Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከኢምፔሪያልና ከሪቬራ ሆቴሎች ጋር በተያያዘ በተመሠረተው ክስ ላይ መቃወሚያ ቀረበ

ከኢምፔሪያልና ከሪቬራ ሆቴሎች ጋር በተያያዘ በተመሠረተው ክስ ላይ መቃወሚያ ቀረበ

ቀን:

ከኢምፔሪያል ሆቴል፣ ከሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ፕላስቲክ ፋብሪካ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸውና ዋስትና ተከልክለው በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙት አቶ ኤርሚያስ አመልጋና አቶ ዓለም ፍፁም ላይ የቀረበው ክስ፣ ማሟላት ያለበት የወንጀል ሕግ ድንጋጌን ያሟላ አለመሆኑን ጠበቆች አስታወቁ፡፡

የዓለም ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም በጠበቆቻቸው አማይነት ባቀረቡት የመጀመርያ የክስ መቃወሚያ የቀረበባቸው ክስ እሳቸውን አይመለከትም እንጂ ይመለከታል ቢባል እንኳን፣ የፍትሐ ብሔር ጉዳይ እንጂ ወንጀል አይደለም ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው ክስ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 ድንጋጌ እንዲሟሉ የሚያስቀምጣቸውን የወንጀል ማቋቋሚያ መሥፈርቶችን ያሟላ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ዓለም በመቃወሚያቸው ዘርዝረው እንዳስረዱት፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያቀርብ ተገቢውን ምርመራ አድርጎ ተፈጽመዋል የሚላቸው የወንጀል ድርጊቶች በጠቀሳቸው የሕግ አንቀጾች ሥር የሚወድቁ መሆን አለባቸው፡፡ ማስረጃዎችን ሲመረምርም ለክስ የሚያመቸውን ብቻ ሳይሆን ተከሳሹን ከጥርጣሪ ነፃ ሊያደርገው የሚችልን ማስረጃ መመዘን ያለበት ቢሆንም፣ በአቶ ዓለም ላይ ግን ያቀረበው ክስ ‹‹ራሳቸው ማስረጃዎችን አቅርበው ነፃ ይወጡባቸው›› በማለት መልኩ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ ዓለም ፋብሪካውን ለሜቴክ ሲሸጡ ሁለት የማይሠሩ ማሽኖች መኖራቸውን እያወቁ ሒሳብ ሳይቀንሱ በመሸጣቸው፣ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን በሚመለከት ሲያስረዱ ርክክብ ሲደረግ ሁሉም ማሽኖች ይሠሩ ነበር ብለዋል፡፡ ይኼም በወቅቱ ሲረካከቡ የተሞሉ ሰነዶች ከ200 ገጽ በላይ ተጠርዘው እንደሚገኙና፣ የፋብሪካው ማሽነሪዎች 76 መሆናቸውንና ለእያንዳንዳቸው የመለዋወጫ ዕቃዎች አብረው መሸጣቸውንም አስረድተዋል፡፡ የጠቅላላ ማሽኖች የሽያጭ ዋጋ 6,498,188 ብር ሆኖ ሳለ፣ ዓቃቤ ሕግ ከጠቅላላ ዋጋው 50 በመቶ የሚሆነውን 3,700,000 ብር የሁለት ማሽን ዋጋ አድርጎ ማቅረቡ አግባብ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡ የማሽኖቹ ዋጋ ተቀናሽ ሳይደረግ ክፍያ በመፈጸሙና ማሽኖቹ እስካሁን በመቆማቸው 345,299,758 ብር ጉዳት እንዳደረሰ ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ በክሱ ቢያሰፍርም፣ ክሱ የፍትሐ ብሔርና ከውል ኃላፊነት ውጪ የሚደርስ ኃላፊነትን የሚመለከት የፍትሐ ብሔር ጉዳይ ስለሆነ፣ ጥያቄውን ማቅረብ የሚችለው ገዥው ኮርፖሬሽኑ ከመሆኑ ውጪ፣ በማመሳሰል የሚቀርብ የወንጀል ክስ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡

