Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ነፃና ገለልተኛ ሆኜ ለመምራት ተስማምቼ ስለሆነ ዳኞች ያለ ምንም ፍርኃት በነፃነት እንዲሠሩ ዋናው ፍላጎቴ ነው››

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

ከሦስት ወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅራቢነት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ለቤተሰቦቻቸው አምስተኛ ልጅ ሲሆኑ፣ ተወልደው ያደጉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ነው፡፡ አባታቸው የአሶሳ ከተማ ከንቲባ እንደነበሩ የሚናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሶሳ ከተማ ተከታትለው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወስደው ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በጀማሪ የሕግ ባለሙያነት ሥራቸውን በንግድ ሚኒስቴር ጀምረው ጥቂት ጊዜ ከሠሩ በኋላ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ለሦስት ዓመታት በዳኝነት ከሠሩ በኋላ፣ በሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን የሕግ አማካሪ ሆነው ከእነ አቶ ክፍሌ ወዳጆ ጋር ሠርተዋል፡፡ አቶ ክፍሌ ወዳጆን ጨምሮ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ የተለያዩ  ምሁራን ያሳደሩባቸው በጎ ተፅዕኖ በሕዝብ አገልግሎት ዙሪያ እንዲያዘነብሉ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ሥራ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሴት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርን በመመሥረት ለስምንት ዓመታት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መርተዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ይሠራ የነበረውን ኢንተር አፍሪካ ግሩፕን ለአንድ ዓመት ከመሩ በኋላ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ወደ አሜሪካ አምርተዋል፡፡ በኒውዮርክ ሲቲና ቦስተን መካከል ከሚገኘው ኪነቲካ ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ሥርዓተ ፆታ (Gender) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተው፣ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በሥርዓተ ፆታ አማካሪነት ተቀጥረው እየሠሩ፣ ጎን ለጎን እናት ባንክን በማቋቋም ለስድስት ዓመታት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በተለይ ለሴቶች መብት ተቆርቋሪ ሆነው የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወናቸው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ ከኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወ/ሮ መዓዛ በተለይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ በፍትሕ ላይ እየተሠሩ ስለሚገኙ ሪፎርሞችና ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም አጠቃላይ የፍትሕ ጉዳዮች ላይ ከታምሩ ጽጌ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሦስት ወራት በፊት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል፡፡ እርስዎ እንደሚሾሙ ቀድመው ያውቁ ነበር? ጥያቄው የቀረበለዎት በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው? ወይስ ሌላ አካሄድ ነበረው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ እሾማለሁ ብዬ አላሰብኩም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላትን 50 በመቶ ሴቶችን ሊያደርጉ እንደሆነ ስሰማ በጣም ተደስቼ ነበር፡፡ የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከት አብዛኛውን የዕድሜን ክፍል የሠራሁበትና የደከምኩበት በመሆኑ ስሰማ በጣም ተደስትኩ፡፡ አንዲት ሴት የመምርያ ኃላፊ ለማድረግ በማይቻልበት አገር 50 በመቶ የካቢኔ ቦታ መስጠት ትልቅ መና ነው፡፡ አንድ ስማቸውን መግለጽ የማልፈልገው የመንግሥት ኃላፊ ሐሳቡን አቀረቡልኝ፡፡ እኔን ሳይሆን ሌላ ሰው እንድጠቁማቸው መስሎኝ፣ ‹‹እኔ ከፍርድ ቤት አካባቢ ከራቅሁ ቆይቻለሁ፡፡ እስቲ ላፈላልግና እነግርዎታለሁ፤›› ብያቸው ተለያየን፡፡ ሌላ ጊዜ ደውለው፣ ‹‹የያዝነው የአንቺን ስም ነው፤›› ሲሉኝ ምላሼ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ምክንያቱም እየሠራሁ ያለሁት በሌላ አቅጣጫ (ስትሪም) ውስጥ በመሆኑና ሠርቼም ልጆች ማስተማር ስላለብኝ ምላሼ የእውነት ነበር፡፡ ባለቤቴንና ጓደኞቼን ሳማክር፣ በአንቺ ሙያ ከዚህ የበለጠ ክብር ከየት ይመጣል? ለሌላው ነገር ሌላ ዘዴ ይፈለግለታል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የሽግግር ጊዜ ማገልገል ካለብሽ መሆን ያለበት አሁን ነው ሲሉኝ፣ እኔም ትንሽ አሰብኩበትና አመንኩበት፡፡ መስማማቴን ገለጽኩኝና ሹመቱን ተቀበልኩ፡፡   

ሪፖርተር፡- ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ በኋላ በአጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱን እንዴት አገኙት? ብዙ ጩኸት ያለበት ተቋም ከመሆኑ አንፃር ሥራዎን ከምን ጀመሩ?  

ወ/ሮ መዓዛ፡-  የሚገርምህ ነገር የገጠሙኝ ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው ተቋሙ ይኼንን ያህል ትልቅ አልመሰለኝም ነበር፡፡ በፌዴራል ጠቅላ ፍርድ ቤት 49 ዳኞች፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከ100 በላይ ዳኞች፣ በፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከ180 በላይ ዳኞች፣ እንዲሁም ባለሙያዎችና ደጋፊ ሠራተኞች በአጠቃላይ ከ3,000 በላይ አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥራ ፍርድ ቤቶችን ብቻ ማስተዳደር አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ፣ የፍትሕ አካላትና የዴሞክራቲክ ተቋማት፣ የሕግ ምርምርና ጥናት ኢንስቲትዩትና የመሳሰሉትም በእሱ ሥር ናቸው፡፡ ሌላው ቢቀር ከእነሱ ጋር ተገናኝቶ ለመነጋገር የሚወስደው ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ አንዳንዶቹ መልክ ያልያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ እየሠራ ነው፡፡ ከ4,000 በላይ ጉዳዮችን እያየ ነው፡፡ ፍርድ ቤት ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይኼ የሚያሳየው ተቋሙ ምንም ዓይነት የአሠራር መመርያ (ፕሮሲጀር) የለውም፡፡ ሰበር ችሎት ላይ የተፈረደበት ሁሉ ወደ ጉባዔው ይሄዳል፡፡ ጉባዔው የተቋቋመው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም የሚስፈልጋቸውን ጉዳዮች አጣርቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ፣ ወይም የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደማያስፈልገው ለመግለጽ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን የአሠራር ሥርዓት መመርያ እያዘጋጀን ነው፡፡ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሌሎችም ተቋማት አሠራራቸው መስተካከል ያለበት ሆኖ አግኝተናቸዋል፡፡    

ሪፖርተር፡-  ሥራ እንደጀመሩ የፍትሕ ተቋማት የሚባሉትን ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎችን ከጎበኙ በኋላ፣ የፍርድ ቤት ተዋናዮችን ማለትም ጠበቆችን፣ ዳኞችንና ደጋፊ ሠራተኞችን ሲያነጋግሩ ቆይተዋል፡፡ ያገኟቸው ምላሾች ምንድናቸው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ሌላው ቀርቶ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውስጥ ያሉ ዳኞች እንኳን እርስ በርስ ተነጋግረው አያውቁም፡፡ ዳኞችና ጠበቆች ተቀራርበው አይነጋገሩም፡፡ ጠበቆች በፍርድ ቤት አሠራር ላይ እንኳን አስተያየት ሊሰጡ ቀርቶ በግል ጉዳይ ላይ እንኳን መነጋገር የማይችሉበት አሠራር ነበር የነበረው፡፡ ሁሉንም በተናጠል በማነጋጋራችን ብዙ ግብዓት አግኝተናል፡፡ እኔ ከፍርድ ቤቱ ራቅ ብዬ በመቆየቴ ከውይይቱ ብዙ መረጃዎችን ማግኘት ችያለሁ፡፡ ሁሉም ከራሱ አኳያ የሚያቀርበው አስተያየት አለ፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ከአገር አቀፍ (ከሁሉም ክልሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር) የፍትሕ አካላት ጋር ውይይት በመደረጉ ለሪፎርሙ ብዙ ግብዓት ለማግኘት ችለናል፡፡ ሌላው የውይይቱ ጥቅም በራስ መተማመን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ሁሉም የየራሳቸው ቁጭት አላቸው፡፡ ፍትሕ ሰፍኖ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በአንድም በሌላ የሚሠሩት በፍትሕ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ቀርበው ባለመነጋገራቸው ልዩነታቸው እየሰፋና እየተፈራሩ ነው የቆዩት፡፡ ሌላው በተለይ ለዳኞች በውይይቱ ትልቅ መልዕክት ማስተላለፍ ችያለሁ፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ የምትሠሩት ነፃና ገለልተኛ ሆናችሁ ለሕዝብ፣ ለሕገ መንግሥቱና ለህሊናችሁ ብቻ ታማኝ ሆናችሁ ነው፤›› ብዬ መናገር ችያለሁ፡፡ በሥራቸው ጣልቃ የሚገባ ካለ እንዲያሳውቁኝ ገልጬላቸዋለሁ፡፡ ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ነፃና ገለልተኛ ሆኜ ለመሥራት ተስማምቼ ስለሆነ ዳኞች ያለ ምንም ፍርኃት በነፃነት እንዲሠሩ ዋናው ፍላጎቴ ነው፡፡ ቀደም ብሎ የምንሠራበት መንገድ ተቀይሮ አዲስ አሠራር በአዲስ መንፈስ የምንጀምርበት ወቅት መሆኑንም መልዕክት ያስተላለፍኩበት በመሆኑ፣ በውይይቶቹ ብዙ ነገሮችን አግኝተናል፡፡ ለጀመርነው ሪፎርም አስተዋጽኦው ብዙ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ዳኞችና ጠበቆች፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ስለፍትሕ ሥርዓቱ የሚገልጹበት መንገድ ወይም አረዳድ የተለያየ ነው፡፡ ይኼንን የተለየ ሐሳብ ወደ አንድ አምጥቶ የሪፎርሙ ግብዓት ለማድረግ እንዴት ይቻላል? 

