Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የድል አጥቢያ አርበኛው በዛሳ?

እነሆ መንገድ። ከጳውሎስ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። አላፊ አግዳሚው ወጪ ወራጁ ከምትፋጀው ፀሐይ ለመጠለል ታዛ እየፈለገ ይሰባሰባል። ተራ አስከባሪዎቹ ‹‹አንድሽም ሳትሠለፊ አትሳፈሪም፤›› እያሉ ያስፈራሩናል። ‹‹እናንተ ሰዎች ለምን አትተውንም ግን? የት እንድረስላችሁ?›› ትላለች የመረራት መሳይ። ‹‹የት ይደረሳል ብለሽ ነው? በየደረሽበት ሁሉ መደብደብ ነው። የማንም ጉልቤ መጫወቻ መሆን። አበቃ!›› ይላሉ አንዲት አዛውንት። ‹‹ወርኃ ጥር ደግሞ ጨፈሩልኝ ብሎ ነው የሚጨፍርብን?›› ይላል ሽበት የወረረው ጎልማሳ። ‹‹ኧረ ዝም በለው ደግሞ በእኔ አሳበው በሉ ብሎ ነው እንጂ፤›› አለ አጠር ቀጠን ያለ መላጣ። ‹‹ማወራረጃ መሆኑ ነው? ታዲያ እኛ መፋረጃ እንጂ ማወራረጃ መቼ ቸገረን? ጊዜም እንደ ባለጊዜው ማባበል ከጀመረማ ምን ቀረን ልጄ?›› ያሽሟጥጣሉ አዛውንቷ። ‹‹ኑና ሠልፍ ያዙ አሁን። አባርቷል…›› ይላል ጥርሰ ወላቃው ተራ አስከባሪ። ‹‹ድሮስ? ሰማይማ ሚዛን ያውቃል። አላባራ ያለን የምድሩ ነው እንጂ፤›› ቆንጂት የአዛውቷን የአነጋገር ዘይቤ እየቀዳች ታሸሙራለች።

‹‹የቤት ኪራይ መክፈል ሳትችይ እንደ ፈረንጅ እያደረገሽ አሁን አንቺም ከእሳቸው እኩል ልትፖተልኪ ያምርሻል? ወገኛ . . . ›› አላት ወላቃው። ‹‹ታውቀኛለህ?›› ‹‹ምን የሚታወቅ አለሽ?›› ንትርክ ሲጀምሩ የተጠለልንበት ካፌ ባለቤት እየተንጎማለለ ገፈታትሮን በመሀላችን አለፈ። ‹‹እስካሁን ለቆማችሁበት ሁለት ሁለት ብር ዱብ ዱብ በሉ ክፍያው ‹ቫት› አያካትትም፤›› ብሎን አረፈው። ይኼኔ አሹቅና ቆሎ በልቶ ለአቅመ እንጀራ የደረሰውን አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ከንፈር ያስመጠጠ ደንዳና ሰውነት ያለው ጠጋ ብሎ፣ ‹‹እውነት አንተ ዘጠኝ ሱሪ ታጥቅሃል ገና ቀኑን ሙሉ ቆሜ እውላለሁ የምታደርገውን አያለሁ፤›› ሲለው ያ የምሩን ገንዘብ ሊቀበለን የመጣው ባለቤት ተብዬ፣ ‹‹ . . . የሚባልበት ዘመን ሊመጣ ምን ቀረው ለማለት ፈልጌ ነው ኧረ?›› ብሎ ታጠፈ። እንግዲህ መተሳሰብና ቀናነትን ለማስመለስ ‹ቦዲ ጋርድ› ሊያስፈልገን ነው ማለት ነው? ወይ ዕዳ ከሜዳ አለ የተራራውን ያላየ!

