Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክበቀድሞ የንብ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ላይ የስም ማጥፋት ወንጀል አለመፈጸሙን ያረጋገጠው የጠቅላይ...

በቀድሞ የንብ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ላይ የስም ማጥፋት ወንጀል አለመፈጸሙን ያረጋገጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድና ውሳኔ

ቀን:

የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 613 የሌላውን ሰው ክብር ወይም መልካም ስም ለማጉደፍ በማሰብ፣ ‹‹እንደዚህ ያለውን ሥራ ሠርቷል፣ እንደዚህ ያለውን ነገር አድርጓል፣ ወይም እንደዚህ ያለ መጥፎ ነገር አለበት፤›› በማለት ለሦስተኛ ወገን ያስታወቀ ማንኛውም ሰው የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በእስራት ወይም በገንዘብ እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡

የዚህን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ በመተላለፍ ስማቸው መጥፋቱን በመግለጽ የቀድሞ የንብ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታፈሰ ቦጋለ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቅርበው ነበር፡፡

አቶ ታፈሰ፣ ‹‹በግብረ አበርነት ስም የማጥፋት ወንጀል ፈጽመውብኛል፤›› በማለት የባንኩ የቦርድ አባል የነበሩትን አቶ ኮሬ ባዌን ጨምሮ ሦስት ግለሰቦች ላይ ክሳቸውን አቅርበው ነበር፡፡

የክሳቸው ዋና ጭብጥ ተከሳሾቹ የእሳቸውን ክብር ወይም መልካም ስም ለመጉዳት በማሰብ እሑድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹እያጠፉ የጩኸቴን ቀሙኝ ክስ የትም አያደርስ፤›› በሚል ርዕስ ባንኩ የቅርንጫፍ ቢሮዎችን ሲከራይ ብዙ ችግር እንዳለበት በመግለጽ እንደሆነ በክሳቸው አስፍረው ነበር፡፡ ንብ ባንክ መገናኛ አካባቢ የሚገኘውንና የአቶ ታምራት አጋታ ንብረት የሆነውን ሕንፃ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለመከራየት አቶ ታፈሰ ያቀረቡትን ሐሳብ የባንኩ ቦርድ አበላት ሳይቀበሉት ይቀራሉ፡፡ አቶ ታፈሰ በድጋሚ ሐሳቡን ሲያቀርቡ፣ የቦርድ አባላቱ ሕንፃው ያለበት ቦታ ድረስ በመሄድ ከተመለከቱ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ውድቅ ቢያደርጉትም፣ ‹‹በድርጅታዊ አሠራርና በተለመደው መንገድ እንዲከራይ፤›› በማለት ጽሕፈት ቤቱን ይከራያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ኮሬ፣ ቤቱን ለመከራየት ከተደረሰበት ውሳኔ (ስምምነት) ጀርባ፣ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታፈሰ ቦጋለ መመሳጠር ያለበት መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሱትም አቶ ታፈሰ ቦሌ ወደ ፒኮክ መናፈሻ መታጠፊያ ላይ በስተግራ በኩል የነበረው፣ ‹‹ኤሌፋንት ወክ›› የሚባለው ካፌያቸው በልማት ምክንያት ሲፈርስባቸው፣ ለባንኩ ቅርንጫፍ ቢሮ ያከራዩት አቶ ታምራት አጋታ የሚባሉት የሕንፃው ባለቤት፣ በዚያው አካባቢ ከኤሌፋንት ዎክ ፊት ለፊት ቦሌ ማተሚያ ቤት አጠገብ ከመንግሥት ተከራይተው ልብስና ጫማ ይነግዱበት የነበረን ሱቅ ኤሌፋንት ዎክ ካፌ እንዲከፈትበት በመደረጉ ነው፡፡ ‹‹ይኼ ግምት ማለትም አቶ ታፈሰና ሕንፃ አከራዩ አቶ ታምራት አጋታ መመሳጠራቸው እኛንም ሆነ የሁሉንም ሰው ግምት የሚያጠራጥር አይደለም፤›› በሚል አቶ ኮሬ ጽሑፍ አዘጋጅተው በሪፖርተር ጋዜጣ ታትሞ እንዲሠራጭ በማድረግ ክብራቸውን ወይም መልካም ስማቸውን ማጉደፋቸውንና ማጥፋታቸውን ዘርዝረው ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡    