ወ/ሮ መዓዛ፡- በሁሉም አካል የሚነገረውና የሚቀርበው ችግር በአጭር ጊዜ መፍትሔ አያገኝም፡፡ ነገር ግን አሁን ሪፎርም ላይ እኔ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር ግንኙነት ስለነበረኝ፣ በአጭር ጊዜ ሪፎርም እንዴት መሥራት እንዳለብን ለማሰባሰብ ችያለሁ፡፡ ለምሳሌ ቀደም ብለው የሚሠሩ ቢኖሩም፣ አዲስ ኃይል ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ሁለት ባለሙያዎችና ከፍተኛ አማካሪዎች (ሪፎርሙ ላይ የሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች)፣ እንዲሁም በአንድ ካናዳዊ ኤክስፐርት በመታገዝ እየሠራን ነው፡፡ ለተለያዩ ለጋሾች ፕሮፖዛል ጽፈን እየሰጠን የሪፎርሙን ሥራ ለማፋጠንም እየሠራን እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ከውይይቶች ያገኘናቸው ግብዓቶች እንደየ አገባባቸው በሪፎርሙ እንዲካተቱ ይደረጋሉ ማለት ነው፡፡ ሌላው በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር ተቋቁሞ ከነበረው ብሔራዊ የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት፣ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸውና በተለያዩ ቦታዎች በመሥራት ሰፊ ልምድ ያካበቱ 18 አባላት ወደ እኛ ተቋም መጥተው እያገዙን እየሠራን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙ ሕጎችን ማሻሻል ወይም ሙሉ በሙሉ መለወጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዋናው ሪፎርም መሠራት ያለበት በሰዎች ላይ መሆን እንዳለበት፣ በዳኞች ላይ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ሕጉ ብቻ ለውጥ አያመጣም የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን እየተሠራ ነው?  

ወ/ሮ መዓዛ፡- ትክክልና ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በቅርቡ ለዳኞች ሥልጠና መስጠት ጀምረናል፡፡ ሥልጠናው በሙግት አመራር ሥርዓት ዙሪያ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጋችን እንዴት እንደሚጀመርና እንደሚካሄድ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ መቼ ተጀምሮ መቼ ማለቅ እንዳበት በሥነ ሥርዓቱ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ዳኞችም ሆኑ ጠበቆች ያንን አይከተሉም፡፡ ያ በመሆኑ ጉዳዮችን (ክርክሮች) እንዲጓተቱ ያደርገዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ቢመራ ኖሮ ቀልጣፋና ተገማች የሆነ ውሳኔ ይገኝ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ሥልጠና መስጠት ጀምረናል፡፡ በሌሎም ወሳኝ በሆኑ የፍርድ ቤት አሠራሮች ላይ ሥልጠና መስጠትን እንቀጥላለን፡፡ ሌላው የጀመርነው የዳኞች ሴሚናር ነው፡፡ ዳኞች ተነጋግረው አያውቁም፡፡ በአንድ ችሎት ውስጥ የሚሠሩ ዳኞች ምናልባት የሚነጋገሩት በአንድ ጉዳይ (Case) ላይ ሲወያዩ ብቻ ነው፡፡ አንድ ላይ ቁጭ ብለው ውይይት በማድረግ ስለሚያጋጥሟቸው ነገሮች ሐሳብ ተለዋውጠው አያውቁም፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኞች ሴሚናር (Judges Seminar) ብለን በወር አንድ ጊዜ ለማካሄድ ጀምረናል፡፡ ባለመነጋገራቸው በአንድ ሰበር ችሎት የሚሰጥ ውሳኔ በሌላ ሰበር ችሎት በተመሳሳይ ሁኔታ ቢቀርብም ሌላ ውሳኔ ይሰጣል፣ ተሰጥቷልም፡፡ አሁን በተጀመረበት ሁኔታ በአጭር ሰዓት ያልቃል ያልነው ውይይት ረዥም ሰዓት ወስዶ ነው የተጠናቀቀው፡፡ በመነጋገራቸው ትልቅ ሀብት (Resource) ነው የተገኘው ወይም እንዳለ የታወቀው፡፡ ይኼ ውይይት ወደ መገናኛ ብዙኃን መወሰድ አለበት የሚል አቋም ይዣለሁ፡፡ መዝገቦችን በማይነካ ሁናቴ ከውይይቱ ሕዝቡ መማማር አለበት፡፡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተጀመረው ሴሚናር በሥር ፍርድ ቤቶችም በወር አንድ ቀን መቀጠል አለበት፡፡       

