Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ለሜቴክ በሸጡት ኢምፔሪያል ሆቴል ምክንያት በሙስና ወንጀል ተከሰሱ

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ለሜቴክ በሸጡት ኢምፔሪያል ሆቴል ምክንያት በሙስና ወንጀል ተከሰሱ

ቀን:

የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤትም በ415.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት  ተከሰዋል

የአክሰስ ሪል ስቴትና የዘመን ባንክ አክሲዮን ማኅበራትን በመመሥረትና በመምራት የሚታወቁት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ኢምፔሪያል ሆቴልን ለሜቴክ ከመሸጣቸው ጋር በተያያዘ የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው፡፡

ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት ማክሰኞ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀረቡት አቶ ኤርሚያስ፣ ከሜቴክ ኃላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በወቅቱ (በ2003 ዓ.ም.) ከ41 ሚሊዮን  እስከ 51 ሚሊዮን ብር የሚገመተውን ኢምፔሪያል ሆቴልን በ72 ሚሊዮን ብር ሜቴክ እንዲገዛቸው በማድረግ፣ በመንግሥት ላይ የ21 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ማድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

 አቶ ኤርሚያስ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ እንደገለጹት፣ ኢምፔሪያል ሆቴልን ለሜቴክ ሸጠዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው ሳይሆን፣ ሁለት ሚሊዮን ብር ከስረው ሆቴሉን መሸጣቸውን አስረድተዋል፡፡ ኢምፔሪያል ሆቴልን ከአቶ  አስፋው ተፈራ ሕጋዊ ተወካይ አቶ ፀጋዬ አስፋው በ70 ሚሊዮን ብር መግዛታቸውን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ 47 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 23 ሚሊዮን ብር ደግሞ ያለበትን የባንክ ዕዳ ለመክፈል መስማማታቸውንና የግዥ ውል መፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 47 ሚሊዮን ብር በ18 ወራት ክፍያ ለመፈጸም መስማማታቸውንም አክለዋል፡፡ ሆቴሉን ከገዙ በኋላ ዘግተውት እንደነበርና የሜቴክ ኃላፊዎች እንደሚገዙ ሲነግሯቸው ቫትን ጨምሮ 72 ሚሊዮን ብር መሸጣቸውን ገልጸዋል፡፡ ለአቶ ፀጋዬ አስፋው ሙሉ ክፍያ ስላልፈጸሙና ስመ ሀብቱ ባለመዛወሩ፣ ሜቴክና አቶ ፀጋዬ አስፋው ውል መፈጸማቸውንም አክለዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በሥራ አስኪያጅነት የሚወክሉት አክሰስ ሪል ስቴት ከግብይይት ሒደቱ መወጣቱን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ አክሰስ ሪል ስቴት በሕግ ፈርሶ ኅልውናውን ማጣቱን ገልጸው፣ እሳቸው በምን የሕግ አግባብ እንደታሰሩ እንዳልገባቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