አቶ ታፈሰ በፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ የመሠረቱት የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅን ጨምረው በሌሎች ሦስት ግለሰቦች ላይ የነበረ ቢሆንም፣ በክርክር ሒደት በሪፖርተር ዋና አዘጋጅ ላይ የቀረበውን ክስ ያነሱ ሲሆን፣ ሌሎች ሁለት ተከሳሾች ደግሞ በመሞታቸው ክሳቸው ተቋርጦ ክርክሩ ከአቶ ኮሬ ጋር ቀጥሏል፡፡ አቶ ኮሬ የቀረበባቸውን ክስ ክደው በመከራከራቸው የሰው ምስክር እንዲሰማ ተደርጓል፡፡ አቶ ታፈሰ መሃላ ፈጽመው መስክረዋል፣ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ምስክርነቱንና ሰነዱን መርምሮ አቶ ኮሬ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ከሳሽ አቶ ታፈሰን ጨምሮ መከላከያ ምስክር ያቀረቡት አቶ ኮሬ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክና የሪፖርተር ጋዜጣን የሰነድ መከላከያ ማስረጃ አድርገው አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን የሰውና የሰነድ መከላከያ ምስክር መዝኖ፣ አቶ ኮሬ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል መቻላቸውን ገልጾ፣ በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኙት አቶ ታፈሰ ውሳኔውን በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ መልካም ስማቸው መጥፋቱንና ጉዳት እንደደረሰባቸው ለሥር ፍርድ ቤት በዝርዝር በማቅረባቸው፣ ተከሳሹን አቶ ኮሬን ‹‹ይከላከሉ›› ያላቸው ቢሆንም፣ ተከሳሹ የቀረበባቸውን የሰው ምስክርነትና የሰነድ ማስረጃዎችን ማስተባበል ሳይችሉ ወይም በብቃት ሳይከላከሉ በነፃ መሰናበታቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት አቶ ታፈሰ አቤቱታቸውን ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ አቶ ኮሬ ለሥር ፍርድ ቤት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የጻፉት ጽሑፍ የንብ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ቀደም ብሎ በጋዜጣው ለጻፈው መልስ መሆኑን ማስረዳታቸው፣ ተገቢነት የሌለው መሆኑን አቶ ታፈሰ በይግባኛቸው ጠቅሰዋል፡፡ የንብ ባንክ ቦርድና እሳቸው (አቶ ታፈሰ) የተለያዩ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ የባንኩ ቦርድ አባላት ጽሑፍ ይዘትም የማንንም ስም የማይጠራ መሆኑንና በተለየ ምክንያት የተጻፈ መሆኑን አስረድተው፣ አቶ ኮሬ ‹‹ለተጻፈ ጽሑፍ መልስ ነው፤›› ማለታቸው ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ‹‹የቦርዱ ሊቀመንበር (አቶ ታፈሰን) ከሕንፃው አከራይ ጋር ተመሳጥረዋል፤›› ያሉበትንና የግል ጥቅም መኖሩን ሳያስረዱ በነፃ መሰናበታቸው ተገቢ ባለመሆኑ እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡

የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ (አቶ ታፈሰ) ከባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የአብላጫ ድምፅ ውሳኔን በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ከሌሎች አባላት ጋር መወሰኑም ሆነ ውሳኔው እንዲፈጸም ማድረግ ሕጋዊ ሥራው እንጂ ሕገወጥ ሥራ እንዳልሆነ በይግባኛቸው አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የዳይሬክተሮች ቦርድ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቁትን የኪራይ ውል ፍጻሜ እንዲያገኝ ማድረግም የቦርድ ሰብሳቢ ግዴታ መሆኑም አክለዋል፡፡ ክሳቸው (አቶ ታፈሰ) ከሕንፃ አከራይ ጋር ተመሳጥረው ያገኙት የግል ጥቅም ወይም ያስገኙት ጥቅም ስለመኖሩ አቶ ኮሬ ያቀረቡት ማስረጃ በሌለበት በነፃ ሊሰናበቱ እንደማይገባም በይግባኝ አቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡ መገናኛ አካባቢ ንብ ባንክ የተከራየው ቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ ባለቤት አቶ ታምራት አጋታንም በአባልነት ከመተዋወቃቸው በስተቀር ዝምድና እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡ አቶ ኮሬ በግምትና በወሬ ብቻ በአሉባልታ የእሳቸውን (የአቶ ታፈሰን) ክብር ለመጉዳትና መልካም ስም ለማጥፋት ሲሉ ጽፈውና ፈርመው ለሪፖርተር ጋዜጣ በመስጠት እንዲሠራጭ ማድረጋቸውን አቶ ታፈሰ በይግባኝ አቤቱታቸው ላይ ዘርዝረዋል፡፡