ሪፖርተር፡- ለፍትሕ ሥርዓቱ መበላሸት ትልቁን ድርሻ ይዘዋል የሚባሉት በተለይ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየው የትምህርት አሰጣጥ፣ የዳኞች ምልመላና የባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የሚሾሙ ዳኞች ታማኝነታቸው ለሕዝቡ፣ ለህሊናቸውና ለሕገ መንግሥቱ መሆን ሲገባው አባል ለሆኑበት የፖለቲካ ድርጅትና ለሥርዓቱ በመሆኑ፣ በጅምላ ሥልጠናና ሴሚናር መስጠቱ ሀብትና ጊዜ ከማባከን ያለፈ ምን ለውጥ ያመጣል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ችግር ነበር፣ አለም፡፡ አንዳንዱ ችግር ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንዱ ችግር ደግሞ ከዳኞች አሿሿም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከዚያም በላይ ነው፡፡፡ የትምህርት ጥራትን እንደ ምሳሌ ማንሳት እንችላለን፡፡ በእርግጥ የትምህርት ጥራት በሕግ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ፕሮግራሞች (ትምህርት ዘርፎችም) ያለ ችግር ነው፡፡ ትክክል ነው፡፡ አገራችን በሁሉም ዘርፍ ብቃት ያለው ባለሙያ ቢኖራት ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ችግሮቻችን ሁሉ ከብቃት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ በተለየ ሁኔታ ወደ ዳኝነት ስንመጣ ግን ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነገር (Political Orientation) ነበረው፡፡ የዳኞች አመላመል፣ ፈተና አሰጠጥና አመዳደቡ ፖለቲካዊ ንክኪ ነበረው፡፡ ይኼንን ስንል ግን ሁሉንም ሳይሆን የተወሰኑትን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ ዳኛ ሲሾም ጥንቃቄ የተሞላበት የአመራረጥ ሒደት (Voting Process) ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዳኛ እንደ ማንኛውም ሠራተኛ የሚነሳና የሚባረር አይደለም፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት ዳኛ እንደተፈለገ ሲባረርና ሲነሳ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አናደርገውም፡፡ የራሳችን የሆነ ውስጣዊ የአመራረጥ ሒደት (Internal Voting Process) አለን፡፡ ሙሰኛና በራሱ የማይተማመን ዳኛ ከእኛ ጋር አይቀጥልም፡፡ ይኼንን ደግሞ በዘዴና በጥንቃቄ እያጣራን ነው፡፡ በውጭ ሁሉም ዳኞች ሙሰኞች፣ የአቅም ብቃት እንደሌላቸውና መባረር እንዳለባቸው ይወራል፡፡ ነገር ግን ‹‹ማነው? ወይም ማነች? ስም ጥቀሱና በማስረጃ አስደግፋችሁ ንገሩን›› ሲባሉ የሚያቀርብ የለም፡፡ እኛ እንደ ምኞታችን ሁሉም ዳኞች ብቁ፣ ለሕዝብ፣ ለህሊናቸውና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ እንዲሆኑ ነው የምንፈልገው፡፡ ብቻችንን ለውጥ ስለማናመጣ ረዥም ጊዜ ያገለገሉ፣ ብቃት ያላቸውንና ለሕዝብ ታማኝ ናቸው የምንላቸውን ጠበቆችንና የሕግ ባለሙያዎችን ወደ ዳኝነት ለማምጣት ጠይቀናል፡፡ ግን ፈቃደኛ የሚሆን አላገኘንም፡፡ ይኼም ቢሆን አልፈርድባቸውም፡፡ ምክንያቱም ለፍርድ ቤት ዳኞች የሚከፈለው ደመወዝ በቂ ባለመሆኑ ያሉበትን ሥራና የሚያገኙትን ገቢ ማጣት አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ ያሉትን ዳኞች በአንድ ጊዜ ማባረር አይቻልም፡፡ እንኳን ዳኛ ለማባረር ቀርቶ አንድ ዳኛ ታሞ ሲቀር የሕዝቡ ቁጣና ጫጫታ አይቻልም፡፡ የዳኝነትና የደኅንነት ሥራ አንድ ዓይነት ነው፡፡ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ (Sensitive) ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሙስና የሚጠረጠር ዳኛ ደመወዙ ከተስተካከለ፣ የሥራ ነፃነቱ ከተከበረለትና ያለ ጣልቃ ገብነት ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ ከተደረገ ሊስተካከል ይችላል ይባላል፡፡ ዕውቀትና ክህሎት ግን በራስ ጥረት እንጂ በሌላ ነገር ሊመጣ አይችልም፡፡ የሰጡት ፍርድና ውሳኔ ምን እንደሚል ለመረዳት ጽሑፋቸው የማይነበብ፣ የቀረበውን ክስ የሚመጥን የሕግ አንቀጽ መጥቀስ የማይችሉ፣ ነገር ግን ባላቸው የፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ዳኛ ሆነው በመሾም በመሥራት ላይ የሚገኙ አንዳንድ ዳኞች እንዳሉ ስም በመጥቀስ ጭምር እየተነገረ በመሆኑ በሪፎርሙ ሊወሰድ የታሰበ ዕርምጃ አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ከፍተኛ የሆነ የብቃት ማነስ (Gross Incompetent) ያለበት ዳኛ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ሕገ መንግሥቱም ይፈቅድልናል፡፡ በአንቀጽ 79 (4ሀ) ድንጋጌ መሠረት ውሳኔ ሊተላለፍበት ይችላል፡፡ በአቅም ማነስ ብቻ ሳይሆን የዲሲፕሊን ጥፋት ፈጽሞ የተገኘም ዳኛ ከዳኝነት ይባረራል፡፡ ነገር ግን ሥልጠና በመስጠትና የአቅም ግንባታ እንዲያገኙ በማድረግ እንዲሻሻሉና ብቃት ያላቸው ዳኞች እንዲሆኑ ማድረግ ግን ተቀዳሚ ተግባራችን ነው፡፡ የዳኝነት ሥራ በቀጥታ ከሰው ጋር ፊት ለፊት የሚገናኝ ነው፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነትም ጠይቃል፡፡ በመሆኑም ዝም ብሎ የዳኞችን ችግር ብቻ መናገር ሳይሆን ዳኞችና ተቋሙም ያለባቸውን ችግር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች አሉባቸው፡፡ ይኼንን ግን የሚያስረዳ የለም፡፡ ሕዝቡ በውጭ ሆኖ ‹‹ዳኛ እንዲህ ነው›› ብሎ ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡ ምናልባት በተቋሙ ውስጥ ጥፋት የሚያጠፉት አሥር በመቶ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም ቁልፍ ቦታ ላይ ያሉና እንደፈለጉ ማድረግ የሚችሉ ናቸው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ግን አንገቱን ደፍቶ ሲሠራ ውሎ ሲሠራ የሚያድር ነው፡፡ ዳኞች ቀን ሲያከራክሩ ውለውና መዝገብ ተሸክመው ወደ ቤታቸው በመሄድ ሲሠሩ የሚያድሩ ናቸው፡፡ ይኼንን የሚያደርጉት የተመቸ ቤት እንኳን ሳይኖራቸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሕይወታቸውም ላይ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሚያዩት ከባድና የሰው ሕይወት ያለፈበት የወንጀል ጉዳይ ነው፡፡ የሞት ፍርድ ፈርደው በእግራቸው ከሕዝብ ጋር እየተጋፉ ነው የሚሄዱት፡፡ የዳኝነት ሥራ በተፈጥሮ ዝግ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ውስን ነው፡፡ አብዛኛው ሥራ በዝግ የሚሠራ በመሆኑ ኅብረተሰቡም ስለሚሠራው ነገር ስለማያውቅ ትኩረቱ ፍረጃ ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ደፍረው ስለሥራው ሁኔታ ለሕዝብ እንዲያደርሱ አልተደረገም፡፡ የከሳሽንና የተከሳሽን ፍላጎት ለማወቅ ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ሕግ ከመተርጎም ጀምሮ ብዙ ውስብስብ ሥራ ያለበት ሙያ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እንዲገነዘበው ማድረግ ተገቢ በመሆኑ በእሱም ላይ መሥራት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ዳኞች በችሎት አመራራቸውም ሆነ በችሎታቸው ብቃት ያላቸው ቢሆኑም፣ በውሳኔና ፍርድ አሰጣጣቸው ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ ችግር ይታይባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የፖለቲካ ታማኝና ታዛዥ በመሆናቸው ነው፡፡ አገሪቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መመራት ከጀመረች በኋላ፣ በተለይ ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው ሕግንና ሕግን ብቻ በመጠቀም ገለልተኛ ሆነው እንደሚሠሩ ቢነገርም፣ ቀድሞ ይሠሩበት የነበረው ፖለቲካዊ ዕይታቸው አሁንም እንዳልለቀቃቸውና ቀድመው ይሠሩበት በነበረው ሁኔታ መቀጠላቸው እየተነገረ ነው፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ ያው ኢሕአዴግ ስለሆነ፣ ሰው እንጂ የአሠራር ሲስተም ያው ነው እየተባለ ነው፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንግዲህ ከዳኞች ጋር ፊት ለፊት ተናጋግረናል፡፡ የምትሠሩት በሕጉ ነው፡፡ በሕግ ብቻ ከሠራን ማንም ጣልቃ አይገባብንም፣ ወደዚህ ኃላፊነትም የመጣነው በዚህ ላይ ተስማምተን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ችግር ካጋጠማችሁ ለእኔ አሳውቁኝ ብያቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ባይሆኑ፣ በአንዳንድ ዳኞች ቀድሞ ሲሠሩበት የነበረው አሠራር ሊለቃቸው አልቻለም የሚባል ነገር ካለ መጀመርያ እውነት መሆኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ወደድንም ጠላንም በሽግግር ውስጥ ነን፡፡ ብዙ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ጊዜ ኖሮኝ ድረ ገጾችና ሌሎች ነገሮች ላይ ማንበብ ባልችልም እሰማለሁ፡፡ በመሆኑም መረጃ የምናገኝበትን ቦታ ማስተዋልና መጠንቀቅ አለብን፡፡ እውነት አሁንም ቀድሞ ከነበሩበት የፖለቲካ ጫና ያልተላቀቁ ዳኞች መኖራቸውን በተገቢው ሁኔታ ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ነፃነት የማይሰማቸው ዳኞች ካሉ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ለዳኞች ሥልጠና መስጠት ጀምረናል፡፡ አንዱ የምንሰጠው ሥልጠና ‹‹የዳኝነት ነፃነት ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚል ነው፡፡ እንደ ተቋም፣ እንደ ግለሰብ ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ መፈጠር አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአመለካከት ልዩነቶች አሉ፡፡ ይኼም የአመለካከት ልዩነት በአብዛኛው የሚያጋጥመው ከጊዜ ቀጠሮ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ አንዳንዱ ዳኛ፣ ‹‹ፖሊስ ምርመራ ካላጠራና ዓቃቤ ሕግ ክስ ካልመሠረተ የእነሱን ሥራ መሥራት የለብኝም፤›› ብሎ ሥራውን ይለቃል፡፡ አንዳንዱ ዳኛ ደግሞ፣ ‹‹የፖሊሶቻችንን ብቃት እናውቀዋለን፡፡ የዓቃቤ ሕግ የመሥራት ፍላጎትና የጉዳዩንም ብዛት እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ መታገስ አለብን፤›› የሚልም አለ፡፡ በእርግጥ ተጠርጣሪም ሆነ ኅብረተሰቡ እንደሚለው በአንድ ጉዳይ ላይ በተሰጠ 14 የምርመራ ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ቢቀርብ ጥሩ ነበር፡፡ ይኼንን ማድረግ ስለማይቻል ተደጋጋሚ ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ጩኸት ይበዛል፡፡ ነገር ግን ‹‹ዳኛው ዝም ብሎ ጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠው በተፅዕኖ ነው? ወይስ በራሱ ውሳኔ ነው?›› የሚለውን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ ስለዚህ እነዚህና ሌሎች ችግሮችን በሥልጠና ለመቅረፍ እየሠራን ነው፡፡        

ሪፖርተር፡- በወንጀል ድርጊቶች ላይ ክስ የመመሥረት ሥልጣን የዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ ወንጀል ደግሞ በመንግሥት አካላት ወይም በግለሰቦች ይፈጸማል፡፡ በተለይ በመንግሥት አካላትና ተቋማት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ችላ ማለትና ማዳላት እንዳለ፣ ይኼ የሚሆነው ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ አማካሪ በመሆናቸው በአንድም ይሁን በሌላ የፖለቲካ ተፅዕኖ ስለሚያርፍበት ነው የሚሉ አሉ፡፡ በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ የተሰጠውን የአማካሪነት ሥልጣን ትቶ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መሥራት ካልቻለ የተሟላ ፍትሕ ማግኘት አይቻልም ይባላል፡፡ በሪፎርሙ በዚህ ላይ የምትሠሩት ነገር አለ?  

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼ በጣም ጥሩ ዕይታ ነው፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም አወቃቀር እንዴት እንደሆነና ምን እንደሚመስል ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የመንግሥት አማካሪ ስለመሆኑ አላሰብኩበትም፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሕዝቡን ወክሎ ነው የሚሠራው፡፡ ፖለቲካዊ ያለው ግንኙነት ግን መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም ነገር ለመወያየት በሩ ክፍት ስለሆነ ይኼም ከውይይት ውጪ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ተሞክሮው ምን ይመስላል? ምን ዓይነት ተፅዕኖ አለው? የሚለው መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ዕውነቱን ለመናገር በደንብ ስላላሰብኩበት ተገቢ ምላሽ ላልሰጥ እችላለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በከባድ የወንጀል ድርጊቶች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች በማረፊያ ቤት ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው እያለ፣ የምርመራ ሒደቱ ሳይጠናቀቅና ክስ ተመሥርቶ ጥፋተኛ መሆናቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ንፁህ ሆነው የመገመት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ጭምር የተደነገገ መብት ቢሆንም፣ የተለያዩ ዘጋቢ (Documentary) ፊልሞችን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ባላቸው የመገናኛ ብዙኃን በመልቀቅ በሕዝብ የማስፈረድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የሚቃወሙም፣ የሚደግፉም አሉ፡፡ እርስዎ ከየትኛው ወገን ነዎት?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎችን በሚመለከት በመገናኛ ብዙኃን የማቅረቡ ጉዳይን በሁለት መንገዶች መመልከት አለብን፡፡ ይኼ ያለፈው መንግሥት አሠራር ውርስ (ሌጋሲ) አለው፡፡ ቀሪ ምልክቶች አሉ፡፡ ይኼ የሕዝብ ጉዳይ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ዘጋቢ ፊልም መሠራቱን እኔም አልደግፍም፡፡ በዴሞክራት አገሮች ተመሳሳይ ጉዳይ የሕዝብ ነው በሚል በመገናኛ ብዙኃን ውይይት ይደረግበታል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብንወስድ በትራምፕ ላይ የተለያዩ ምርመራዎች ሲደረጉና ለሕዝብ ይፋ ሲሆኑ እናያለን፡፡     