ገዥና ሻጭ በሕግና በሞራል ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በነፃነት የመዋዋል መብት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ ዓለም፣ ውል በሁለቱ ወገኖች መካከል ሕግ ስለሆነ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ስለታክስ አከፋፈል ተዋዋይ ወገኖች በግልጽ ማስፈር እንዳለባቸው፣ ካላሠፈሩ ግን የሕግ ግምት እንደሚወስድ አክለዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ዓለም ሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ለሜቴክ በ128 ሚሊዮን ብር ሲሸጡ፣ ካፒታል ጌይንና ከሽያጭ በኋላ ያለውን የሊዝ ክፍያ ግን ሜቴክ እንዲከፍል መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡ የግዥው ዋጋ ተጋኗል ባልተባለበት ሁኔታ ገዥ እንዳይከፍል የሚገድብ ሕግ ባለመኖሩ፣ ግብይይቱ ሕጋዊ መሆኑንም አክለዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ዓለም የልዩ ወንጀል ተካፋይ እንደሆኑ ከመግለጽ ባሻገር፣ ዓቃቤ ሕግ አብራርቶ ያቀረበበት የሕግ መሠረት እንደሌለም ገልጸዋል፡፡

ሜቴክ ከንግድ ሥራ የወጣና የንግድ ፈቃዱንም ሆነ ሌሎች ተያያዥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ማቆሙን የሚያስረዱ ሰነዶች በማስረጃ አያይዞ ከማቅረቡ አንፃር፣ ‹‹ትርፍ አጥቷል›› ሊያሰኝ የሚያስችል ብቁ ምክንያት እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡ የአቶ ዓለም የወንጀል ድርሻ ወይም ተሳትፎ ምን እንደሆነ ባልተመለከተበት ሁኔታ፣ የሚከላከሉበትን መከራከሪያ ሐሳብ ማቅረብ እንደማይችሉም አክለዋል፡፡ አቶ ዓለም 7,229,025 ብር ካፒታል ጌይን መክፈላቸውን ጠቁመው፣ ገቢዎችና ጉምሩክ በድጋሚ ጠይቆ ሜቴክ በመክፈሉ ዓቃቤ ሕግ እንደ ስህተት ቢመለከተውም፣ መሆን ያለበት ግን ሜቴክ በስህተት በመክፈሉ ከማስመለስ በስተቀር አቶ ዓለም የወንጀል ድርጊት እንደፈጸሙ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ‹‹ካፒታል ጌይን ታክስ›› እና ‹‹የገቢ ግብር ታክስ›› የሚለው የሕግ ቃል ከአዋጁ አንፃር አሻሚ በመሆኑ፣ አቶ ዓለም ከሁለት አንዱ የትኛው እንደሚመለከታቸው አለመገለጹና 25,911,962 ብር እንዳልተከፈለ ተደርጎ መቅረቡ በምን ሥሌት እንደተገኘ ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹መመሳጠር›› የሚለው ቃል በክሱ ስለተገለጸ ብቻ የሙስና ወንጀል ተፈጽሟል ማለት እንደማይቻል የገለጹት አቶ ዓለም፣ ‹‹መዋዋል›› የሚለው ‹‹መመሳጠር›› ተብሎ ሊተረጎም እንደማይገባና በዕዳ የተያዘ ንብረታቸውን በ128 ሚሊዮን ብር ሸጠው ለልማት ባንክ 95,663,787 ብር መክፈላቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ከሌሎች ተከሳሾች ጋር በጥቅም ተመሳጥረው የሚለው አባባል ግልጽ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ሌላው ዓቃቤ ሕግ ያነሳው ነጥብ ‹‹ምንም ዓይነት ውድድር በሌለበት›› የሚለው ሲሆን፣ እሳቸው ተወዳዳሪ እንዲመጣ ምን ማድረግ እንደነበረባቸው ዓቃቤ ሕግ ካለመግለጹም በተጨማሪ፣ የእሳቸው ዓላማ ንብረታቸውን በማናቸውም ሁኔታ የመሸጥ ሕጋዊ መብት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሆቴሉ ሽያጭ በ2004 ዓ.ም. ተከናውኖ ከጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም ዓይነት ሥራ ባለመሥራቱ፣ ኮርፖሬሽኑ 415,222,069 ብር ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስበት ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ማካተቱን አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ዓለም በነፃ ገበያ መርህ መሠረት ሆቴሉንና ፋብሪካውን በሚያዋጣቸው ዋጋ መሸጥ ሕጋዊ መብታቸው መሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 የተደነገገ በመሆኑ፣ እንደ ወንጀል እንደማይቆጠር ገልጸዋል፡፡ ሆቴሉን መግዛት ወይም አለመግዛት መወሰን የገዥ እንጂ የሻጭ ውሳኔ እንዳልሆነም አክለዋል፡፡      

