰጥቷል።

አጣሪ ጉባዔው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ደንብ ቁጥር 155/2000 አንቀጽ 37 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37/1 ጋር የሚቃረን ሆኖ እንዳገኘው በመጥቀስ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሐሳቡን እንደላከ በይፋ እሰታውቋል።

 ‹‹የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በሙስና የጠረጠረውንና እምነት ያጣበትን ማንኛውንም ሠራተኛ መደበኛውን የዲሲፕሊን ዕርምጃ አፈጻጸም ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት እንደሚችል፣ በተላለፈበት ውሳኔ ቅር የተሰኘ ሠራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት የለውም የሚለው የደንቡ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37/1/ ላይ ማናኛውም ሰው በፍርድ ቤት ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ ማግኘት እንደሚችል በመጥቀስ የሰጠውን መብት የሚጣረስ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› በማለት የአጣሪ ጉባዔው አዲስ ውሳኔ ያመለክታል።

በማከልም ‹‹የሕገ መንግሥቱን መርህ ተከትለው የወጡት ሕጎች ለማንኛውም የመንግሥት ሠራተኞች ተፈጻሚነት ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በተለየ የሕገ መንግሥቱን መርህ ባልተከተለ መንገድ ለአትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞች ብቻ ተብሎ የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሆኑን በመጥቀስና ድንጋጌው ከሕገ መንግሥቱ የሚጋጭ ስለሆነ፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል፤›› በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን ይገልጻል።

ቀደም ሲል ባደረጉት ጥናት የደንቡንም ሆነ የቀደመውን የአጣሪ ጉባዔ ውሳኔ ኢሕገ መንግሥታዊ ናቸው ሲሉ የተቹት በአሁኑ ወቅት የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ገረመው፣ አጣሪ ጉባዔው በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን የሰጠው ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን ይገልጻሉ።

አጣሪ ጉባዔው ቀድሞውንም ቢሆን ይኼንን መወሰን እንዴት አልቻለም? አሁንስ እንዴት ወደዚህ ውሳኔ ሊመጣ ቻለ? የሚል ጥያቄ በማንም ላይ ሊያጭር እንደሚችል የሚያምኑት አቶ እንዳልካቸው ‹‹መልሱ አጣሪ ጉባዔው የዳኝነቱ አንድ አካል ከመሆን ይልቅ የፖለቲከኛ ቁራኛ መሆኑን ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል።

ቀደም ሲል ደንቡ ከሕገ መንግሥቱ አይጣረስም ብሎ የሰጠው ውሳኔ በወቅቱ የፖለቲካ አስተዳደሩን ይጠቅም ስለነበረ እንደሆነ፣ ከሰሞኑ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የሰጠው ውሳኔም ትክክለኛ ቢሆንም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ አስተዳደር የለውጥ አየር እየተነፈሰ በመሆኑ፣ ከፖለቲካው አየር የሚስማማ ውሳኔ ለመወሰን መገደዱን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -