Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበዋስትና እንዲፈታ ተፈቅዶለት የነበረው የሶማሌ ክልል ወንጀሎች ተጠርጣሪ በሙስና ወንጀል ሊከሰስ ነው

በዋስትና እንዲፈታ ተፈቅዶለት የነበረው የሶማሌ ክልል ወንጀሎች ተጠርጣሪ በሙስና ወንጀል ሊከሰስ ነው

ቀን:

የክስ መመሥረቻ 15 ቀናት ተፈቀደበት

በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማና ሌሎች ከተሞች ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ግድያ፣ ቃጠሎ፣ መፈናቀልና ሌሎች ወንጀሎችን እንዲቀጣጠሉ በማድረግ ተጠርጥሮ ታስሮ የነበረው አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) በ80 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ ሳይፈጸም፣ በሙስና ወንጀል ክስ ለመመሥረት ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አቶ ቴዎድሮስ በክልሉ ከሚገኘው ትምህርት ቢሮ ኃላፊና ከኒያላ ኢንሹራንስ ጋር በመመሳጠር ፈጽሞታል ያለውን የሙስና ወንጀል አጣርቶ፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገቡን ማስረከቡን ለፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡

- Advertisement -

መርማሪ ቡድኑ አጣርቶ የጨረሰውን ወንጀል ድርጊት በሚመለከት እንዳስረዳው፣ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ የተለያዩ የመማርያ መጻሕፍት አትሞ ለመስጠት ከቢሮ ኃላፊው ጋር ውል ይዋዋላል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በገባው ውል መሠረት መጻሕፍት በወቅቱ አትሞ ለመስጠት ኒያላ ኢንሹራንስ ዋስትና እንደገባለት መርማሪው ገልጿል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በገባው ውል መሠረት 15.6 ሚሊዮን ብር ቅድሚያ ክፍያ የወሰደ ቢሆንም፣ መጻሕፍቱ በገባው ውል መሠረት ሊያስረክብ ባለመቻሉ በክልሉ የመማር ማስተማር ሒደት ላይ ችግር መፈጠሩን አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው በጥቅም በመመሳጠር ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቁሞ፣ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ገልጿል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግም የምርመራ መዝገቡን እንደተቀበለ አረጋግጦ፣ መዝገቡን መርምሮ ክስ ለማቅረብ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 109 (1) መሠረት 15 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪው የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት በፀረ ሙስና ሕግ አንቀጽ 434/2007 እና በተሻሻለው ልዩ ሥነ ሥርዓት 882/2007 ድንጋጌ መሠረት ከአሥር ዓመታት በላይ ሊያስቀጣው ስለሚችል፣ ዋስትናው ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ በጠበቃ አማካይነት ባቀረበው የመቃወሚያ መከራከሪያ ሐሳብ እንደተናገረው፣ ከታሰረ አራት ወራት አልፎታል፡፡ ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ ደግሞ የሚሠሩት አንድ ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ፖሊስ ሲመረምር የነበረውን ሥራ ዓቃቤ ሕግም ስለሚያውቀው፣ 15 ቀናት የክስ ማቅረቢያ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ እንዳልሆነ ጠበቃው አስረድተዋል፡፡ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉም ቢሆን የግድ 15 ቀናት እንዲሰጥ ስለማያስገድድ የተወሰኑ ቀናት ብቻ ሊፈቀድለት እንደሚገባ አክለዋል፡፡ ደንበኛቸው በሌላ መዝገብ ተጠርጥሮ ረዥም ጊዜ ከታሰረና ከተመረመረ በኋላ፣ ወንጀል ስላልተገኘበት ክስ ለመመሥረት ስላልተቻለ በዋስ እንዲለቀቅ ተፈቅዶለት እንደነበርም ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል፡፡

ሌላው ጠበቃው ያነሱት መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ ገና ባልተመሠረተና ሊጠቀስ ስለሚችለው የሕግ አንቀጽ ሳይታወቅ፣ ደንበኛቸው ዋስትና እንዲከለከል መጠየቁ የሕግ መሠረት ስለሌለው መከራከሪያ ሐሳቡ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ እሱ ከአራት ወራት በፊት ተጠርጥሮ ሲያዝ በኅትመት ሥራ ላይ የነበሩ ቀለም የተሞላባቸው አራት ማሽኖች፣ ቀለሙ ተጋግሮ ስላበላሻቸው ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ራሱ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በማተሚያ ቤቱ ውስጥ በርካታ ንብረቶች የነበሩ ቢሆንም፣ እሱ የቀጠራቸውን የጥበቃ ሠራተኞች የክልሉ ፖሊሶች በማባረር እንዲዘረፍ በማድረጋቸው በአሁኑ ጊዜ ማን ተጠያቂ እንደሚሆን ግራ እንደገባው ተናግሯል፡፡ በወቅቱ አንዱ ማሽን ዶላር አንድ ብር በ23 ብር ይመነዘር በነበረበት ወቅት የተገዛና 900 ሺሕ ብር ዋጋ ያለው በመሆኑ፣ አራት ማሽኖች ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ሲጠየቅ ፌዴራል ፖሊስ እንዳገደው፣ ፌዴራል ሲጠየቅ ክልሉ እንዳገደው እየተናገሩ አንዱ በአንዱ ላይ እያመሃኙ ንብረቱ ያለበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሲፈልግ ግን የሕግ አንቀጽ ጠቅሶ ተጠያቂ እያደረገው በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊሰጥለት እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ትዕዛዝ መስጠት የሚችለው በያዘው ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑን ገልጾ፣ ነገር ግን አቶ ቴዎድሮስን በቁጥጥር ሥር ያዋለው የፌዴራል ፖሊስ ከክልሉ ጋር በመነጋገር ሊያስተካክል እንደሚገባ አስታውቋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስም ክስ ማቅረብ እንደሚችል ገልጿል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ግን የአቶ ቴዎድሮስ ንብረትን ሲያሳግድም ሆነ ስላለበት ሁኔታ የማሳወቅ የሕግም ግዴታ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ተጠርጣሪው በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ስለሆነ፣ ሁሉንም ኃላፊነት መወጣት ያለበት ፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በማስታወቅ፣ እያንዳንዱ ፖሊስ የሚሠራውን ያህል ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስቧል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላም ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን 15 የክስ መመሥረቻ ጊዜ ፈቅዶ ለየካቲት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...