ወዲያው አንዲት ታክሲ ከተፍ ስትል ሰው ታዛውን ለቆ መሯሯጥ ጀመረ። ታክሲዋ በራፍ ላይ ግብግቡ ጦፈ። አዛውንቷ አልቻሉም። ወጣቶቹ አላዘኑላቸውም። ‹‹ምናለበት እዚያው እንደ ዘመናችሁ እርስ በእርሳችሁ ብትጋፉ? ምን ቤት ነኝ እኔ?›› ይላሉ። ይኼኔ ጎልማሳው ቀድሞ ገብቶ ኖሮ ተጋፍቶ አስገብቷቸው አጠገቡ አስቀመጣቸው። ‹‹እንዲህ እየተጋፋችሁ ነው ገፉን ብላችሁ የምታለቃቅሱት?›› አዛውንቷ ጭራሽ ገብተው ሲቀመጡ ብሶባቸዋል። ‹‹እማማ ይኼ እኮ የታክሲ ወጉ ነው፤›› አላቸው አንዱ ከጋቢና አንገቱን አጣሞ። ‹‹ለካስ ወግም ታውቁ ኖሯል? መልስማ ማን ብሏችሁ?›› እያሉ የነካካቸውን አቡዋራ ከእግራቸው ላይ መጠራረግ ጀመሩ። ይኼኔ አንድ ባሃታዊ መሳይ ከየት መጣ ሳይባል ተከሰተ። ‹‹እያንዳንድሽ ብትሰሚ ስሚ! የስምንተኛው ሺሕ አንደኛው አጋንንት የተሳፈረው መኪና ላይ ነው። እግዜር እግር ሰጣችሁ። እናንተ ግን አራት እግር አማራችሁ። እሱ ጤናችሁን በዕርምጃችሁ ልክ መተረው። እናንተ ግን የባቡር ናፍቆት ገደለን እያላችሁ አላስቆም አላስቀምጠው አላችሁ። አንድ የአጋንንት ሰረገላ ላይ ለመሳፈር ሦስት አራት ሰዓት ትሠለፋላችሁ። ተረግጠን ተገዛን ብላችሁ ስትጮሁ፣ እንኩ ነፃነት ስትባሉ ጦርነት ያምራችኃልና ወዬውላችሁ . . . ›› ብሎ አካባቢውን አደበላለቀው።

‹‹ደግሞ ምን ሊለን ነው? ክርስቶስ በታንኳ አልተሳፈረም እንዴ?›› ትላለች ከመጨረሻ ወንበር መልከ መልካም። ‹‹የሕዝብ ሀብትና ንብረት ላይ በማናለብኝነት ተሰቅለው የሚፋንኑትን እንደ መናገር፣ በሰው አናት ላይ የሚሳፈሩትን እንደ መገሰጽ፣ ታክሲ አትሳፈሩ ብሎ የትዕቢት ጠበቃ መሆን አለ?›› ይላል አጠገቧ የተሰየመ ወጣት ገርሞት። ‹‹እሱ ምን ያድርግ የጫማ ብትል፣ የቤት ምን ወጪ አለበት? እንኳን ተጉዘንበት ቆማችሁብኝ ብሎ ሶላችን ካለቀ እሱ እንደሚለው በእግር ብናቀጥነው ምናችን ይተርፋል?›› ትላለች ሦስተኛው ረድፍ ላይ። ‹‹ደግሞ ብለን ብለን በመኪና አደጋ የምናልቀው አንሶ በእግር እየኳተትን እንለቅ? የዛሬው ደግሞ ሌላ ነው!›› ይላል አንዱ፡፡ እኚያ አዛውንት ግን፣ ‹‹ሰውየው በምሳሌ ሲነግራችሁ አልገባችሁም ማለት ነው፡፡ ማሳረጊያው ነው እኮ ዋናው መልዕክቱ፡፡ ነፃነት እንኩ ስትባሉ ከበዳችሁ ነው እኮ ያላችሁ እናንተ ጉዶች . . . ›› እያሉ ሲናገሩ ምድረ ጥሬ ጭጭ አሉ፡፡

ጉዟችን ከተጀመረ ቆይቷል። ‹‹እስኪ ቀስ እያልክ ንዳ ሾፌር። ይኼ መንገድ እኮ ምሱ በዝቷል፤›› ይላሉ አዛውንቷ ከጀርባው ስለተቀመጡ አሥር ጊዜ ወደ ጆሮው እያሰገጉ። ‹‹አይዞዎት እማማ፡፡ ለ24 ዓመታት ታክሲ የሾፈርኩ ሰው ነኝ። አንድ ቀን ተጋጭቼ አላውቅም፤›› አላቸው። ሾፌራችን ማረጋጋቱ ነበር። ‹‹እስኪ ማል?›› አዛውንቷ ስሜታቸው ግራ ያጋባል። የሚወደውን ታቦት ጠርቶ ማለ። ‹‹እንዲያው ምንም ተጫጭረህ ተነካክተህ አታውቅም?›› ጎልማሳው ነው የሚጠይቀው። ‹‹በጭራሽ!›› ሾፌሩ ባናየውም ደረቱ እያበጠ ነው። ‹‹24 ዓመታት ነው ያልከኝ?›› አዛውንቷ ጫን ብለው ይጠይቁታል። ሾፌሩ አስረግጦ ይመልሳል። ‹‹ማነህ ወያላ አውርደኝ! አውርደኝ!›› እያሉ ታክሲዋ ገና ፍጥነቷ ሳይቀዘቅዝ ከወንበራቸው ተነሱ። ‹‹የት ሊሄዱ ነው?›› ጎልማሳው ራሱ ግራ ተጋባ። ‹‹አትሰማውም እንዴ የሚለውን? እንኳን ሰው ድንጋይ ከድንጋይ ጋር በሚጋጭበት አገር ተጫጭሬም አላውቅ ሲል አትሰማውም? የሰውን ልጅ መፈጠሩን እስኪጠላ ሲያሰቃዩ የነበሩና አገርን በአጥንት ያስቀሩ ወረበሎችም እኮ እንዲህ ነው የሚዋሹት . . . ›› ብለው ፖለቲካውን አዘነቡት። ሌሎቹማ እንደ ጉድ ተጎልተው ያዳምጣሉ፡፡

