Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በታሰሩት የቀድሞ የማዕከላዊ አሥር መርማሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በታሰሩት የቀድሞ የማዕከላዊ አሥር መርማሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ

ቀን:

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር፣ የምርመራ ቡድን መሪና መርማሪ ሆነው ሲሠሩ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦነግ አባል ናቸው ተብለው በተጠረጠሩና በታሰሩ በርካታ ግለሰቦች ላይ ተገቢ ያልሆነ የምርመራ ዘዴ ተጠቅመዋል በተባሉ በአሥር የቀድሞ ማዕከላዊ መርማሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ተከሳሾቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ማዕከላዊ ታስረው የነበሩትን የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የኦነግ አባላትን ማዕከላዊ በሚገኘውና በተለምዶ ሳይቤሪያ በሚባለው ቀዝቃዛና ጭለማ እስር ቤት ውስጥ በማሰር፣ ለምርመራ በማለት በተለያዩ  ጊዜያት እንዲወጡ በማድረግ በቦክስ፣ በጥፊና በእርግጫ የተለያየ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ እንደ ደበደቧቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

‹‹የግንቦት ሰባት አባል ነኝ ብለህ እመን›› በማለት እጃቸውን በካቴናና በምስማር በማሰርና በማንጠልጠል፣ በኤሌክትሪክ ገመድ የውስጥ እግራቸውን በመግረፍ ምርመራ ማድረጋቸውንም አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ አባል እየመለመሉ ወደ ኤርትራ እንደሚልኩ፣ ወረቀት እንደሚበትኑና ይህንንም እንዲያምኑ በኤሌክትሪክ ሽቦ በመግረፍና የተወሰኑትን ጉልበታቸውን በመርገጥና የጉልበታቸው ሎሚ እንዲወልቅ በማድረግ፣ በእርግጫና በጥፊ ጆሮአቸውን በመምታት፣ በካቴና ብረት እግራቸውን በመምታትና በብልታቸው ላይ ውኃ በማንጠልጠል ምርመራ ያደርጉ እንደነበርም አክሏል፡፡

- Advertisement -

ተጠርጣሪዎቹን ግድግዳ በማስገፋትና በጣውላ እንጨት እግራቸውን በመምታት፣ ልብሳቸውን አውልቀው በሆዳቸው እንዲሳቡ በማድረግ፣ በመቀመጫቸውና በጀርባቸው ላይ ውኃ በመድፋት፣ በኤሌክትሪክ ሽቦ በመግረፍ፣ እጃቸውን በካቴና በማሰርና በመሀል እንጨት በማስገባት ተገቢ ያልሆነ የምርመራ ዘዴ ይጠቀሙ እንደነበርም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

የግንቦት ሰባትና የኦነግ አባል ናቸው ተብለው የታሰሩትን ግለሰቦች ጨለማና ጠባብ ክፍል ውስጥ በማሰር፣ ከባድና አድካሚ ስፖርት በማሠራት፣ ‹‹በእነ እከሌ ላይ ካልመሰከርክ አሥር ዓመታት ይፈረድብሃል›› በማለት ፂማቸውንና የብብት ፀጉራቸውን በመንጨት የማይገባ ምርመራ ይፈጽሙባቸው እንደነበርም ገልጿል፡፡

የአንዳንድ ተጠርጣሪዎችን የእግር አውራ ጣት ጥፍር በብረት ጉጠት በመንቀልና ‹‹ካላመንክ ሌሎች ጥፍሮችህም ይነቀላሉ›› በማለትና በማስፈራራት፣ ተገቢ ያልሆነ የምርመራ ዘዴ መጠቀማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ጥርሳቸውን በሽጉጥ አፈሙዝ በመምታት ጉዳት ማድረሳቸውንም አክሏል፡፡ እግራቸውን በገመድ በማሰርና በእግራቸው መሀል እንጨት በማስገባት በሁለት ጠረጴዛ መሀል በመገልበጥ በኤሌክትሪክ ገመድና በዱላ በመግረፍ፣ በግድግዳ ላይ አስሮ በማንጠልጠል አንድ እግራቸውን ከአንድ ምሰሶ ጋር በማሰርና ሌላው እግር እንዲንጠላጠል በማድረግ በመተባበር ተገቢ ያልሆነ ምርመራ ይፈጽሙ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የተወሰኑ ተከሳሾች ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃጠለውን የቂሊንጦን ማረሚያ ቤት እንዲያጣሩ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ተውጣጥቶ የተቋቋመ መርማሪ ቡድን ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን የጠቆመው ዓቃቤ ሕግ፣ እንዲያጣሩ ሽዋሮቢት ማረሚያ ቤት ሄደው መሥራታቸውን ገልጿል፡፡ ሄደው በሚሠሩበት ወቅት ወደዚያ የተወሰዱ እስረኞች ያልፈጸሙትን ተግባር እንዲያምኑና አንዳቸው በሌላኛው ላይ እንዲመሰክሩ በብረት ላይ በማሰርና በማንጠልጠል፣ በመግረፍ፣ ከምርመራ ክፍሉ ውጪ ባለ ረግረጋማና ጭቃ ቦታ ላይ በማሰር፣ በዱላና በብረት በመደብደብ ያሰቃዩዋቸው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀናለ) እና 424(1) ላይ ያለውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተገቢ ያልሆነ ምርመራና አሠራር በመከተል ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በክሱ ያካተታቸው ተከሳሾችም ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ፣ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፈዓይኔ፣ ዋና ሳጅን ኪዳኔ አሰፋ፣ ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን፣ ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግሥቱ ታደሰ፣ ረዳት ኢንስፔክተር ዓለማየሁ ኃይሉና ኢንስፔክተር ስንታየሁ ፈጠነ ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያቀረበው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለተከሳሾቹ ከሰጠ በኋላ ክስ ለማንበብና የክስ መቃወሚያ ካለ ለመቀበል ለየካቲቲ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...