ሪፖርተር፡- የተያዘው ጉዳይ የሕዝብ ከመሆኑ አንፃር በመገናኛ ብዙኃን መታየቱ ትክክል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ካለችበት የዴሞክራሲ ዕድገትና ሰዎች የፈለጉትን መረጃ አግኝተው የሚረዱበትን ሁኔታ ከአሜሪካና ከሌሎች ካደጉ አገሮች ጋር ማነፃፀሩ ተገቢ ነው ይላሉ? ተደብቆ ሲፈጸም የነበረን ድርጊት በአንድ ጊዜ ማሳየቱ፣ በሕዝቡ ላይ የሚፈጥረውን ስሜትና የሚወሰደው ዕርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ከግምት ውስጥ ማስገባቱ ጠቃሚ አይመስልዎትም?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ያደጉ አገሮችን ተሞክሮ ላነሳልህ የፈለግኩት በሕግ የተያዙ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ መለስ በራሳቸው ምርመራ የሚያገኙትን መረጃም በዝርዝር ያቀርባሉ ለማለት ነው፡፡ ነገር ግን በዶክመንተሪው ላይ ‹‹ያላግባብ ስሜን አንስቷል፣ ስሜን አጥፍቷል›› የሚል ካለ መክሰስ ይችላል፡፡ የሕዝብ ጉዳይ ስለሆነም ዝም ብሎ መያዝም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይኼንን ጉዳይ በሚመለከት በግልጽ ከዳኞች ጋር አንስተን ተነጋግረናል፡፡ የተጠርጣሪ ጠበቆች ወይም ራሳቸው ተጠርጣሪዎች ያላግባብ ስማቸው መነሳቱን በመጥቀስ አቤቱታ ካቀረቡ ውሳኔ እንዲሰጡበት ለዳኞች ሥልጣን ሰጥተናል፡፡ ወደፊት የሚዲያ ፖሊሲና ሕግ ይወጣል፡፡ እስካሁን ያለው የሚዲያ ሕግ ዳኞችን እንዳይናገሩ የሚያደርግ ነው፡፡ በሕግ የተያዘን ነገር በሚዲያ ማስተላለፍ ክልክል መሆኑን የሚያስጠነቀቅ ሕግ ነው ያለው፡፡ በራሱ የሚተማመንና ብቃት ያለው ዳኛ በሚዲያ ምንም ቢባል መሥራት ያለበት በሕግ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ዳኛ በሕዝባዊ አስተሳሰብ ሥር ከወደቀ ትክክለኛ ዳኝነት አይገኝም›› የሚለው አስተሳሰብ እንዳለ ሆኖ፣ በሕግ የሚሠሩ ዳኞችን ማብቃት አለብን፡፡ በሌላ በኩል የሕዝቡን መረጃ የማግኘት መብት እየገደብን በመሆኑ እያመጣጠንን መሄድ አለብን፡፡    

ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ ዘጋቢ ፊልሞችን ከፍርድ ውሳኔ ቀድሞ ማሳየት፣ በተጠርጣሪው ወይም ተከሳሹ ላይ ፍርድ ሊያሰጥ ይችላል፡፡ ዳኞች ሕጉን ብቻ ተከትለውና አድልኦ ሳያደርጉ የሚሰጡት ውሳኔ ሕዝቡ እንደጠበቀው ሆኖ ባያገኘው ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚሉ ስላሉ ያለዎት ምላሽ ምንድነው? 

ወ/ሮ መዓዛ፡- ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ትክክል ነው፡፡ እኔም እስማማለሁ፡፡ መረጃ ወደ ሕዝቡ ከመድረሱ በፊት እንዴትና በምን መንገድ መድረስ እንዳለበት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ያልጠበቅናቸው ችግሮች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡     

ሪፖርተር፡- በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥር የተቋቋመው የሕግ ማሻሻያ ብሔራዊ ምክር ቤት ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተዛውሯል፡፡ ሌሎችም ልምድና ዕውቀት ያላቸው ግለሰቦች ተመርጠው እየሠሩ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን የተመረጡበት ሒደት ትክክል እንዳልሆነና በሕግ መጠየቅ የነበረባቸው ግለሰቦች ጭምር ተመርጠው የተቀላቀሉ ስላሉ፣ ሪፎርሙን እንዳይሳካ እንቅፋት ይሆናሉ እየተባለ ስለሆነ ስላለው ሁኔታ ቢያስረዱን?  

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንዳልከው 18 ሰዎች ናቸው፡፡ በዳኝነት፣ በአስተዳደርና በጥብቅና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ ከእነሱ ውስጥ ምናልባት አንድ ሁለቱ ላይ የተለያዩ ነገሮች ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ግን ስለዚህ ጉዳይ አስቤበታለሁ፡፡ ኅብረተሰባችን ክፍፍል ላይ ያተኩራል፡፡ ግን ያ ሰው ወንጀል እስካልሠራና ወንጀለኛ እስካልሆነ ድረስ መታሰብ ያለበት ስለሚያበረክተው አስተዋጽኦ መሆን አለበት፡፡ ልምዱንና ለሪፎርሙ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ነው የምናየው፡፡ ‹‹እከሌማ እንደዚህ ነው፡፡ እሱማ እንዲህ ነው . . . ›› እያልንና እየከፋፈልን ከሄድን ምንጊዜም ወደ ዕርቅ ልንመጣ አንችልም፡፡ እየተከፋፈልን ከቀጠልን የማኅበረሰብ ስምምነት ሊመጣ አይችልም፡፡    

ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የተቋቋመው የሕገ መንግሥት ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችን መርምሮ ትርጉም የሚያስፈልገው ሆኖ ሲገኝ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ጉባዔው ሌሎች ጉዳዮችንም በመቀበል፣ ከፍርድ ቤቶች ያልተናነሱ መዝገቦችን እያስተናገደ ስለመሆኑ ምን ይላሉ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት ጉባዔው የሚመራበት ፕሮሲጀር ስለሌለው እንደ አዲስ እየሠራን ነው፡፡ በፌዴሬሽን ሥር ፍርድ ቤት መቋቋም እንዳለበት ወይም የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት መቋቋም እንዳለበት፣ ሕገ መንግሥቱ ሲረቅቅ ጭምር የተነሳ ጥያቄ ነበር፡፡ ነገር ግን በአብላጫ ድምፅ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ይቋቋም ተብሎ ተቋቋመ፡፡ በወቅቱ ተነስቶ የነበረው የመከራከሪያ ሐሳብ ጉባዔው መቋቋሙ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ባይኖረውም ‹የሥልጣን ክፍፍል ያጣርሳል› የሚል ነበር፡፡ በሌሎች አገሮች የለም፡፡ አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤቶች (በውጭው ዓለም) ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን አላቸው፡፡ በእኛ አገር አሁን ባይደረግም ወደፊት ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበት ሒደት ተከትሎ የሚታይ ነው፡፡ ለጊዜው ያለው ግን ጉባዔው ነው፡፡ የእኛ ፍልስፍና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ ሐሳቦችና አልፎ አልፎ አንገብጋቢ ጉዳዮች ሲመጡ ብቻ እንዲያይ ነበር፡፡ ነገር ግን አንተ እንዳልከው ትንንሽ ጉዳዮችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮች ከሰበር ወደ ጉባዔው እየሄዱ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- በሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ላይ እየቀረበ ያለው ጥያቄ የጉዳዮች መብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በጉባዔው ውስጥ የተመደቡ ሰዎች ስብጥርም ጭምር ነው፡፡ በጥብቅና ሥራ የተሠማሩ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ድርጅት አባላት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በመሆናቸው ዜጎች ወደዚያ መሄዳቸው ጥቅም የለውም፡፡ ምክንያቱም በሰበር ውሳኔ የሰጠ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢ በሆነበትና ከዳኛ ጋር ፍርድ ቤት ሲከራከር የሚውል ጠበቃ የሚቀርቡለትን ጉዳዮች ገለልተኛ ሆኖ ያጣራል የሚል ግምት መውሰድ ተገቢ አይሆንም በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አባላቱ 11 ናቸው፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ በመሆኑ፣ በሚቀርበው መዝገብ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል ግምት የለኝም፡፡ አባላቱ ጠንካራ ከሆኑ፣ ጉዳዩን አጠንተው ከመጡና ብቃት ካላቸው በሰብሳቢው ብቻ ይወዛወዛሉ ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የሚመጣው ጉዳይ ከፍርድ ቤት አይደለም፡፡ ከማንኛውም አቅጣጫ ይመጣል፣ መምጣትም አለበት፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል የሥልጣን ጉዳዮችን በሚመለከት፣ በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መካከል በሚነሳ የሥልጣን ግጭት ይመጣሉ፡፡ በመሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሰብሳቢ ቢሆን ችግር የለውም፡፡ በእኛ አገር ስላልሆነ ነው እንጂ ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥራ መምጣት የነበረበት ወደ ፍርድ ቤት ነው፡፡ አምነህ ካስቀመጥከውና እሱም ታማኝ ከሆነ ፍርድ ቤት የፍትሕ ሥርዓቱ ቁንጮ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንዳሉት ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ መሄድ ያለባቸው ጉዳዮች ከተለያዩ አቅጣጫ የሚመጡ መሆን የነበረባቸው ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን በሰበር ችሎት የመጨረሻ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች እንደሚበዙ ይገለጻል፡፡ ይኼ የሚሆነውም በአንዳንድ ብቃት በሌላቸው ዳኞችና አንዳንዶቹ ደግሞ በጥቅም በመደለል ሆን ብለው ያልተገባ ትርጉም በሚሰጡ ዳኞች የተበላሹ ውሳኔዎች በመሰጠታቸው መሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የዳኞችን ብልሹ አሠራር ለዳኞች አስተዳደር በመግለጽ በተጎጂዎች ይግባኝ ቢቀርብም፣ የጉባዔው ሰብሳቢ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት በመሆኑና የሚያቀርቡት አቤቱታ ውጤት እንደማያመጣ ተስፋ በመቁረጥ ወደ አጣሪ ጉባዔው እንደሚሄዱም ይታወቃል፡፡    