ሆቴሉ ከተሸጠ በኋላ ስለመሥራቱ ወይም አለመሥራቱ፣ መክሰር አለመክሰሩ ማሰብ ያለበት ገዥ እንጂ ሻጭ እንዳልሆነም አቶ ዓለም በክስ መቃወሚያቸው ላይ አብራርተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን በክሱ ‹‹ሁሉም ተከሳሾች›› የሚለው እሳቸውን ስለማያካትት፣ ክሱን ሊለይ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ሆቴሉና ፋብሪካው ከተሸጠበት ጊዜ ጀምሮ ማስገኘት የነበረበትን ትርፍ ሳይጨምር፣ ያለ ምንም ማጋነን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡ ክሱን ለማካበድና ዋስትና ለማስከልከል የታለመ ስለሚመስል ዓቃቤ ሕግ ትክክለኛና ሚዛናዊ ክስ ማቅረብ እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ 345,299,758 ብር ሜቴክ ትርፍ እንዳጣ አድርጎ ያቀረበው ክስ ግልጽ እንዳልሆነና እንዴት እንዳሰላውና የተከሳሽ ተሳትፎ ምን እንደሆነ እንዳልገባቸው ተናግረዋል፡፡ ሜቴክ ከንግድ መውጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይነግድ ነበር ቢባል እንኳን፣ ይኼንን ያህል ገቢ ሊያስገኝ እንደማይችልና ማሽነሪዎቹም አቅም እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

ማሽኖቹም እየሠሩ ተበላሽተው በመቆማቸው በዓመት የማምረት አቅማቸው ዜሮ መሆኑን ራሱ ዓቃቤ ሕግም ማረጋገጡን አስታውሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የዓቃቤ ሕግ ክስ አቶ ዓለምን የማይመለከት፣ ቢመለከታቸው እንኳን መሆን የነበረበት የፍትሐ ብሔር ጉዳይ እንጂ የወንጀል ጉዳይ ባለመሆኑ፣ ክሱ እንዲሰረዝላቸው ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በክስ መቃወሚያቸው ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡ 

ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ በእነ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የክስ መዝገብ፣ አቶ ዓለም ፍፁምን ጨምሮ 11 ተከሳሾች በቀረቡበት የክስ መዝገብ የተካተቱት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ አቶ ኤርሚያስ የክስ መቃወሚያቸውን በጠበቃቸው በኩል እንዳስረዱት፣ የቀረበባቸው ክስ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 111 እና 112ን የሚያሟላ አይደለም፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ጊዜንና ቦታ አይገልጽም፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ እና ለ) ድንጋጌ መሠረት፣ ወንጀሉ የተፈጸመው በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር ይሁን ምንም የሚገልጸው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ እየተከተለችው ያለው ነፃ የገበያ ውድድር እንጂ የዕዝ ኢኮኖሚ ገበያ አለመሆኑን ጠቁመው፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋጋ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደሚለው የማይንቀሳቀስ ንብረት ዋጋ እየቀነሰ የማይሄድ በመሆኑ፣ አቶ ኤርሚያስ ከ41 እስከ 51 ሚሊዮን ብር ይሸጥ የነበረን ሆቴል በ72 ሚሊዮን ብር ለሜቴክ ሸጠው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባለው ኢምፔሪያል ሆቴል፣ በአሁኑ ጊዜ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጣ አስረድተዋል፡፡ ክሱ የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1815 የጊዜውን የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ የገበያ ዋጋን ያላገናዘበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በተጋነነ ዋጋ የሚለው የዓቃቤ ሕግ መለኪያ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የራስን ንብረት ለመሸጥ ግን መመሳጠር አስፈላጊ እንዳልሆነ አክለዋል፡፡ በአደባባይና በግልጽ የተሸጠ ንብረት መሆኑን፣ በውል ቁጥር 204/2006 ከእሳቸው ድርጅት ከአክሰስ ጋር የሆቴሉ ሕጋዊ ወኪል አቶ ፀጋዬ አስፋው መዋዋላቸውንና መጨረሻ ላይ ሜቴክ ከካርታው ባለቤት ወኪል ጋር ውል መፈጸሙ እየታወቀ፣ ዓቃቤ ሕግ እሳቸውን የሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሌለበትና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 130(2ለ) መሠረት የወንጀል ኃላፊነት እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡

የራስን ንብረት መሸጥ መለወጥ ወንጀል ባለመሆኑና ዓቃቤ ሕግም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23(2) ድንጋጌ መሠረት መሥፈርቱን አሟልቶ ያቀረበው ነገር ስለሌለ፣ ክሱን ውድቅ አድርጎ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠይቀዋል፡፡

የክስ መቃወሚያውን የተቀበለውና ክሱን እየመረመረው የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ዓቃቤ ሕግ ለመቃወሚያው ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ በመስጠት ለጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...