ቀደም ብሎ የባንኩ ቦርድ አባላት ለሌላ ዓላማ ‹‹ንብ ባንክን እንታደግ›› በሚል በሪፖርተር ካወጣው ጽሑፍ ጋር ሲነፃፀርም በሥር ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ መከላከል የሚያስችላቸው ካለመሆኑም በተጨማሪ፣ ከተከሰሱበት ወንጀል ጋርም አብሮ የሚሄድ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ኮሬ በግላቸው፣ ‹‹አቶ ታፈሰ በቦርድ ሰብሳቢነታቸው የሥራ ጉድለት ፈጽመዋል፤›› በማለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ምርመራ ጉድለት አለመገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤት አቶ ኮሬ ነፃ ናቸው ብሎ የሰጠው ውሳኔ ተሽሮ፣ ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ፣ ከተመሳሳይ ድርጊት እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ቅጣት እንዲጣልባቸው ይግባኝ ሰሚውን ፍርድ ቤት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታፈሰ በይግባኝ አቤቱታቸው እንደገለጹት፣ ክሱ ወንጀል ቢሆንም የመሠረቱት ግን በራሳቸው ነው፡፡ ይኼንን ያደረጉት ደግሞ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ሕግ ቁጥር 211 መሠረት ክስ ማቅረብ እንደሚችሉ በመፍቀዱ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 43 (7) መሠረትም ክሱን በግል ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የይግባኝ አቤቱታውን መርምሮ የሥር ፍርድ ቤት አቶ ኮሬ የቀረበባቸውን ማስረጃ በማየት ‹‹ተከላክለዋል›› በማለት በነፃ ያሰናበታቸው ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ለማጣራት ‹‹ያስቀርባል›› ብሏል፡፡