ወ/ሮ መዓዛ፡- በጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ ዳኞች 49 ናቸው፡፡ ጉዳዩ ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ መመጣጠን አልቻለም፡፡ ብቃትን በሚመለክት ሁሉም ዳኞች ብቃት የላቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ‹‹ችሎታ ያለው ማነው? የሌለውስ ማነው? በንፅህናና በተጠያቂነት ስሜት የሚሠራው ማነው? ሥልጣኑን ተገን አድርጎ የሚሠራውስ?›› የሚለውን በመረጃ ላይ ተመሥርተን ነው መነጋገር ያልብን፡፡ በአጠቃላይ እንደ አገር የአቅም ችግር አለ፡፡ አቅም ያላቸው ደግሞ ዕድል አላገኙም፡፡ ስለዚህ በኔትወርክ ይሁን፣ በፖለቲካ ወይም በተለያየ መንገድ እንደ ሌላው ተቋም ሁሉ ጥቂት ሰዎች መጥተው ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ በሒደት እየተስተካከለ የሚሄድ ነው፡፡ ነገር ግን በፍጥነት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ በሒደትም እየተስተካከለ ይሄዳል፡፡ ታማኝ የሆኑና ብቃት፣ ክህሎትና ልምድ ያላቸው ሰዎች እንዲመጡ ለማድረግ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ የለም፡፡ ይኼ በመሆኑ ነገ ጠዋት የሚፈለገው የፍትሕ ደረጃ ላይ አደርሳለሁ ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ምክንያቱም ችግሮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሁል ጊዜ ችግር እያወራን አንቀጥልም፡፡ በአጭር ጊዜና በረዥም ጊዜ የምንወስደው ዕርምጃ አለ፡፡ ሌላው መንግሥትም መመልከት ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ዳኞችን የሚያበረታታ ነገር ማድረግ አለበት፡፡       

ሪፖርተር፡- ሰበር ሰሚ ችሎት የሚያየው መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመባቸውን የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ችሎቱ መሠረታዊ የሕግ ስህተቶችን ከማየት ባለፈ በፍሬ ነገሮች ላይ አከራክሮ እስከ መወሰን ደርሷል፡፡ ይኼ ደግሞ ትክክል እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ የሰበር ችሎት ዳኞች ደግሞ የሚሰጡት ምላሽ በአስተዳደር ሕግ መታረም የሚገባቸው ውሳኔዎች ቢቀርቡለትም፣ አገሪቱ የአስተዳደር ሕግ ስለሌላት ጠቅሶ የሚያርምበት ሕግ ስለሌለውና ዜጎች መብታቸውን ማጣት ስለሌለባቸው፣ ራሱ ባያከራክርም የሥር ፍርድ ቤቶች እንደገና አከራክረው ውሳኔ እንዲሰጡ ጭብጦችን በማውጣት መዝገቦችን እንደሚመልሱ ይናገራሉ፡፡ ትክክሉ የትኛው ነው?   

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼ ማለትም ሕጉ አለመኖሩ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ሕዝቡ ግን የሕጉን ሥርዓት እስከ መጨረሻው መጠቀሙ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቅሬታውና አቤቱታው በዝቷል፡፡ ከክልል እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ ይመጣል፡፡ ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት መሠረታዊ የሕግ ስህተትን ማረም ስንመጣ፣ አንዱ ችግር ሕጉ ትርጉም አልተሰጠበትም፡፡ ‹‹የሕግ ጥሰት ምንድነው? መሠረታዊ የሕግ ጥሰትስ ምንድነው?›› የሚለው በግልጽ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ትርጉሙ በግልጽ ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ሥራውን ሊያቀለው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በሪፎርሙ መሻሻልና መለወጥ ስላለባቸው ሕጎች በጥናት እየሠራን ነው፡፡ እስከዚያው ግን የሰበር መመርያ እየተዘጋጀ ነው፡፡ የአሠራር መመርያ ነው፡፡ በዳኞች ሴሚናር ላይ ከተወያየን በኋላ ባለድርሻ አካላትን አወያይተን እናፀድቃለን፡፡ አንዱና ዋነኛው ክፍል ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት ምንድነው?›› የሚል ነው፡፡ ፍሬ ነገር የሆነውን ክርክር ትተን የሰበር ችሎት ሥልጣን/ሥራ ወደሆነው ማዘንበል የምንችልበትን አሠራር መመርያው ይመልሳል የሚል እምነት አለን፡፡ አሁን የፍሬ ነገሩና የሕግ ስህተቱም ተደባልቆ ስለሚመጣ ሬጂስትራሩ የቀረበለትን አቤቱታ መክፈት እንጂ የማየት ሥልጣን የለውም፡፡ በመሆኑም ጉዳዮቹ የግድ ወደ ዳኛው ይሄዳሉ፡፡ ዳኛው ደግሞ የሚለየው መርምሮ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ጊዜ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም ጉዳዮቹ ተጣርተው የሚቀርቡበትና ዳኞቹም ጉዳዮችን ረጋ ብለውና አጣርተው እንዲሠሩ የሚያደርጋቸው መመርያ እየተሠራ ነው፡፡           

ሪፖርተር፡- እርስዎ ቀደም ብለው እንዳነሱት በሰበር የሚሠሩ ዳኞች ባለመነጋገራቸውና ባለመወያየታቸው፣ በተመሳሳይ አቤቱታዎች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች ተሰጥተዋል፡፡ የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ደግሞ በሥር ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡ ተመሳሳይ ጉዳዮች አስገዳጅነት ስላላቸው የመዝገቦችን ብዛት መቀነስ ያስችላሉ፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ሰበር የሰጣቸው ውሳኔዎች የተለያዩ በመሆናቸው፣ የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎቹን በመተው የራሳቸውን ውሳኔ ስለሚሰጡ ወደ ሰበር የሚመጡ ጉዳዮች እየጨመሩ መሄዳቸው እየተገለጸ ነው፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ደግሞ የሥነ ሕግን  (Jurisprudence) ለማሳደግ ውሳኔዎች በሰበር ችሎት ውስጥ ታግደው መቆም የለባቸውም ይላሉ፡፡ መሆን ያለበት የትኛው ነው?    

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼ ከመዝገቦች ብዛት የተነሳ የተለያዩ ዳኞች የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊሰጡ ችላሉ፡፡ እነዚህን መዝገቦች እያስለቀምኩ ነው፡፡ በጣም ብዙ አይመስሉኝም፡፡ ነገር ግን አጋጥሟል፡፡ ይኼ መሆን የለበትም፡፡ አንድ ጉዳይ አንድ ጊዜ ውሳኔ ካገኘ በኋላ፣ ተመሳሳይ ጉዳይ ሲያጋጥም የዚያ ውሳኔ እየተጠቀሰ በድጋሚ ውሳኔ እንዳይሰጥ መደረግ አለበት፡፡ ይኼ ነገር ደግሞ በመመርያ የሚሠራ ነው፡፡ መታረም ያለበት ጉዳይ ስለሆነ እየሠራን ነው፡፡ በሌላ በኩል ሰበር ችሎት አንድ ጊዜ የሰጠው የሕግ ትርጉም አይለወጥም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ሥነ ሥርዓት (Procedure) ተቀምጧል፡፡ ያንን ትርጉም ለመለወጥ ከተፈለገ፣ የአምስት ዳኞች ውሳኔ በሰባት ዳኞች ታይቶ ሊለወጥ ይችላል፡፡ ይኼ እስካልሆነ ድረስ ግን በሰበር ችሎት የተሰጠ አስገዳጅ ትርጉም ሊሠራበት ይገባል፡፡ ነገር ግን ሥነ ሕጉን (Jurisprudence) ለማሳደግ፣ የሕግ ትርጉም በየጊዜው እየተሻሻለና እያደገ ሊሄድ ስለሚችል ቀደም ብሎ በአምስት ዳኞች የተሰጠው ትርጉም በሰባት ዳኞች እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ ሕዝቡ በፍርድ ቤት አንዱ የሚማረርበት ተገማች አልሆነም የሚል ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- የሰበር ውሳኔን በጠቅላላ የአገሪቱ ፍርድ ቤቶች ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኞቹ ክልሎች ውሳኔውን ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም ይባላል፡፡ በፌዴራል ደረጃም አፈጻጸም ላይ ተቀባይነት እያጣ ነው ይባላል፡፡ ከማስፈጸም አንፃር ሊወሰድ የታሰበ ነገር አለ?  

