Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ስምንት የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች...

ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ኢሰብዓዊ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ስምንት የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተከሰሱ

ቀን:

ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቂሊንጦ የጊዜ ቀጠሮ እስረኞች ማቆያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ፣ በኢሰብዓዊ ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በነበሩ ስምንት የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች ላይ ማክሰኞ የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቂሊንጦ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት የጥበቃ ደኅንነት ዘርፍ አስተባባሪ የነበሩት ዋና ኦፊሰር ገብረ ማርያም ወልዳይ፣ የአደጋ መከላከል ኦፊሰር የነበሩት ሱፐር ኢንቴንደንት አስገለ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ የጥበቃና ደኅንነት ዘርፍ አስተዳዳሪ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ሃዋርያት፣ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ፣ የሸዋ ሮቢት ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤት አስተዳዳሪ የነበሩት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ፣ በዋናው መሥሪያ ቤት የደኅንነት ከፍተኛ ባለሙያ የነበሩት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አዳነ ሐጎስና በዝዋይ ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤት የጥበቃ ዘርፍ አስተባባሪ የነበሩት ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን ናቸው፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በመሠረተው ክስ እንደገለጸው፣ ኦፊሰር ገብረ ማርያም አስገዳጅ ሁኔታን በማለፍ ወይም ሕጋዊ መከላከልን ከመጠን በመተላለፍ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን፣ በቂሊንጦ ማረፊያ ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በተነሳ ረብሻ ምክንያት ትዕዛዝ በመስጠት፣ የሁለት ሰው ሕይወት እንዲያልፍና በሁለት እስረኞች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

ሌሎቹም ተከሳሾች ከ400 በላይ የሚሆኑ እስረኞችን ወደ ሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤት በባዶ እግራቸውና በቁምጣ በመውሰድ፣ በባዶ ቤት ሲሚንቶ ላይ ማስተኛታቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ሁለት ሁለት አድርጎ በካቴና በማሰር ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ በማድረግ፣ በባዶ እግራቸው መፀዳጃ ቤት እንዲሄዱ በማድረግ፣ እጃቸውን ሳይታጠቡ ምግብ እንዲመገቡ በማድረግ፣ ሕክምና በመከልከል፣ ለ24 ቀናት ከአልጋ ጋር በማሰርና ለ24 ሰዓታት በካቴና በማሰር ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደፈጸሙባቸው በክሱ ተገልጿል፡፡

በቃጠሎ ምክንያት ወደ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት የተወሰዱት እስረኞች ምርመራቸውን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ፣ ‹‹ፍርድ ቤት ረበሻችሁ›› በማለት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት እጃቸውን በካቴና በማሰርና በጨለማ ቤት ለሦስት ወራት በማሰር፣ እንዲሁም ቤተሰብ እንዳያገኙ በመከልከል ሥልጣናቸውን ያላግባብ መገልገላቸውንም በዝርዝር አስረድቷል፡፡ በቃጠሎው ምክንያት ወደ ዝዋይ ተሃድሶ ልማት ማረሚያ ቤት የተወሰዱ እስረኞችን ደግሞ ልብሳቸውን በማስወለቅ፣ በቲሸርትና በቁምጣ ብቻ እንዲሆኑ በማድረግ፣ እጃቸውን በካቴና በማሰር፣ በዱላና በፌሮ እንዲደበደቡ በማድረግ ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደፈጸሙባቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ክስ በግልጽ ችሎት ለተከሳሾች እንዲደርስ ካደረገ በኋላ ክሱን በንባብ አሰምቷል፡፡ የተከሳሾችን የመጀመርያ ክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለየካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...