አቶ ኮሬ ለይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክርክር እንዳብራሩት፣ አቶ ታፈሰ ክስ እንዲያቀርቡ ፍትሕ ሚኒስቴር አልፈቀደም፡፡ የድርጊቱ ይዘት በወንጀል ሕግ 613 እና በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 43 የሚሸፈን ነው፡፡ አቤቱታውም በፖሊስ የሚጣራ አይደለም፡፡ ዓቃቤ ሕግም ክስ የሚመሠርትበት ጉዳይ አይደለም፡፡ በወንጀል ሕግ ቁጥር 211 መሠረት ‹‹ተፈቅዶልናል›› ቢሉም አቅጣጫ ማሳየቱ እንጂ ራሳቸው ክስ እንዲመሠርቱ መፍቀዱ አይደለም፡፡ ክስን በግል ማቅረብ የሚቻለውም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 44 መሠረት መሆኑንና ይኼም የሚሆነው ምርመራ ተጣርቶ በዓቃቤ ሕግ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ፣ ክስ አቅራቢ ካልተስማማ መሆኑን በመልሳቸው አብራርተዋል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ኮሬ ክሱን ይርጋ የሚያግደው መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ታፈሰ መልካም ስማቸውና ክብራቸው የተጎዳውና የጠፋው፣ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በተጻፈ ጽሑፍ መሆኑን ጠቁመው፣ ክስ ያቀረቡት ግን ከአራት ወራት በኋላ የካቲት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በወንጀል ሕግ ቁጥር 213 መሠረት የግል ክስ ማቅረብ የሚቻለው በሦስት ወራት ውስጥ መሆኑን ጠቁመው፣ ይርጋ እንደሚያግደው አክለዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት ደግሞ ማንም ሰው የመሰለውን መናገርና አመለካከቱን የመግለጽ መብት እንዳለው በመግለጽ ይግባኙ ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዝርዝር እንዳስረዳው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 24 (1) እንደተደነገገው ማንም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ መከበር አለበት፡፡ አንቀጽ 29 (2) ደግሞ ማንም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው፡፡ በንዑስ አንቀጽ (7) ደግሞ የተፈቀደው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጥሶ የተገኘ በሕግ የሚቀጣ መሆኑንም አብራርቷል፡፡ ከሕጉ ድንጋጌ  መረዳት የሚቻለው ሐሳብን በነፃነት መግለጽ መብት ቢሆንም፣ እውነት ያልሆነንና ያለ ማስረጃ ከሆነ የሚያስጠይቅ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ተንትኗል፡፡ አቶ ኮሬ ያቀረቡትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከሕጉ አንፃር ሲመዘን፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የጻፉት በቦርድ አባልነታቸው በውሳኔ ያልተስማሙበትን ‹‹ሊሆን ይችላል›› በማለት የገመቱትን ነው ከማለት በስተቀር የአቶ ታፈሰ ድርጊት ከንብ ባንክ ጥቅም ጋር የተጋጨ መሆኑን በማስረጃ አረጋግጠው ነው ለማለት እንደማይቻል ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡ አቶ ኮሬ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያወጡት ጽሑፍ አንድም በጥቅም ግጭት ምክንያት ወይም አቶ ታፈሰን ለመጉዳት በማሰብ ከሥልጣን ጋር በተያያዘ የጻፉት መሆኑን ስለሚያሳይ፣ ሆን ብለው ስም ለማጥፋት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ድምዳሜ ላይ መድረሱን አብራርቷል፡፡ አቶ ኮሬ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 613 (1)ን በመተላለፍ የስም ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በማለት የእስራት ቅጣትን ወደ ገንዘብ በመቀየር 1,000 ብር እንዲቀጡና የአቶ ታፈሰ ቦጋለ ገብረ ወልድ የጠፋ ስምና የተጎዳን ክብር እንዲመልሱ ትዕዛዝ በማስተላለፍ፣ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔን ሽሮ ነበር፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቅር የተሰኙት አቶ ኮሬ ባዌ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የክርክሩ አመጣጥን ከመረመረ በኋላ ‹‹ያስቀርባል›› በማለት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 192 ድንጋጌ መሠረት ሁለቱንም ተከራካሪ ወገኖች በማስቀረብ አከራክሯል፡፡

ክርክሩን የመረመረው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ‹‹የወንጀል ሕግ አንቀጽ 613 (1) የተደነገገውን በሚያሟላ መንገድ በአቶ ታፈሰ ቦጋለ ላይ የስም ማጥፋት ወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል?›› የሚለው ጭብጥ ምላሽ ማግኘት የሚገባው መሠረተ ሐሳብ መሆኑን እንዳመነበት በውሳኔው ገልጿል፡፡

አቶ ኮሬ ከመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ባደረጉት የግራ ቀኝ ክርክር፣ በክሱ ፍሬ ነገር ላይ የተገለጸውንና ‹‹የስም ማጥፋት ድርጊት ነው›› የተባለውን ስለመጻፋቸውና በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስለመታተሙ ያልካዱና ክሱን በሚመለከትም አለመከራከራቸውን ገልጿል፡፡ እንዲያውም አከራካሪ የሆነው ጉዳይ፣ የተጻፈውና በጋዜጣው ላይ የታተመው ፍሬ ነገር እውነት በመሆኑ ‹‹የስም ማጥፋት ወንጀል አይደለም፡፡ ይኼንንም በማስረጃ አረጋግጠናል፤›› የሚልና የቀረበው ክስ በይርጋ የሚታገድ ሆኖ እያለ ታልፎ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠቱ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጽ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ ገልጿል፡፡ በይርጋ መታገድ እንዳለበት ገልጸው፣ አቶ ኮሬ ክሱ ውድቅ እንዲደረግላቸው ያቀረቡትን መከራከሪያ ሐሳብ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎ፣ ለሁለቱ ከተራካሪ ወገኖች ለክስ መነሻ ወደሆነው ነገር ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ በመሆኑም አቶ ታፈሰ የንብ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ፣ መገናኛ አካባቢ ሕንፃ አላቸው ከተባሉት አቶ ታምራት አጋታ ባንኩ ቅርንጫፍ ቢሮ ለመከራየት ያቀረበውን ሐሳብ የባንኩ ቦርድ ሁለት ጊዜ በሙሉ ድምፅ ውድቅ ካደረገው በኋላ፣ ጥያቄው ለሦስተኛ ጊዜ ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ ተቀባይነት አግኝቶ ለመወሰኑና አቶ ኮሬ ባዌ እንደ ቦርድ አባልነታቸው ተቃዋሚ ሆነው ከውሳኔ ሐሳቡ መለየታቸውን ከቀረበው ክርክር የሰነድ ማስረጃ መረዳት መቻሉን ፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በተያያዥነት የተመለከተው፣ በንብ ባንክ የቦርድ አባላት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ጉዳዩ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡንና አቶ ታፈሰ ከቦርድ ሊቀመንበርነታቸው የታገዱ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሕንፃው ኪራይ ጋር በተያያዘ መሆኑ የታመነ ፍሬ ነገር መሆኑንም አክሏል፡፡