ወ/ሮ መዓዛ፡- እሱንም በሚመለከት አንድ መረጃ አግኝቼ እንዴት እንደምንሄድበት እያሰብንበት ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል አንድ ጉዳይ የክልሉ ሰበር ችሎት ድረስ ሄዶ ውሳኔ ካገኘ እዚያው ማብቃት እንዳለበት የሚደነግግ ሕግ መውጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ኅብረተሰቡ ደግሞ እየተጠቀመ ያለው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 80 (ሀ)፣ ‹‹ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ካለበት የማረም ሥልጣን አለው›› የሚለውን ነው፡፡ ስለዚህ ይኼንን መመልከት አለብን፡፡ ምንም እንኳን የሕዝቡ መብት መጣበብ ባይኖርበትም፣ ትንሹም ትልቁም እስከ ሰበር መምጣቱ ችግር እያስከተለ ነው፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ ስለፈቀደ መምጣት ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ ሌላ ድንጋጌ እስካልተሰጠ ድረስ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ መጣስ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የጉዳዩ ዓይነት መለየት አለበት፡፡ ሙግት አንድ ቦታ ማብቃት አለበት፡፡ ውጤቱ አንዳንድ ጊዜ መራራ ቢሆንም ሕዝቡ መቀበል አለበት፡፡ ሌሎች መፍትሔ ማግኛ መንገዶችንም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡    

ሪፖርተር፡- ዳኝነት ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ ነው፡፡ በመሆኑም በተቋሙ የሚመደቡ ዳኞችም ሆኑ አጠቃላይ የተቋሙ አሠራር በማንኛውም ነገር ከሁሉም የተሻለ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ነገር ግን የሚመደቡ ዳኞች ደመወዝ ጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ለመንግሥት ያልተሰጠ በሰው ሕይወት ላይ የመፍረድ ሥልጣን በተሰጠው ተቋም ውስጥ ተመድቦ የሚሠራ ዳኛ፣ የሞት ፍርድ ሰጥቶ ወደ ቤቱ የሚሄደው ከሕዝብ ጋር ተጋፍቶ በእግሩና በሕዝብ ትራንስፖርት ነው ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት ዳኞች ገለልተኛ፣ ነፃና ተዓማኒ ሆነው እንዳይሠሩ የሚገደዱበት ሁኔታ ስለሚኖር የፍትሕ ሥርዓቱ የሚበላሽበት ሁኔታ እንደሚፈጠርና ተፈጥሮም እየታየ መሆኑም እየተገለጸ ስለሆነ በሪፎርሙ ምን የታሰበ ነገር አለ?   

ወ/ሮ መዓዛ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በፍርድ ቤት ያለውን ችግር እንጂ፣ ዳኞች በምን ሁኔታ እንደሚሠሩ ግንዛቤ ያለው የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔም ያለባቸውን ችግር ይበልጥ የተረዳሁት እዚህ ከመጣሁ ነው፡፡ በሥልጣን አከፋፈል ረገድ ሦስተኛው የመንግሥት አካል ነው፡፡ ከዚያ አንፃር የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ደረጃው ከአንድ ሚኒስቴር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ተረስቶ ይሁን ወይም ሆን ተብሎ የተተወ ሴክተር ነው፡፡ ለምሳሌ እኔን ብንወስድ የፕሮቶኮል ሰዎች በሚገባኝ ቦታ ለማስቀመጥ ሲጨነቁ አያለሁ፡፡ እኔ የፕሮቶኮልና ያንን ያህል ከፍ ያለ ነገር የምፈልግ ሰው ባልሆንም፣ ሥርዓቱንና ቦታውን ማስከበር ተገቢ በመሆኑ እንዲስተካከል ጥያቄ እያቀረብኩ ነው፡፡ የዳኞች የዕለት ተዕለት ኑሮ ደግሞ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ መዝገብ ይዘው እጅግ በጣም ርቀት ከሕዝብ ጋር እየተጋፉ ይሄዳሉ፡፡ ሥራው በቢሮ የሚያልቅ ባለመሆኑ የሰው መዝገብ ተሸክመው በእግር ይሄዳሉ፡፡ ለዳኞች የተሟላ መኖሪያ ቤት፣ መጓጓዣና ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ቢሆንም የላቸውም፡፡ አሁን አሁን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች የተሰጠ መኪና ቢኖርም ደረጃው የወረደና በየመንገዱ የሚቆም ነው፡፡ የአገሪቱን አቅም ባውቅም በዚህ ጉዳይ ግን ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ለማስተካከል እሠራለሁ፡፡ ፍትሕ በርካሽ ሊገኝ የሚችል ነገር አይደለም፡፡ አንድ ምሳሌ ባነሳ፣ አንድ ዳኛ ለሥራ ጉዳይ ወደ እኔ ቢሮ አስጠርቼው ሲመጣ በጣም ደክሞት ደረሰ፡፡ ምን ሆኖ እንደሆነ ስጠይቀው የመጣው በእግሩ በመሆኑ ደክሞት እንደሆነ ነገረኝ፡፡ በመቀጠልም ልጆቹ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ከጓደኞቻቸው ጋር ስለቤተሰቦቻቸው ሲጠያየቁ፣ ‹አባታችን ዳኛ ነው› ሲሉ የሌሎቹ ልጆች ጥያቄ፣ ‹ስንት መኪና አላችሁ?› ነው አለኝ፡፡ ይኼ ምን ያህል ደረጃውን ያልጠበቀ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንደ ሌላቸው ማሳያ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ግን ይኼንን አልተገነዘቡላቸውም፡፡ ግን ለማሻሻል እየሠራንና እየጣርን ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- ስለፍርድ ቤቶች ወይም ዳኞች ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ ዳኞች የፍትሕ አጋዥ የሚባሉትን ጠበቆችና ዓቃቤ ሕግን በእኩል ዓይን ዓያዩም፡፡ ለዓቃቤ ሕግ ያዳላሉ፡፡ በተለይ አንዳንድ ዳኞች ጠበቃ በችሎት ውስጥ ለማየትም አይፈልጉም፡፡ ዳኞች ገለልተኛ ሆነው ሁሉንም ተከራካሪ አካል እኩል ማስተናገድ አለባቸው ስለሚባል፣ በሪፎርሙ በዚህ ላይ እየተሠራ ያለ ነገር አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡-  እውነት ነው፡፡ ጠበቆችን ሰብስቤ ባናገርኩበት ውቅት ተነስቷል፡፡ እኩል እንደማይታዩ፣ ዳኞች መጀመርያ ዓቃቤ ሕጎችን በቢሮአቸው አስጠርተው ከተነጋገሩ በኋላ እንደሚሰየሙ፣ ዓቃቤ ሕግ ካልቀረበ አንዳንድ ችሎቶች እንደማይሰሙና በችሎት ሲሰየሙ ሰነዶችን የሚያስቀምጡበት ጠረጴዛ እንኳን እንደሚያጡ ተናግረዋል፡፡ ያንኑ ያህል በጉዳዩ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሪፎርሙ ብዙ ነገር ይሻሻላል፡፡ በዚህ ላይ ብዙ ነገር እየተሠራ ነው፡፡ አንድ አስገራሚና አሳዛኝ ነገር ልንገርህ፡፡ በፍርድ ቤቶች ብዙ ወንበሮች እግራቸው ተቆርጦ ተቀምጠዋል፡፡ ‹‹ይኼ ምንድነው?›› ተብሎ ስጠይቅ ‹‹በቢፒአር ጥናት ዳኛ፣ ጠበቃና ፖሊስ እኩል ናቸው፡፡ አንዱ ከአንዱ በልጦ መቀመጥ የለበትም፤›› ተብሎ መቆረጡን ነገሩኝ፡፡ ይኼንን ያህል ደረጃ የተደረሰበት ሁኔታ ነበር፡፡ አንተም የተገኘህበት የክልሎችና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጉባዔ ላይ በአንድ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት፣ ‹‹የክልል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሰብሳቢ የክልሉ ፕሬዚዳንት ነበሩ›› በማለት የተገለጸበት ሁኔታን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በሁሉም ቦታ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖው ተመሳሳይ ነው፡፡ የእሳቸውን ለየት ያደረገው በገሀድ ፊት ለፊት መሆኑ  ነው፡፡ ሌላው አንድ ልናውቅና ዕውቅናም ልንሰጣቸው የሚገቡ ዳኞች አሉ፡፡ ለዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት ታግለው ተሟግተው ወደ ሥራ የተመለሱ አሉ፡፡ አንዳንዶቹም የሥርዓቱ ተገዥ ባለመሆናቸው የተለያዩ ምክንያቶች እየተፈለገባቸው ከዳኝነት ሥራቸው የተባረሩ፣ እንዲለቁ በጎን ማስፈራሪያ እየደረሳቸው የለቀቁና በዚህ ሁኔታም አልሠራም በማለት በፈቃዳቸው የለቀቁ ምሥጉን ዳኞች ኡሉ፡፡ ይኼንንም አብሮ ማየት ተገቢ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 ለዓቃቤ ሕግ የተለያዩ ሥልጣኖችን ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስን ምርመራ የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመምራት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ በሕግም ባይሆን ደግሞ በቢፒአር ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ በምርመራ ወቅት አብረው እንዲሠሩ ተደርገው እየሠሩ ነው፡፡ አሁን አሁን ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ሥልጣን እንደተሰጠው ለፍርድ ቤት በመግለጽ፣ በጊዜ ቀጠሮ በሚነሱ ክርክሮች ላይ እንዲሳተፍ ጠይቆና ተፈቅዶለት እየተከራከረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ተከራካሪ የሕግ ባለሙያዎች ዓቃቤ ሕግ በመርማሪ ፖሊስ ሥራ ላይ ጣልቃ ገብቶ የመከራከር ሥልጣን የለውም፡፡ የአዋጁ ዓላማ እንደዚያ አይደለም ይላሉ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ደግሞ የፖሊስ ሥራ ምንድነው በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ ትክክለኛው አካሄድ የትኛው ነው? 

