Monday, June 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ምስክሮች ለቀዳሚ ምርመራ እንዲቀርቡ መጠየቁ ተቃውሞ አስነሳ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች ምስክሮች ለቀዳሚ ምርመራ እንዲቀርቡ መጠየቁ ተቃውሞ አስነሳ

ቀን:

አንድ ተጠርጣሪ በሃምሳ ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ታዟል

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች፣ የሚደረግባቸው ምርመራ ተጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ ይሰጣል ብለው ሲጠብቁ፣ ዓቃቤ ሕግ ቀርቦ ተጠርጣሪዎቹንና በእነሱ ላይ የተቆጠሩትን ምስክሮች ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት የሚያቀርብበት ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ በተጠርጣሪዎቹ ተቃውሞ አስነሳ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል ያላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን የምርመራ ሒደት አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለፌዴራል ዓቃቤ ሕግ አስረክቧል፡፡

- Advertisement -

የምርመራ መዝገቡን የተረከበው ዓቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) ድንጋጌ መሠረት የምርመራ መዝገቡን በመመርመር ክስ ለመመሥረት፣ ወይም ተጠርጣሪዎችን በነፃ ለማሰናበት የተደነገገውን የ15 ቀናት ጊዜ ይጠይቃል ተብሎ ቢጠበቅም አልጠየቀም፡፡ ዓቃቤ ሕግ በጊዜ ቀጠሮ ችሎት ማለትም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ያስረዳው፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃል የተቀበላቸውን ግለሰቦች የምስክርነት ቃል ለማስጠበቅ (ሕጋዊ ለማድረግ) ቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት አቅርቦ ማረጋገጥ እንዳለበት ነው፡፡ በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምስክርነታቸውን የሰጡ ግለሰቦችን በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር እንዳስረዳው፣ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ጉዳት ደርሶባቸው ሕይወታቸው አልፏል ስለተባሉ ግለሰቦች፣ ቃል የተቀበላቸው ምስክሮችና ከሕክምና ተቋማት የተገኘው የሰነድ ማስረጃ የተወሰነ ልዩነት ስላለው፣ የሕክምና ባለሙያዎችን በቅድመ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት በማቅረብ ማረጋገጥ እንዳለበት አስረድቷል፡፡

ይኼም የሚሆነው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 83(2) ድንጋጌ መሠረት መሆኑን ጠቁሞ፣ ፍርድ ቤቱ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት የተጠርጣሪውን ቃል ተቀብሎና አስፈርሞ የመዝገቡ አካል ማድረግና በተመሳሳይ ሁኔታ የምስክሮችን ቃልም በፍርድ ቤቱ ፊት አረጋግጦ የመዝገቡ አካል ማድረግ፣ ክስ ሲመሠረት በማስረጃነት ከመቅረቡም በተጨማሪ በክርክር ሒደት በጣልቃ ገቦች ምክንያት በሰነዶች ላይ ልዩነት እንዳይኖር እንደሚከላከልም ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ የተቃወሙት በእነ ጎሃ አጽብሃ የምርመራ መዝገብ የሚጠሩና ለአራት ተከፍለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙት ተጠርጣሪዎች፣ ከሁሉም በፊት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ትዕዛዝ የተሰጠው መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ እንዲቀርብ እንጂ፣ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንዲጠይቅ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 83(2) የሚጠቅሰው ወይም ተጠርጣሪና ምስክሮች ለቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የሚያዘው፣ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ወይም በከባድ ውንብድና ወንጀል የተጠረጠረን እንጂ እነሱን እንደማይመለከት አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሌላው ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው ጥያቄ ተጠርጣሪዎቹ ፎቶ ለመነሳት ፈቃደኛ አለመሆናቸውንና ያንን በሌላ ማስረጃ ለመቀየርም ጊዜ የሚያስፈልገው መሆኑን በሚመለከትም ተጠርጣሪዎቹ ተቃውመዋል፡፡ እነሱ እንደሚሉት ፎቶግራፍ ማንሳት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ፎቶግራፋቸው ካስፈለገ ይሠሩበት በነበረው ተቋም ሙሉ መረጃቸው ስለሚገኝ ከዚያ መውሰድ ይቻላል፡፡ ይኼ ለፍርድ ቤቱ የሚቀርብ ሳይሆን ቧልት የሚመስል ነገር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የሕክምና ማስረጃን ከምስክሮች ቃል ጋር ለማመሳሰል ባለሙያ ማነጋገር፣ እነሱን ከማሰር ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ መቀጠል የሚችል ቢሆንም፣ ከዓቃቤ ሕጉ ንግግር የተረዱት ነገር ቢኖር ወይም የሰነዱና የምስክሮቹ ቃል መለያየት የሚሳየው ምንም ወንጀል አለመኖሩን እንደሆነ ነው፡፡ ጊዜን ተከትሎ ማሊያ በመቀየር እውነትን ለማውጣት መሯሯጥ እውነተኛ መንገድ (ውጤት) ላይ መድረስ እንደማያስችልም አክለዋል፡፡

