Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በአዲስ አበባ እንዲታይላቸው...

አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በአዲስ አበባ እንዲታይላቸው ጠየቁ

ቀን:

ፖሊስ የዳሸን ቢራ ከፍተኛ ድርሻ በ90 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠበት ሰነድ ሊገኝ አልቻለም አለ

ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ገንዘብ ያላግባብ በማባከንና ማጥፋት የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ረቡዕ ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ማለዳ አዲስ አበባ ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ከሚገኘው ቤታቸው ተይዘው ወደ አማራ ክልል የተወሰዱትና ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ፣ ካለባቸው የጤና ችግርና የቤተሰብ ሁኔታ አንፃር ጉዳያቸው በፌዴራል ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ እንዲታይ ጠየቁ፡፡

በባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ በረከት፣ ከጤናቸው በተጨማሪ ቤተሰቦቻቸውም እሳቸው በታሰሩበት አካባቢ ባለመኖራቸው፣ በአካባቢው የፀጥታ ሁኔታም ለሕይወታቸው ስለሚሠጉ፣ ጉዳያቸው ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ እንዲታይላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታደሰም ባለባቸው የጤና ችግር እንደ ልባቸው መመገብ ስለማይችሉና ቤተሰቦቻቸው በአዲስ አበባ ስለሚኖሩ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወር ጠይቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በማረፊያ ቤት ቆይታቸው ሰብዓዊ መብታቸውንና ክብራቸውን የሚነካ ድርጊት እንደተፈጸመባቸውም ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ካለባቸው የጤና ችግር አንፃር በጥንቃቄ የተዘጋጀ ምግብ እንደሚመገቡ ገልጸው፣ በማረፊያ ቤቱ ምግብ በአግባቡና በሰዓቱ እንደማይቀርብላቸው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በማረፊያ ቤት ዙሪያ የተሰበሰቡ ወጣቶች፣ ‹‹ወንጀለኛ፣ ሌባና ነፍሰ ገዳይ፤›› በማለት ክብራቸውንና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚነካ ድርጊት ፈጽመውብናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የክልሉ መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የመቃወሚያ መከራከሪያ ሐሳብ፣ ሁለቱም የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ከማጥፋት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ የተጠረጠሩበት ኩባንያ የሚገኘውም በአማራ ክልል ስለሆነ ጉዳዩን የማየትና የመመርመር ሥልጣን የክልሉ ፍርድ ቤት መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ጉዳያቸው ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወርላቸው መጠየቃቸው የሕግ መሠረት ስለሌለው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በዋናነት የተጠረጠሩት በጥረት ኮርፖሬት ሥር የሚገኘውን ዳሸን ቢራ ፋብሪካን ከፍተኛ ድርሻ ለአንድ የውጭ ኩባንያ በ90 ሚሊዮን ዶላር እንዲሸጥ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ሽያጩ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያስረዳ ሰነድ ሊገኝ ባለመቻሉ፣ ያንን ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በድጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ ጥረት ኮርፖሬትን በሚመለከት በብአዴን (በአሁኑ አዴፓ) ከፍተኛ አመራሮች፣ በቦርድና በተቋሙ ሲገመገም የቆየና የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን ጉዳዩ አዲስ እንደሆነ በማስመሰል በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ስማቸውን ማጥፋት እንደተያዘ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ጉዳያቸው 90 በመቶ መጠናቀቁ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር የተገለጸና ዋስትናም የማይከለክል መሆኑን በመጠቆም፣ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ባቀረበው መቃወሚያ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፍተኛ ገንዘብ ማጥፋት በመሆኑ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ሰነድ ሊያጠፉና ምስክሮችንም ሊያባብሉ ስለሚችሉ፣ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው የባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት፣ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተጠየቀውን 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለየካቲት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...