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ይኼ አሠራር የመጣው ከቢፒአር ነው፡፡ የፖሊስ ሥራ ቴክኒካዊ የሆነ ምርመራ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ የፖሊስ ምርመራ ውጤትን ቅርፅ ማስያዝና ክስ መመሥረት ነው፡፡ ተቀራርበው ቢሠሩ ነገሮች ከሚንዛዙ የተፋጠነ ፍትሕ ለመስጠት ያስችላል ተብሎ ነበር በቢፒአር ተቀርፆ ወደ ሥራ የተገባው፡፡ ያ አሠራር በአዋጅ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ነገር ግን የሕግ አሠራር ሒደትን የሚያደናቅፍ ከሆነ ለክርክር ቀርቦ የማይስተካከልበት ምክንያት የለም፡፡ በዚህ ላይ ሐሳብ ያላቸው ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች በነገሩ ላይ ትኩረት አድርገው ካቀረቡት በመድረክ ጭምር ውይይት ሊደረግበት ይችላል፡፡    

ሪፖርተር፡- የዋስትና መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ በልዩ ሁኔታዎች ከሚከለከል በስተቀር ዝም ተብሎ የዋስትና መብት አይነፈግም፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቶች አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ዋስትና ሲከለክሉ ይስተዋላል፡፡ አንደኛው መርማሪ ፖሊስ የተጠርጣሪን ዋስትና በማስከልከል ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ፣ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ያስረክባል፡፡ ዓቀቤ ሕግ በተረከበው የምርመራ መዝገብ ላይ ክስ ለመመሥረት ወይም ውድቅ ለማድረግ 15 ቀናት እንዲፈቀድለት ሲጠይቅ፣ በሚመሠርተው ክስ ላይ የሚጠቅሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና ሊከለክል ስለሚችል፣ ተጠርጣሪው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ ብሎ ያመለክታል፡፡ ጠበቆች ደግሞ ባልተመሠረተ ክስ በይሆናል የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ሊጣስ አይገባም ብለው ይከራከራሉ፡፡ መሆን ያለበት ምንድነው?   

ወ/ሮ መዓዛ፡- እነዚህ ቴክኒካዊ ነገሮች ናቸው፡፡ የዳኞችም ትርጉም አሰጣጥ ሒደት የተለያየ በመሆኑ ይኼንን በደንብ ማየት ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ ነው ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ  መብት ነው፡፡ የሚከለከልበት ልዩ ልዩ ምክንያቶችም በሕጉ ተቀምጠዋል፡፡ አሁን እየተሠራ ያለበትን ሁኔታ በደንብ መመልከት አስፈላጊ ስለሚሆን እናየዋለን፡፡     

ሪፖርተር፡- ሌላው በርካቶችን እያበሳጨ ያለውና ሆን ተብሎ የዜጎችን የዋስትና መብት ለመግፈፍ የተሰጠ ነው የሚባል የሰበር ውሳኔ አለ፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ከሁለት በላይ ተደራራቢ ክሶች በአንድ መዝገብ ከቀረቡበት የተጠቀሰበት ሕግ እንኳን ዋስትና ባይከለክልም፣ ዋስትና እንደማይፈቀድለት የተሰጠ አስገዳጅ ውሳኔ አለ፡፡ ያ ውሳኔ እየተጠቀሰ የዜጎች መብት እየተጣሰ ስለመሆኑ ያውቃሉ?  

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼንን ዛሬውኑ ነው የማየው (ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም.)፡፡ በእውነት ያነሳህልኝ ጥያቄዎች ጥሩ በመሆናቸው የምከታተላቸው ናቸው፡፡ አዲስ በመሆኔ እያንዳንዱን ሁኔታ ገና በመረዳት ላይ በመሆኔ እየተስተካከሉ እንዲሄዱ አደርጋሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊት ሊያስጠይቀው የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን አስቀድሞ መመርመርና ማወቅ ሕጋዊ ግዴታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አገሪቱን መምራት እንደጀመሩ፣ ‹‹አንድም ሰው የተጠረጠረበት ወንጀል ሳይረጋገጥ አይታሰርም›› ነበር ያሉት፡፡ ነገር ግን ይህ ሲተገበር አይታይም፡፡ ተጠርጣሪዎች ሳይያዙ አምስት ወራትና ከዚያ በላይ ምርመራ ተደርጎ መጠናቀቁ ለሕዝብ ይፋ የተደረገ ጉዳይ፣ ተጠርጣሪዎች ከተያዙ በኋላም ከሦስት ወራት በላይ እየወሰደ ነው፡፡ ይህ አሠራር ከዜጎች የተፋጠነ ፍትሕ ከማግኘት አንፃር እንዴት ይታያል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እንደነገርኩህ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለ፡፡ ነገር ግን ቀደም ባለው ጊዜ በነበሩባቸው የተለያዩ ተፅዕኖዎች ዳኞቹ በተለያየ ምክንያት ቀጠሮዎችን ያራዝሙ ነበር፡፡ አሁን እየሠሩ ያሉት ዳኞች ግን ቀጠሮ የሚያራዝሙት በራሳቸው ችግር ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የለባቸውም፡፡ አሁን እኔ በኃላፊነት ላይ ካለሁበት ጊዜ ጀምሮ አስፈጻሚው አካል ለዳኞች ደውሎ በመዝገቦች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያደርግበት አሠራር የለም፡፡ በአሠራራችን ዳኞች ካላቸው ቅልጥፍናና ለነገሮች ትኩረት ሰጥቶ ከማፋጠን አኳያ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ከችሎታም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ክርክሩ በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ አይችልም፡፡ አሁን እየሠራን ያለነው በተጠርጣሪዎችና በተከሳሾች ላይ ችግር ሳይደርስ ፍትሕ የሚያገኙበት አሠራር ለመዘርጋት ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ፍትሕና መድረክ ዛሬውኑ አይገኝም፡፡ ሒደት ነውና ጊዜ ይወስዳል፡፡ የተነሱትን ነጥቦች ዕውቅና ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ እያሻሻልን እንሄዳለን የሚል ሙሉ እምነትም አለኝ፡፡ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጎችም ላይ እየተሠራ ስለሆነ በቅርቡ መፍትሔ የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የፍትሕ አካላት ማለትም ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ እንዲሁም የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በጋራ በመሆን የሚሠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህ አሠራር ወይም ጥምረት ሕጋዊ መሠረት የለውም፡፡ አንዱ ሌላውን የመቆጣጠር ሥልጣን ያሳጣል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ በፖሊስ ጣቢያዎችና በማረሚያ ቤቶች በሚገኙ ዜጎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ነገር መቀጠል የለበትም የሚሉ ወገኖች ስላሉ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የሚገርምህ ይህ ጥያቄ ለእኔም ተነስቶልኝ ነበር፡፡ እውነት ነው፡፡ በዓብይ ኮሚቴ ደረጃ ተቋቁሞ በወር አንድ ጊዜ እንገናኛለን፡፡ ለሕዝቡ ተገቢውን ፍትሕ ለማድረስ አምስቱ ተቋማት ባለድርሻ ናቸው፡፡ ሙያዊ ነፃነታቸው እንዳለ ሆኖ በጋራ ጉዳያቸው ላይ ደግሞ እየተገናኙ ይወያያሉ፡፡ ነገር ግን ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዱ በሌላው ላይ ተፅዕኖ እንደነበረው ስለሚታወቅ፣ ኅብረተሰቡ አሁንም በዚያው የቀጠለ ሊመስለው ይችላል፡፡ የምንወያየው ግን የፍርድ ቤትን ነፃነት በሚነካ ጉዳይ ላይ ሳይሆን፣ ፍትሕን በሚያጠናክር ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ምርመራ የሚፋጠንበት፣ ክስ የሚመሠረትበትና ታራሚዎች በአግባቡ የሚያዙበት ሁኔታ ላይ ነው የምንወያየው፡፡ ሪፎርሙ ላይ ለጋሽ ድርጅቶች ሊረዱን የሚፈልጉት በተናጠል ሳይሆን በጋራ ስለሆነም ነው፡፡ በሚያገናኙን ሥራዎች ላይ በምን ሁኔታ ብንሠራ ሥራዎች የተቀላጠፉና ምንም ዓይነት እንከን ሳያጋጥሟቸው መከናወን እንደሚችሉ ፍኖተ ካርታ ለማስቀመጥ እንጂ ሌላ ነገር የለም፡፡ ይኼ የሚሆነውም የኅብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እስከሆነ ድረስ መተባበር ባለብን ነገር ላይ ተባብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራውን በፈለገው ፍጥነትና መንገድ እንዳይሠራ ፍርድ ቤቶች እንቅፋት እንደሆኑበት በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል፡፡ ይኼም የሚሆነው ለልማት ሲባል የከተማው ነዋሪዎች ከሚኖሩበት ቦታ እንዲነሱ ሲጠየቁ፣ ‹‹ሁከት ይወገድልኝ›› በማለት የፍርድ ቤት ዕግድ በማቅረብ ሥራውን እንደሚያስተጓጉሉበት ነው፡፡ በቅርቡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እና ካቢኔያቸው ወደ እርስዎ ቢሮ መጥተው ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይታችሁ ከተነሱት ችግሮች ጋር በተገናኘ ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ትክክል ነው፡፡ ከንቲባውና ካቢኔያቸው ወደ እኔ ቢሮ መጥተው ነበር፡፡ አንደኛ ለመተዋወቅ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አንተ እንዳነሳኸው ‹‹ሥራዎችን በፈለግነው መንገድ ለማስኬድ ችግሮች እየተፈጠረብን ነው›› ለማለት ነው፡፡ የሁለቱንም ችግር እረዳዋለሁ፡፡ ሰዎች መብታቸውን የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልማት መቀጠል አለበት፡፡ መሆን ያለበት ግን ፍርድ ቤቶች የሚቀርብላቸውን አቤቱታዎች ተመልክተው አግደው ማቆየት ሳይሆን፣ ቶሎ ቶሎ ውሳኔ መስጠት አለባቸው፡፡ በተለይ ጊዜ የማይሰጡና ከፍተኛ የልማት ሥራዎች ከሆኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ማድረግ እንጂ፣ ዜጎች ለምን ስለመብታቸው ጥያቄ አነሱ ማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄያቸው ግን ትኩረት የሚሰጠውና እኛም በሪፎርሙ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየሠራንበት ነው፣ የተነጋገርነውም ይኼንን ነበር፡፡      