በአንድ የፌዴራል ፖሊስ አመራር (ስም እየጠሩ) በተደጋጋሚ እየተጠሩ ቃላቸውን እንዲሰጡና ምስክር እንዲያመጡ ሲጠየቁ ከርመው በሆነ ወረቀት ላይ እንዳስፈረሟቸው ጠቁመው፣ ‹‹እኔ ጉቦ አልሰጥ ገንዘብ የለኝ፣ የሰነድ ማስረጃ እንዳልደብቅ ከሆነ ሁሉም የሰነድ ማስረጃ እነሱ ጋ ነው፡፡ ከአገር እንዳልወጣ ዕግድ ተጥሎብኛል፡፡ ለምንድነው ታስሬ ማስረጃ የሚፈለግብኝ? ሥርዓቱ የተሻሻለ መስሎኝ ነበር፣ ያው ነው፡፡ ለመርማሪው አንድም ቀን መፈቀድ የለበትም፡፡ ንፁህ ሰው ማሰር የቀረ መስሎኝ ነበር፡፡ የተቀየረ ነገር የለም፡፡ ፍርድ ቤቱ ንፁህ ሰው መታሰር እንደሌለበት ማሳየት አለበት፤›› በማለት ሳግ እየተናነቃቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በድጋሚ ባቀረበው መከራከሪያ ሐሳብ አቶ ኤርሚያስ ያነሱት ብሶት ከምርመራው ጋር እንደማይያያዝ ጠቁሞ፣ በተጠርጠሩበት ወንጀል ብዙ ማስረጃዎችን መሰብሰቡንና በችሎት ሳይሆን በዳኞች ጽሕፈት ቤት የምርመራ ሒደቱን ማሳየት እንደሚፈልግ በመጠቆም፣ የጠየቀው አሥር ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ የምርመራ መዝገቡን ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት በዕለቱ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ከቀትር በኋላ ትዕዛዝ ለመስማት ፍርድ ቤት የተገኙት አቶ ኤርሚያስ ያጋጠማቸው የዳኞችን ትዕዛዝ መስማት ሳይሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ቀርቦ በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ላይ ክስ መመሥረቱን የሚያረጋግጥበት የክስ መዝገብ ቁጥር ለፍርድ ቤቱ በመንገር የምርመራ መዝገቡ እንዲዘጋለት ነው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት የምርመራ መዝገቡን መዝጋቱን ካሳወቀ ከደቂቃዎች በኋላ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ኤርሚያስን ጠርቶ የተመሠረተባቸውን ክስ ሰጥቷቸዋል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው አቶ ኤርሚያስ ክስ የተመሠረተባቸው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ከነበሩት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውና የሜቴክ የተለያዩ መምርያዎች ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከነበሩበት ኮሎኔል በርሄ ወልደ ሚካኤል፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል፣ ብርጋዴር ጀኔራል በርሄ በየነና የተለያዩ ክፍል ኃላፊዎች የነበሩት ኮሎኔል ስለሺ ቤዛ (በሌሉበት)፣ ኮሌኔል ስምረት ኪዳነ፣ ኮሎኔል ግርማ መዘርጊያ፣ ሻምበል አግዘው አልታዬና የዓለም ገነት ቆርቆሮ ባለቤት ከአቶ ዓለም ፍፁም ጋር ነው፡፡

አቶ ኤርሚያስም የተከሰሱት ከላይ እንደተጠቀሰው ኢምፔሪያል ሆቴልን የጥገና ወጪ ሦስት ሚሊዮን ብር በመጨመር በ75 ሚሊዮን ብር ለሜቴክ ከመሸጣቸው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ይህም የተፈጸመው ከሜጀር ጀኔራል ክንፈ፣ ከኮሎኔል በርሀ፣ ከኮሎኔል ስምረት፣ ከኮሎኔል ግርማና ከሻምበል ግዛው ጋር መሆኑን ክሱ ያስረዳል፡፡ በአጠቃላይ ሆቴሉ  በወቅቱ  ከ41 ሚሊዮን እስከ 51 ሚሊዮን ብር በሚገመትበት ወቅት፣ 72 ሚሊዮን ብር በመሸጥ በመንግሥት ላይ የ21 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸውን በመግለጽ፣ በልዩ ወንጀል ተካፋይነትና ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የዓለም ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁም፣ በአጠቃላይ በመንግሥት ላይ የ415,222,069 ብር ጉዳት አድርሰዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ አካቶ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

የሜቴክ ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በክስ መዝገቡ የተጠቀሱ ስድስት ኃላፊዎች የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት ከአቶ ዓለም ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ 4,371 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ፒቪሲ ፕሮፋል ማምረቻ ፋብሪካ ሜቴክ ግዢ እንዲፈጽም መደረጉን ክሱ ያብራራል፡፡ የፋብሪካው ስፋት 6,941 ካሬ ሜትር ቢሆንም፣ 11,000 ካሬ ሜትር እንደሆነ በማድረግ በ128 ሚሊዮን ብር የግዥ ውል መፈጸሙንም ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡ አቶ ዓለም የካፒታል ዕድገት ክፍያ መክፈል ቢኖርባቸውም ሜቴክ እንዲከፍል በማድረግ 7,229,025 ብር ቅጣት ተጨማሪ ክፍያ መፈጸሙንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡

የፒቪሲ ፕሮፋይል ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ የነበሩና የማይሠሩ ሁለት ማሽኖች ዋጋ ሳይቀነስ ግዥ በመፈጸሙና ማሽኖቹ ሳያመርቱ በመቅረታቸው፣ ሜቴክ ያገኝ የነበረውን 345,255,758 ብር ትርፍ ማጣቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ 415,222,069 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት በመድረሱ አቶ ዓለም በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆናቸውና ሌሎቹ ተከሳሾቹ ደግሞ ሥልጠናቸውን ያላግባብ በመገልገላቸው፣ በከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክሱን ለተከሳሾች በችሎት አንብቦ፣ የክስ መቃወሚያ ካላቸው የሚያቀርቡበትን ጊዜ ለመጠየቅና የመብት ጥያቄ የሚያቀርቡ ከሆነ ሰምቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለረቡዕ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...