ምርመራው እየሄደበት ያለው አግባብ ትክክል እንዳልሆነ፣ ትክክኛ የነበረው አሠራር ወንጀል ነው ከተባለ ደግሞ አሁንም በኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ስላሉ መጠየቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ሴት ደፍሮ ብልት መስፋቱ የተረጋገጠበት ወንጀለኛ በነፃ እየተሰናበተ፣ እነሱ ለአገር በመሥራታቸው መታሰራቸው አግባብ ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸውና ፍርድ ቤቱን እያሳሳቱ ጊዜ የሚወስዱት ዓቃቤ ሕግና መርማሪ ቡድን ሃይ ሊባሉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የሚከራከሩት በሕግ ጉዳይ ቢሆንም፣ በእነሱ ላይ እየቀረበ ያለው ምርመራ ግን ከመጀመርያው ጀምሮ ወንጀል እንዳልሆነም አክለዋል፡፡        

እነሱን በማጉላላትና በማሰቃየት የተወሰኑ አካላትን ለማስደሰት ስለሆነ፣ ዕጣ ፈንታቸው የሰጣቸውን እየተቀበሉ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲያውቅላቸው ጠቁመዋል፡፡ የተጠረጠሩበትን ማንኛውንም ጉዳይ የበላይ ኃላፊዎች ሳያውቁትና ሳያረጋግጡት ያደረጉት ነገር እንደሌለ ተናግረው፣ መጠየቅ ካለባቸውም እነሱ ሳይሆኑ አሠራሩ ትክክል መሆኑን አረጋግጦ ያዘዛቸው ኃላፊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በግላቸው የሠሩት እንደሌለ፣ ቢኖር እንኳን ተቋሙ ዝም ሊላቸው ስለማይገባ ተቋሙ መጠየቅ ስላለበት፣ ፍርድ ቤቱ በሕግና ሥርዓቱ መሠረት ሊዳኛቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ ባቀረበው ክርክር ለፍርድ ቤቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 83(2)ን ጠቅሶ፣ ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊና ተገቢ መሆኑን አስረድቷል፡፡ አንቀጹ ከባድ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ቢልም፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁትር 25/88 አንቀጽ (12) ላይ ስለ ሰብዓዊ መብት ጥሰትም በግልጽ ተደንግጎ ስለሚገኝ፣ የተጠርጣሪዎቹ  መቃወሚያ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎች መከሰስ ያለበት ተቋሙ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚናገሩ ቢሆንም፣ እነሱ የሠሩትንና የሠሩበትን ሁኔታ ተከትሎ እየተጠየቁ መሆኑን ማወቅ እንዳለባቸወም አክሏል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለዓቃቤ ሕግ የቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ስለሚያቀርባቸው ምስክሮች፣ ስለሚቀርቡበት ጉዳይ ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ስለመሆኑ ማለትም፣ የተጠረጠሩት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በመሆኑ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት ቀርበው ስለሱ ስለመጠየቃቸውና ሌሎች ጥያቄዎችንም አቅርቦ ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ለሥራው አመቺ እንዲሆንለት አራት ቦታ ተከፋፍሎ እንዲመረምር ፍርድ ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ፣ ‹‹በአንድ መዝገብ ክስ ስለምናቀርብ›› በማለት ሁሉንም በአንድ ላይ በቀዳሚ ምርመራ አድራጊ ፍርድ ቤት እንዳቀረበ ሲያስረዳ፣ ‹‹እናንተ እንደፈለጋችሁ ሥሩ፡፡ ግን ፍርድ ቤቱ ባዘዛችሁ መሠረት መሥራት አለባችሁ፤›› በማለት ገስጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የተጠርጣሪዎቹን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ፣ በምክትል ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን፣ ኢንስፔክተር ፈይሳ ደሜና ምክትል ኢንስፔክተር ምንላርግልህ ጥላሁን (ሁሉም የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መርማሪዎች የነበሩ ናቸው) እና ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን ላይ ዘጠኝ ቀናት ፈቅዷል፡፡ በኦፊሰር ገብረ ማርያም ወልዳይ፣ ኦፊሰር አስገደ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አዳነ ሐጎስ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተስፋ ሚካኤል አስገደ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን፣ ረዳት ኢንስፔክተር ዓለማየሁ ኃይሉና ረዳት ኢንስፔክተር መንግሥቱ ታደሰ (ሁሉም የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበሩ ናቸው) ላይ የሰባት ቀናት ጊዜ ተፈቅዷል፡፡ ከኦፊሰር ገብረ ማርያም ወልዳይ በስተቀር በሁሉም በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ጊዜ የተሰጠው በአብላጫ ድምፅ ነው፡፡ በኦፊሰር ገብረ ማርያም ላይ ሁሉም ዳኞች ተጨማሪ ጊዜውን በሙሉ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

በዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ሐዋርያት ላይ በቂ ማስረጃ እስከሚያሰባስብ ድረስ በዋስ ቢወጡ እንደማይቃወም ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት በመግለጹ፣ በ50 ሺሕ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የመርማሪ ቤት ተጠርጣሪዎች ለጥር 20 እና የፌዴራል ፖሊስ  ተጠርጣሪ መርማሪዎች ለጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...