ሪፖርተር፡- እርስዎ ተሹመው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ከሌሎች አስፈጻሚ አካላት የገጠመዎት ችግር አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ከተሾምኩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያገኘኋቸው በቤተ መንግሥት በእራት ግብዣ ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ተገናኝተን አናውቅም፡፡ በዚያን ዕለትም ያሉኝ ምንድነው፣ ‹‹የፍትሕ ሥርዓቱ መስተካከሉን ሕዝቡ እንዲረዳው፣ ፍርድ ቤቶች ከሥራ አስፈጻሚ እኔንም ቢሆን ችሎት ማቅረብ አለባችሁ›› በማለት ፍርድ ቤቶች ያለ ምንም ፍርኃት መሥራት እንዳለባቸው ከማበረታታት ውጪ፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ፈጥረውብኝ አያውቁም፡፡ ሌላም አስፈጻሚ አካል እስካሁን ምንም የፈጠረብኝ ተፅዕኖ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች በተለይ ከመንግሥት ተቋማት ጋር የተገናኙ ከሆኑ ለማስፈጸም ችግር ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ እንዲያውም ‹‹አንፈጽምም›› የሚሉ የተቋማት ኃላፊዎችም ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤቶች አስገድደው የማስፈጸም ኃይል ሲያጡ ይታያል፡፡ ዜጎችም ያገኙት ፍትሕ ከወረቀት ላይ ያልዘለለ ሆኖ የሚቀርበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ፍትሕ ማግኘት ብቻ አይደለም፡፡ ዋናው ችግር አፈጻጸም ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ለማስፈጸም ብዙ ግብግቦች አሉ፡፡ የፍርድ አስፈጻሚ ተቋማችን በደንብ የሚሠራና የተደራጀ ነው፡፡ ዋና ችግሮች ግን ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ውሳኔ ያረፈበት አካል የተለያየ ዘዴ እየተጠቀመ አፈጻጸሙ እንዲዘገይ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል ያ ውሳኔ ያረፈበት መዝገብ ቅርፁን ቀይሮ እንደገና ክርክር ይነሳበታል፡፡ አንድ መዝገብ ሁለትና ሦስት ጊዜ እስከ ሰበር ችሎት የሚደርስበት አጋጣሚ አለ፡፡ በዚህ በዚህ ሁኔታ አፈጻጸሙ ይዘገያል፡፡ በእሱም ላይ ምን መሆን እንዳበትና መፍትሔ ለመስጠት እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በርካታ የውጭ አገር ኢንቨስተሮችና በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ዜጎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በአገር ደረጃ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በግል ሕጋዊ ውሎችን ፈጽመው የሚሠሩ ናቸው፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ ሕግ ይኬዳል፡፡ ክርክሮች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ስለሚካሄዱ የኢትዮጵያ ውሳኔዎችን የማስፈጸም አቅም በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የዓለም ባንክ “Ease of Doing Business” (የንግድ አሠራር ምቹነት) በሚያወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች ትኩረት አድርገው በመሥራት ደረጃቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡ ይኼ ትልቅ ማመላከቻ ነው፡፡ ከውጭ አገር መጥቶ ኢንቨስት ለሚያደርግ ኩባንያ “Ease of Doing Business” ምን ይመስላል? የፍርድ ቤቶች አሠራር ምን ይመስላል? ኮንትራትን ለማስፈጸም (Enforce) እንዴት ነው የሚቻለው የሚለውን ለማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንድ ጉዳዮች አንተም እንደጠቀስከው ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በብቃት ለማስፈጸም የንግድና ኢንቨስትመንት ፍርድ ቤት ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡ እኛም ወደፊት ለማቋቋም እያሰብን ነው፡፡ እንደ Ad hoc Judges ማለትም ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን ጠበቆችን ጭምር የሚይዝ የሕግ ማሻሻያ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች ለተወሰነ ጊዜ የሚታዩበትን ሁሉ እያሰብን ነው፡፡ አስፈላጊም ነው፡፡ እስካሁን ባለን ሒደት ዓለም አቀፍ ፍርድ ሒደቶችን በማስፈጸም ጥሩ ደረጃ ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በፍርድ ቤት የሚገኙ ባለሙያዎችና አጋዥ ሠራተኞችን ሰብስበው ሲያናግሩ በፍርድ ቤት ውስጥ ያለውን አሠራር ያለ ምንም ፍርኃት ግልጥልጥ አድርገው እንደነገሩዎት ተሰምቷል፡፡ በሠራተኛውና በተቋሙ ላይ ምን እየተሠራ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ባለሙያዎችና የድጋፍ ሠራተኞች የሚተዳደሩት በሲቪል ሰርቪስ ሕግ ነው፡፡ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅምን በሚመለከት ጥሩ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ሠራተኞቹ የሚያነሱት ችግር ‹ጄኤጂ› በሚባለው ምደባ ላይ ነው፡፡ ፍልስፍናው ‹‹ሥራና ሠራተኛን ማገናኘት›› የሚል ነው፡፡ ሠራተኞች መመደብ ያለባቸው በልምድ ብቻ ሳይሆን፣ በሥልጠና ባገኙት ዕውቀት መሆን እንዳለበት ፍልስፍናው ስለሚገልጽና በዚያ መሠረት ሲመደቡ ከፍ ዝቅ ስለሚሉ በዚህ ቅሬታ አንስተዋል፡፡ ሌላው ቅሬታቸው የሥራ ቦታ አለመመቻቸት ነው፡፡ ይኼ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ከልደታ ወደ ጦር ኃይሎች የተዛወረው የፍትሐ ብሔር ችሎት ትልቅ ቅሬታ የቀረበበት ነው፡፡ እኔ ጊዜ አግኝቼ ባልጎበኛቸውም በኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች አስቀርጬ ቪዲዮውን ስመለከት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ሠራተኞች እንደተጎዱ ዓይቻለሁ፡፡ በወረዳ አስተዳደር እንኳን ምን የመሳሰለ ሕንፃ በተገነባበት በዚህ ወቅት፣ ፍርድ ቤቶች ግን ችሎት የሚያስችሉት በየመንደሩና በማያመቹ ቦታዎች ነው፡፡ ይኼ የፍርድ ቤቶችን ገጽታ ጭምር ያበላሸ ጉዳይ ነው፡፡ የዳኞቹም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተብሎ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ሦስት ዳኞች በተጠባበቀ ወንበር ነው የሚሠሩት፡፡ ችግር ስለሆነ እንጂ የሥራ ተነሳሽነትን የሚገድል ነው፡፡ አሁን በአጭር ጊዜ ማድረግ የሚቻለው ለድጋፍ ሠራተኞች በተለይ ተጎጂዎቹ ሴቶች ከመሆናቸው አንፃር መዝገብ ተሸክመው ስድስትና ሰባት ፎቅ በእግራቸው ሲወጡና ሲወርዱ ማየት የሚያም በመሆኑ፣ ሊፍት እንዲገጠም አድርገናል፡፡ ሕንፃዎች እስከምንገነባ በልደታ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ቤቶችን ለማሠራት በሒደት ላይ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከአንድ ሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅት ነብዩ የተባለ ሕፃን በጉዲፈቻ ልጃቸው አድርገው ወስደዋል፡፡ ሕፃኑን የወሰዱት በፌዴራል ፍርድ ቤት ቀርበው ሕጋዊ መሥፈርቶችን ካሟሉ በኋላ ነው፡፡ ሕፃኑን በፍርድ ቤት ቀርበው ሲወስዱ እርስዎም ተገኝተው ነበር፡፡ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ፍርድ ቤት ቀርበው ሕጋዊ ግዴታዎችን መፈጸማቸው ሰዎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ላይም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው ብሎ ተደንግጎ ሳለ፣ የቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሕግ ሒደቶችን ከመፈጸም ባለፈ ያደረጉት ነገር ስለሌለ እርስዎ እንደዚያ ብለው መናገር የፈለጉት ምን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔም እዚያ የተገኘሁት ይኼንኑ ለማስተላለፍ ነው፡፡ ለአደጉ አገሮች ቢሆን ይኼ መልዕክት አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ግዴታ ነው፡፡ ሕጉ ቢኖርም እስካሁን ድረስ የመንግሥት ባለሥልጣን ወይም ቤተሰቦቻቸው ፍርድ ቤት ተገኝተውና በችሎት ዳኛ ሲሰየም ቆመው ትዕዛዝ ሲቀበሉ ወይም ግዴታ ሲፈጽሙ ታይተው አይታወቅም፡፡ የሕግ የበላይነትን በቃላት ከመናገር ባለፈ በተግባር ሲፈጽሙ አይታዩም፡፡ የሕግ የበላይነትን የሚጥሱት አቅም ያላቸውና ሥልጣን ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን ሥልጣን ያላቸውም ሆኑ አቅም ያላቸው ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እንደ ማንኛውም ኅብረተሰብ በችሎት ተገኝተው እንደሚዳኙ፣ የቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ድርጊት ምሳሌ ነው፡፡ የራሱ የሆነ መልዕክት አለው፡፡ ሌላው ደግሞ ጉዲፈቻ ይደረግበት የነበረው ሒደት ሕጋዊ መደረግ እንዳለበትም ማስተማሪያ በመሆኑ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...