ሌላው የተረጋገጠው ፍሬ ነገር የአቶ ታፈሰ ንብረት የሆነው ኤሌፋንት ዎክ የሚባለው ካፌ ከነበረበት ቦታ በመፍረሱ ምክንያት፣ ለንብ ባንክ አክሲዮን ማኅበር መገናኛ አካባቢ ያለውን ሕንፃቸውን ያከራዩት አቶ ታምራት አጋታ፣ በፈረሰው ኤሌፋንት ዎክ ካፌ ፊት ለፊት ቦሌ ማተሚያ ቤት አካባቢ ከኪራይ ቤቶች የተከራዩትን የልብስና የጫማ መሸጫ ሱቅ ኤሌፋንት ዎክ ካፌ እንዲከፈትበት በማድረጋቸው መሆኑ በፍርዱ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን አቶ ታፈሰ የንግድ ድርጅቱን የወሰዱት በንግድ ድርጅት የሽያጭ ውል መሆኑንም መገንዘብ መቻሉን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ጠቁሟል፡፡ ይኼ ነገር የሚያሳየው አቶ ታምራት አጋታ መገናኛ አካባቢ ያለውን ሕንፃቸውን ለንብ ባንክ ከማከራየታቸው በፊት ከአቶ ታፈሰ ጋር በውል የተመሠረተ ግንኙነት ይሁን ወይም በሌላ ግንኙነት የነበራቸው መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም አክሏል፡፡ ባንኩ ሕንፃውን ከመከራየቱ በፊት ሁለቱ ግለሰቦች ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ ይኼ ደግሞ አቶ ታፈሰ የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ በሆኑበት ጊዜ ስለሕንፃ ኪራዩ ሁለት ጊዜ ውድቅ የተደረገን የኪራይ ጥያቄ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ሐሳብ ቀርቦ በአብላጫ ድምፅ ባንኩ ከአቶ ታፈሰ ጋር ግንኙነት የነበረውን ግለሰብ ሕንፃ እንዲከራይ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው፣ በማንኛውም ምክንያታዊ ሰው ሲታይ አቶ ታፈሰ የአቶ ታምራት አጋታን ሕንፃ ባንኩ እንዲከራይ የተለየ ፍላጎት የነበራቸው መሆኑን እንደሚያሳይ አስረድቷል፡፡ ይኼም ከነበራቸው ግንኙነት አኳያ መሆኑንና ይኼንንም ግምት መውሰድ ‹‹ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ነው ወደሚል ድምዳሜ የሚያደርስ አይደለም፤›› ብሏል፡፡

በመሆኑም አቶ ኮሬም ሆኑ ሌሎቹ በሥር ፍርድ ቤት በአቶ ታፈሰ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ግለሰቦች ግምታቸውንና ለግምታቸው መነሻ ያደረጉትን ፍሬ ነገሮች በመግለጽ በክሱ ላይ የተገለጹትን ፍሬ ነገሮች በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ማሳተማቸው፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 613 (1) በተደነገገው አግባብ የስም ማጥፋት ወንጀል ነው ወደሚል መደምደሚያ የሚያደርስ ሆኖ እንዳላገኘው፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 187791 በአቶ ኮሬ ላይ የሰጠውን የጥፋተኝት ውሳኔ በመሻር አቶ ኮሬ ጥፋተኛ አይደሉም ብሎ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 30056 የሰጠውን ውሳኔ በማፅደቅ መዝገቡን ዘግቶታል፡፡               

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...