‹‹ተው አይፍረዱበት! እንከን አልባ ነኝ፣ ይገጩኛል እንጂ ገጭቼ አላውቅም፣ ወዘተ ወሬ የሃያ ምናምን ዓመታት ውጤት ነው። ምን ያድርግ እማማ?›› እያለ ጎልማሳው ማረጋጋቱን ተያያዘው። ‹‹ምነው ኢሕአዴግ በአዲሶቹ መሪዎቹ በአደባባይ ችግሮቹን አምኖ፣ በተለይ ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንም አድርጎት የማያውቀውን በይፋ ይቅርታ ጠይቀው፣ እኛ ምን አስቸገረን? ይኼው ራስን ዘወር ብሎ ዓይቶ ችግርን አለማመን፣ ሒስን ያለመቀበል ፅኑ አባዜ አይደለም እንዴ ያስቸገረን? ሰው እንሁን ሲባል ሰይጣን ካልሆንን እያልን በአደባባይ በመወጣጠራችን መስሎኝ አዙሮ እየደፋን ከመንገድ ሲያስቀረን የኖረው?›› ሲሉ አዛውንትዋ ተሳፋሪዎች ዕይታቸው ተመችቶት ጭብጨባ ቃጣቸው። አጨብጭበውላቸው ያጨበጨቡባቸው ትዝ አሉዋቸው መሰል ሁሉም መዳፋቸውን እያፋተጉ ዝም አሉ። የምንተፋፈገው ሳይበቃ አፋትገን የምናመነጨው ሙቀት ስንት ዲግሪ ሴሊሺየስ ይሆን? የስንቱን ግዝትና መሀላ አምነን አጨብጭበን የቀረንስ ምን ያህል እንሆን? ስንቱን እንደ ነፃ አውጪ የቆጠርን እንሆን በተራ ድርጊቱ አፍረን ኩም ያልነው፡፡ መጥኔ አሉ የሰለቻቸው፡፡

ወያላው ሒሳብ ይሰበስባል። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመችው ወይዘሮ በሞባይል ስልኳ ታወራለች። ‹‹በይ እየመጣሁ ነው ቡናውን አቀራርበሽ ጠብቂኝ። በዛችኛዋ በትንሿ ድስት አወቅሻት? ገንፈልፈል አድርገሽ ሥሪው። ይኼው በር ላይ ነኝ። ወየውልሽ ቴሌቪዥን ስትጎረጉሪ ባገኝሽ . . . ›› ትላለች። ‹‹ይገርማል እኮ ዘንድሮ የምንቀጥራቸው የቤት ሠራተኞች ይሁኑ የዲሽ ፊልም ተመልካቾች ግራ ያጋባል፤›› አላት ከጎኗ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ተወኝ እስኪ! የእኔይቱ ደግሞ ለየት ያለች ናት። ማየቱንስ ትይ። ብቻ አንድ ነገር ሳወራ ከአፌ ነጥቃ እከሌ እኮ እንዲህ የሆነው እንዲያ ተብሎ ነው። መቼ ዕለት ‹ኢንተርቪው› ሲደረግ ሰምቼዋለሁ ትልልሃለች። ይኼው በእሷ የተነሳ እንግዳ ቤቴ መጥራት እስከ ማፈር ደርሻለሁ። ሰሞኑን ደግሞ የገና ዶሮ ሁለት ቀን ሳይበላ ማለቅ። ‹አለቀ?› እላታለሁ፣ እህሳ የዘንድሮ ዶሮ እንደ በፊቶቹ ሞኝ አይደሉም። ዕድሜ ለዘመነ ኢንተርኔት ነቅተዋል። መታረጃቸውን ስለሚያውቁት ኪሎ ቀንሰው ሆኗል ገበያ የሚወጡት፤›› አትለኝ መሰለህ?›› ስትል ተሳፋሪዎች ያሽካካሉ። ‹‹አንዳንዴ እኮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁሉም ሰው በየቤቱ ተንታኝ ሆኖ ባለሙያዎችን እያስናቀ ነው . . . ›› ነው የሚሉት እኚያ እናት ናቸው፡፡

ሴትየዋ ጨዋታው እንደ ጣመን ገብቷት ድምጿን ከፍ አደረገች። ‹‹ቆይ ልነግራችሁ እኮ ነው። እኔ ደግሞ ግራ ገብቶኝ መቼም የዛሬ ዘመን ሥልጣኔ አይታመን ብዬ ዶሮዎች ኢንተርኔት መጠቀም ጀምረዋል? አልጀመሩም? ብዬ አጣራለሁ ስል ቴሌ ካርዴን አጣራልኛ። ወይ ለኩላሊት ሕሙማን መርጃ አላዋጣሁት፣ ወይ ለህዳሴው ግድብ አልሰጠሁት። ለራሱ ገንዘቡ ጥንቡን ጥሏል። እንኳን ስለዶሮ ንቃተ ህሊና ልናጠናበት ለራሳችንም አልሆነ . . . ›› እያለች ስታስቀን፣ ‹‹አርዝመው አስረውን የፈቱን የመሰለንማ እኛን ነው . . . ›› እያለ አጠገቤ የተቀመጠ ባለ ባርኔጣ ይንሿከክብኛል። የቱን አንስተን የቱን እንደምንጥል ጨንቆናል ልበል? ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፣ ዛሬ አዲስ አድርጋ ትነዛብን ጀመር፤›› ብሎ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች አንደኛው ነገር ጎነጎነ። ወያላችን ሳንቲም እየመለሰ ነው። ‹‹ዛሬስ እንዴት ወግ ደርሶሃል እባክህ? ለመሆኑ ይኼኛው ሳንቲማችንም እየተመለሰልን ያለው በሱዳን በኩል ነው እንዴ?›› አለች ወይዘሮዋ። ‹‹ትንሽ ከጠበቅን ኢሳያስ አፈወርቂ ኤርትራን ጠቅልለው አንድ እንሁን ይላሉ፤›› እያለ ከወዲያ  ያለው ይናገራል። ‹‹እሰይ! ታዲያ አደራውን እንደ አጀማመሩ የሩቅ ሩቁን ብቻ ሳይሆን የቅርቡንም አመፀኛ ትጥቅ ያስፈታልና . . . ›› ብሎው አዛውንቷ ጨመሩበት። ‹‹ደግሞ የምን የቅርብ ጠላት አመጡብን? የቅርቡን ታቅፈን ኖሯል በሩቆቹ ላይ የምንሸልለው?›› ሲላቸው ጎልማሳው፣ ‹‹እንግዲያስ! ሌብነት፣ ድንፋታ፣ ያለ ችሎታቸው በየቦታው እየተሰገሰጉ ጤና የሚነሱን ካድሬ ተብዬዎች፣ በስብሰባ ብዛት የሚቃጠለው ዕድሜያችን፣ በሰላም ገብተህ ተፎካከር የተባለው ጠመንጃ አንግቶ ሲፎክር፣ ትናንት አንገቱን ደፍቶ ሲያለቅስ የነበረ ፈሪ ሁሉ ሌሎች ተጋፍጠው ባመጡት ነፃነት የድል አጥቢያ አርበኛ ሲሆንና አገር ምድሩን ሲሞላው፣ ኧረ ስንቱን አንስቼ እጨርሰዋለሁ… በተለይ የድል አጥቢያ አርበኛው ላያችን ላይ ሲያገሳ ያንገሸግሸኛል…›› ሲሉ የታክሲያችን ጉዞ ተጠናቀቀ። ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ›› ብሎን ወርደን ስንበታተን ከጎኔ ተቀምጦ የነበረው፣ ‹‹እውነታቸውን እኮ ነው። የላይኛው ጌታ የድል አጥቢያ አርበኛውን ልክ እንድናስገባው ልብ ቢሰጠን ምን አለበት?›› ብሎኝ ወደፊት ገሰገሰ። የሆነስ ሆነና የድል አጥቢያ አርበኛው መብዛት ግርም አይልም? መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት